Site icon ETHIO12.COM

“አሸባሪው ሃይል በጋራ ክንድ እየተነቀለ ነው” ተመስገን ጥሩነህ

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመሥገን ጥሩነህ አሸባሪውን የትህነግ ቡድን ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ጋር እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሸባሪው ቡድን አፈንግጦ ትግራይ ክልል በመመሸግ የፌዴራልና የክልል መንግሥታትን በመተንኮስ ለማፍረስ ያደረገውን ሙከራ አንስተዋል፡፡ አሸባሪውን ቡድን በአጭር ጊዜ እስከወዲያኛው ለመንቀል የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ ነው።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በማድረስ የከፈተውን ግልጽ ጦርነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ድል ማድረግ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የማወናበድ ተግባሩን ተጠቅሞ ሕዝቡን በማነሳሳት በየቦታው ጥቃትና ወረራ እየፈጸመ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ የሽብር ቡድኑ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ የሽብር ቡድኖችን ለመጠቀም ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡

በተሳሳተ ፖለቲካ የትግራይ ሕዝብን ለጦርነት በመማገድ ጦርነቱን ሕዝባዊ አድርጎታል ያሉት አቶ ተመሥገን ሕዝቡ ከኢትዮጵያውያን ጋር መጋጨት እንደማይፈልግ ቢገልጽም የአንድ ሳምንት ስልጠና በመስጠት በግዳጅ ለጦርነት አሰልፏል ብለዋል፡፡

በትግራይ ክልል ልጅ ያለው ሁሉ ልጁን ወደ ግንባር እንዲልክ እየተገደደ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህንን አሸባሪ ቡድን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ቡድኑን ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለማስወጣት ብቻ ሳይሆን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት መሆኑንም ዳይሬክተር ጀነራሉ አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያውያን የተጠናከረ ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡ የትግራይን ሕዝብ ከሽብር ቡድኑ ነጻ ለማውጣት ጭምር እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

የአማራ ሕዝብ ወረራውን ለመቀልበስ እየተረባረበ ነው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊትም በሙሉ ዝግጅትና ቁርጠኝነት ሕዝቡን ለመጠበቅ እየሠራ ነው፡፡ ሕግ የማስከበር ተግባሩ በፌዴራልና በክልል ሳይታጠር በጋራ የሚሠራ ነው ብለዋል።

በአማራና በአፋር ግንባር የፌዴራል የደኅንነትና የጸጥታ መዋቅር በስፋት ስምሪት መውሰዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ከፍተኛ የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ክልል ልዩ ኀይል፣ አድማ ብተና፣ ፋኖ፣ ሚሊሻ እና የፖለቲካ አመራር ስምሪት መደረጉንም አስገንዝበዋል፡፡

ሠራዊቱ በወልድያና አካባቢዋ ትልቅ ገድል እየፈጸመ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ መከላከያ ሠራዊት ሕዝባዊ ድጋፍ እንዳይኖረው የሽብር ቡድኑ ሐሰተኛ መረጃ እያናፈሰ ይገኛል፡፡

አንዳንድ ጤናማ ያልሆኑ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና በብልሹ አሠራራቸው የተባረሩ ሰዎች ሕዝቡን እያወናበዱት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በነዚህ አካላት ላይ ርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ሕዝብ እንዳይጎዳ እየተዋጋ ያለውን የመከላከያ ሠራዊት ተጋድሎ የአካባቢው ነዋሪዎች በትክክል እንደሚመሰክሩም ጠቅሰዋል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ በእኩይ ድርጊቱ በሕዝብ ትግል ከስልጣን እንደተወገደ ኹሉ በሕዝብ ትግል እንቀብረዋለን፤ ለዚህም ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

ሁሉም አካል ባለው አቅም ከተንቀሳቀሰ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ማጥፋት ይቻላል ብለዋል። ሕዝቡም ይህንን በመገንዘብ ትግሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ተመሥገን የመከላከያ ሠራዊቱን በማዘመን ይበልጥ የማደራጀት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡

Exit mobile version