በገንዘብ ራስን ለመቻል ቁልፉ የገንዘብ ፍሰት ቁጥጥርን ማወቅ ነው።

የገንዘብ ፍሰት /Cash Flow/

በገንዘብ ራስን ለመቻል ቁልፉ የገንዘብ ፍሰት ቁጥጥርን ማወቅ ነው።

በኮርፖሬት ቢዝነስ ዓለም ይሁን ወይም በኪዮስክ ንግድ አለያም በግል የቤተሰብ ኑሮ የገንዘብ ፍሰት ቁጥጥር ላይ ያለ ቸልታ ህልውናን የሚገዳደር ነው።

ብዙዎች “ወጪን መቀነስ ላይ ማተኮር ለስኬት ያግዛል፣ ውድቀትንም ይከላከላል” ብለው ያስባሉ። ወጪን መቀነስ ጠቃሚ የሚሆንበት ሁኔታ ያለ ቢሆንም፣ ለስኬት ጠቃሚው የገንዘብ ፍሰትን ተቆጣጥሮ ትርፍ ጥሬ-ገንዘብ እንዲኖር ማስቻል ነው።

ዘጠኝ ብር ገዝቶ ዘጠኝ ብር መሸጥ
ትርፉ ዘጥ ዘጥ

እንዲሉ አንዳንድ ንግድ እንዲያ ነው – ልፋት ብቻ። የብዙዎች ተቀጣሪዎች ኑሮ (ይህም ያው ንግድ ነው) ግን ዘጠኝ ብር ገዝቶ ዘጠኝ ብር መሸጥ ዓይነት ንግድ ነው።

20,000 ብር የወር ደመወዝ ያለውን ሰው በምሳሌ እንውሰድ። በነገራችን ላይ ብዙ ሰው 20,000 ብር ደመወዝ አያገኝም። የ20,000 ብር የወር ደመወዝተኛ ሰው ሌላ እዳ ከሌለበት ከታክስና የጡረታ ተቀናሽ በኋላ 13,000 ብር ያህል የተጣራ የወር ገቢ ይደርሰዋል። ከዚህ ውስጥ የቤት ኪራይ ቀድሞ ይከፍላል። የቤት ኪራዩ 5,000 ብር ቢሆን 8,000 ብር ይቀረዋል። ለምግብ፣ ለመብራትና ውኃ ክፍያ፣ ለትራንስፖርት፣ ለልጆች ትምህርት ቤት፣ ለልብስ የሚውለው ክፍያ እንግዲህ ይህ ቀሪ ብር ነው። ይህንን እንግዲህ ለአሠሪው በዱቤ ሠርቶ ደመወዝ ይጠብቃል። እንደሚታየው ከዚህ ላይ የሚተርፍ ጥሬ-ገንዘብ ለማግኘት መሟሟት ከንቱ ትግል ነው። የብዙ ወገኖች ኑሮ እንዲህ በመፍጨርጨር የሚባክን ነው።

ወጪን ለመቀነስ ከመታገል ይልቅ ገቢን ለመጨመር መጣጣር የገንዘብ ፍሰትን ለማሻሻል ይረዳል።

በነገራችን ላይ ድርጅት የሚዘጋው በትርፍ ማጣት ሳይሆን በገንዘብ ፍሰት ችግር ነው። የትዳር ኑሮና የላጤ ነጻነትም የሚናጋው በገንዘብ ፍሰት አስተዳደር ችግር ነው። ላጤ የገንዘብ ፍሰት ችግር ሲያጋጥመው ገቢን ለመጨመር/ወጪን ለመጋራት ጋብቻን እንደ አማራጭ መውጫ ይወስዳል። ይህ ግን ችግሩን ለመቅረፍ ሊያግዝ ወይም ላያግዝ ይችላል። ቁልፉ የገንዘብ ፍሰት አስተዳደርን ማወቅ ነው።

የጥሬ-ገንዘብ ፍስትን ለመጨመር ገቢን መጨመር፣ ወጪን መቀነስ፣ ወጪን ማዘግየት፣ ወጪን መጋራት ፊት ለፊት ያሉ አማራጮች ናቸው።

ታዲያ ገቢን እንዴት እንዲጨምር ማድረግ ይቻላል? የገንዘብ ፍሰትስ በሌሎች መንገዶች እንዴት ሊጨምር ይችላል?

አንዱ መንገድ በያዝከው መስክ ጠንክረህ በብልሃት በመሥራትና የሌሎችን ችግር በመፍታት ታዋቂነትን መገንባት ነው። ራስህንና ሥራህንና ፋይዳውን ደግመህ ደጋግመህ አስተዋውቅ። ለማስተዋወቅ አትፈር። ኮካ ኮላ ይህን ሁሉ የዓለም ህዝብ አውቆትም አሁንም እያስተዋወቀ መሆኑን ልብ በል።

ሌላው መንገድ ያለህበትን Ecosystem መቀየር ነው። ችግሩ በተፈጠረበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ችግሩን መፍታት አይቻልም ይባል የለ? ያለህበት ካልተስማማህ፣ ካልወደድከው፣ በአጥጋቢ ካልከፈለህ ያለህበትን ውሎ፣ የሥራና ትምህርት መስክ፣ መ/ቤት፣ ከተማ ወይም አገር ቀይር። “እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል” ነው ነገሩ።

ሌላው መንገድ ገቢ የማፍራት ዓቅም ያለው ብራንድ መገንባት ነው። Betty Tafeese በመጽሐፏ እንደነገረችን በLTV ላይ ስትሠራ የወር ደመወዟ 60,000 ብር ነበር አይደል? ብዙ ጋዜጠኛ እንደዚያ ዓይነት ገቢ አያገኝም ነበር። አሁንም በተሻለ የወር ገቢ ልትጀምር መሆኑን ሹክ ሹክታ ሰምተናል። ቤቲ እንዴት ብራንዷን ገነባች? ማጥናት ነው።

ሌላው መንገድ በውስጥ ያለን ዓቅም መጠቀም ነው። ያለህ ዓቅም ምንድን ነው? ውበት፣ ጉልበት፣ እውቀት፣ የንግግር ችሎታ፣ የጥንካሬ መንፈስ፣ ድምጽ፣… ልዩ ዓቅምህ ምንድን ነው? በተለይ ለየት ያለ ዓቅም ካለህ እንደኔ አትተኛ! ዳዊት ጽጌን ዓይተሃል አይደል? ገንዘቤ ዲባባንስ?

ዶ/ር ምህረት ለስልጠና ስንት እንደሚከፈለው ታውቃለህ? ፈልግና ስማ! ሌሎችን ጠቅሞ ራስን መጥቀም እንዲያ ነው። የስልጠና ፍላጎት ያለው ድርጅት ካገኘህ እንደኔ የማሰልጠን ችሎታ ካለው ጋር ተባብረህ ሥራ።

ሁሉን ነገር ከ4 ወይም 5 ወይም 6 እና 7 ዓመት የኮሌጅ ትምህርት ጋር ብቻ አታስተሳስር። ሰይፉ ፋንታሁን፣ ቴዲ አፍሮ፣ ሠራዊት ፍቅሬ፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ስኬታቸውን ከኮሌጅ ደጃፍ አላመጡትም። ባለህ ዓቅም ሥራ፣ ሥራ፣ ሥራ! ለመሻሻል አጫጭር ስልጠና ውሰድ፣ ከቻልክበት ደግሞ አሰልጥን። ደግሞ አንብብ፣ አንብብ፣ አንብብ!

ሌላው የገንዘብ ፍሰት ማሻሻያ መንገድ ዓቅምን ማስተባበር ነው። አክሲዮን ማህበራት ዓቅምን የማስተባበሪያ አንድ መንገድ ናቸው። Kefelegn Hailu አዲስ አክሲዮን ማህበራት ካሉ ሹክ በለን እስቲ?

እነዚህ just ጥቂት መንገዶች ናቸው። ሌሎች አማራጮችም በሽ ናቸው። Infinite Possibilities እንበላቸው ይሆን?

መልካም ቀን!

Leave a Reply

%d bloggers like this: