Site icon ETHIO12.COM

የአፍሪካ ጠላቶች የበሉት አፍሪካዊው ፈርጥ! ቶማስ ሳንካራ!

አፍሪካን ማለቱ፤ ለአህጉራዊ ችግር አህጉራዊ መፍትሄ ማስቀመጡና የአገሬን ችግር ለመፍታት የማንም ተላላኪ መሆን አያስፈልገኝም የሚል ጠንካራ አቋም መያዙ በአፍሪካ ጠላቶች ጥርስ ውስጥ አስገባው እንጂ ሌላ ምንም ወንጀል አልሰራም! ሞተር ብስክሌት ጋላቢነቱ፣ ጊታር ተጫዋችነቱና መለሎና ሸንቃጣ ቁመናው ከመልከ መልካም ገፅታው ጋር ተዳምሮ የብዙዎችን ልብ በቀላሉ የሚያማልል እንደነበር ይነገርለታል። ቶማስ ኢሲዶሬ ኖኤል ሳንካራ። 

ከአለባበስ አስከ አስተሳሰቡ አፍሪካዊ፣ ሸበላና ቆፍጣና ወታደር፣ የአፍሪካ ምድር ለአፍሪካ መፍትሄ አድርጋ ያፈራችው አፍሪካዊ እንቁ፣ የድሃ ቡርኪናፋሶያውያን አባትና ተራማጅ የውጭ ጣልቃ ገብነትንና ተላላኪነትን ህይወቱ አምርራ የምትጠላውና የሚጠየፈው ይህ ታላቅ መሪ አፍሪካን መውደዱ ከወንጀል ተቆጥሮበት በአፍሪካ ጠላቶች ሕይወቱ መቀጠፉ አፍሪካውያን የውጭ ጣልቃ ገብነትን አሻፈረኝ ሲሉና ተላላኪነትን ሳይፈቅዱ ሲቀሩ ምን ሊደረስባቸው እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው። 

ታህሳስ፣ 1949 ዓ.ም በሰሜን አፐር ቮልታ የተወለደው ሳንካራ ሀገሩ ከፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ተላቃ ነፃነቷን ስታገኝ የ12 ዓመት ልጅ ነበር። ወጣቱ የጦር ሻምበል ቶማስ ሳንካራ በ1983 ዓ.ም በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ከያዘ ከጥቂት ጊዜ በኋላ አፐር ቮልታ የሚለውን የሀገሩን መጠሪያ ቡርኪና ፋሶ ወይም “የቀና ሰዎች ሀገር” ሲል ቀየረ። መንግሥቱን ከቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ በግልጽ በማራቅ ተራማጅ ያላቸውን ሶሻሊስት ፖሊሲዎችን አስተዋወቀ። የኪዩባ አብዮት እና የቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት ጄሪ ሮውሊንጊስ አድናቂ የነበረው ሳንካራ ከሙስና የጸዳች እና ከጎረቤት አፍሪቃውያን ሀገራት ጋር አንድ የሆነች ቡርኪና ፋሶን ዕውን ማድረግ ነበር ህልሙ። 

ሳንካራ በስልጣን በቆየባቸው አራት ዓመታት፣ በተለይ ቅድሚያ የሰጠው አላግባብ የሚባክን የመንግሥት ወጪን በመቀነስ እና በጤናና በትምህርት ከቡርኪና ፋሶ ሕዝብ ብዙውን ክፍል የሚሸፍኑትን የገበሬዎችን ህይወት ማሻሻልን ነበር። በዚህም መሰረት በአመራር ዘመኑ በየመንደሮቹ የጤና ጥበቃ ማዕከላት አቋቁሟል፣ በ1984 ዓ.ም በተንቀሳቃሽ የጤና ቡድኖች በሁለት ሳምንት ውስጥ ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጡ ሕፃናት መከተቡም ይታወሳል። በዚያው ዓመትም መሬትን ወደ መንግሥት እጅ ካስገባ በኋላ የግብርናው ምርት ጨምሯል። በ1986 ዓ.ም 35,000 ቡርኪናፋሶዎችን በሶስት ወራት ውስጥ ማንበብና መጻፍ አስተምሯል። ሳንካራ ሀገሩን እና ሕዝቡን ለማገልገል ቆርጦ የተነሳ ተወዳጅ መሪ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ። 

ቶማስ በድሆች፣ ፍትሕ እና መደመጥን በሚፈልጉት ዘንድ ተቀባይነት ነበረው። ምንም እንኳን ድሀ ቢሆኑም በቡርኪና ፋሷዊ ዜግነታቸው ኩራት የሚሰማቸው ሁሉ ቶማስን ይረዱት ነበር። ቶማስን ልዩ የሚያደርገው ለሀገሩና እና ለሕዝቡ የነበረው ክብር እና ፍቅር ነው። ሳንካራ በበሳል አመራር በአንድ በኩል ሕዝቡን የሚቆጣጠሩ የአብዮቱ ተከላካይ ኮሚቴዎችን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትሕ የሚሰጡ የአብዮቱ ሕዝባዊ ችሎቶችን አቋቁሞ እንደነበር ይነገራል። 

ከቀድሞ የሊቢያ መሪ ሞአመር ኧል ጋዳፊ እና ከቀድሞው የጋና ፕሬዚደንት ጄሪ ሮውሊንግስ ጋር የቅርብ ግንኙነት በማድረጉ ከጎረቤት ኮት ዲ ቯር እና ቶጎ ጋር ጠንካራ ልዩነት ውስጥ የገባው ሳንካራ ቡርኪና ፋሶን ብቻ ሳይሆን ሌሎች አፍሪቃውያን ሀገራትን ጭምር ከምዕራቡ ዓለም ጥገኝነት የማላቀቅ ጠንካራ ፍላጎት ነበረው። አውሮጳውያን ቅኝ ገዢዎች በአህጉሩ የፈፀሙትን ብዝበዛ በማመልከት አፍሪቃውያን ሀገራት ከምዕራቡ የተበደሩትን የውጭ ዕዳ መክፈል እንዲያቆሙ ያሳሰበበት ጥሪው የቀድሞዎቹን ቅኝ ገዢዎች ሳያስደነግጥ አልቀረም። አፍሪቃውያን ሀገራት ዕዳቸውን ባይከፍሉ ምዕራባውያኑ እንደማይሞቱ፣ አፍሪቃውያን ግን ይሞታሉ የሚል መከራከሪያ ነበር ያቀረበው። 

ሳንካራ ታማኝነቱና ተራ አኗኗሩ ከብዙዎቹ አቻዎቹ የተለዩ አድርጎታል። ፕሬዚዳንቱ ሁለት ልጆቹን ያስተማረው የሰፊው ሕዝብ ልጆች በሚማሩበት የመንግሥት ትምህርት ቤት ነበር። ባለቤቱም በሀገሪቱ የመጓጓዣ ዘርፍ ውስጥ የነበራቸውን ስራ መቀጠላቸው አይዘነጋም። ከቶማስ ሳንካራ በፊት የነበረው መንግሥት ይጠቀምባቸው የነበሩትን የናጠጡ ተሽከርካሪዎችን ሸጦ ለራሱ አነስተኛ መኪና መጠቀሙና ሚኒስትሮቹም አርአያውን እንዲከተሉ ማድረጉም ይታወሳል። 

የአፍሪቃ ቼ ጉቬራ» ተብሎ የሚደነቀው ሳንካራ ለድሆች የሚቆረቆር፤ እኩልነትን የሚያቀነቅን፤ ቅኝ ገዢዎችን እና ጨቋኞችን አጥብቆ የሚቃወም፤ ሕዝብን ለመብቱ እንዲታገል የሚያነሳሳ ቆፍጣና አብዮተኛ ነበር። 

ሳንካራ ነሐሴ 1983 ሌሎች ጓዶቹን መርቶ የአፐር ቮልታን የመሪነት ሥልጣን ሲቆጣጠር ገና የሰላሳ ዓመት ወጣት ሻምበል ነበረ። «ለመብቱ የማይታገል ሰው ሊታዘንለት አይገባም» ዓይነት ብሒልም ነበረው። «ማመፅ ለማይፈልግ ሰው በሚደርስበት በደል ልናዝንለት አይገባም። አንድ ቀን ነፃ እለቅሃለሁ የሚለውን የጌታውን ከንቱ ተስፋ አምኖ የሚቀበል ሰው ለሚደርስበት ችግር ሁሉ ኃላፊነቱን ራሱ መውሰድ አለበትና ነፃ የሚያወጣው ትግል ብቻ ነው።» ሲልም ያምናል። 

ወጣቱ መሪ ከዘመኑ የቀደመ ነበረ ሲሉ ብዙዎች ይገልጹታል። በድሆቹ መወደዱ፤ በተለይ ማርክሲዝምን ማቀንቀኑንም የቅርብ ወዳጆቹ ብቻ ሳይሆኑ ፓሪስ እና ዋሽግተንን የመሳሰሉ ጠላቶቹም ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። 

ሳንካራ ያኔ የአፍሪቃ እና የአረብን ሕዝብ ለአብዮት ከሚያቀነቅኑት ከኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ ጋር መወዳጀታቸው ደግሞ ጠላቶቻቸውን ለ«ይቺ ባቄላ- -» ዓይነት ሴራ አሳደመ። ሐምሌ 1987 አዲስ አበባ ላይ ተሰይሞ በነበረው የአፍሪቃ አንድነት ድርጅት ጉባኤ ላይ ባደረገው ንግግር የብሬተን ውድስ ተቋማት የሚባሉትን የዓለም ባንክ እና የዓለም ገንዘብ ድርጅትን አወገዘ። ተቋማቱ ብድር እያሉ አፍሪቃን መበዝበዛቸውን አጋለጠ። የሳንካራ ውግዘት እና ማሳጣት ምዕራባውያንን ብቻ ሳይሆን በምዕራባውያን ምንዳና ድጋፍ ሥልጣን በተቆናጠጡ የአፍሪቃ መሪዎች ዘንድ ጥርስ አስነከሰበት። እንደ አብዮተኛ አብረው የቆሙና እንደወታደር የተማማሉ ጓዶቻቸውን ጃስ አሉበትና አስገደሉት። 

ሳንካራ ለቦሊቪያዊው ቼ ጉቬራ በተደረገ መታሰቢያ ስነ ስርዓት ላይ አብዮተኞችን እና ግለሰቦችን መግደል ይቻላል፣ ሀሳብን ግን መግደል አይቻልም ሲል አንድ የኪዩባ ዓብዮት ጦር መኮንን በመጥቀስ ከተናገረ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር የተገደለው። 

ቶማስ ሳንካራ እንደተናገረው ግለሰብን መግደል ይቻላል ሃሳብንና እውነትን መግደል ግን ፈጽሞ አይቻልም። ቶማስ ሳንካራ ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ስላሉና የነብሬተንውድስን የመሳሰሉ ተቋማትንና የምዕራባውያንን ሴራና ተንኮል ስላጋለጡ በአፍሪካ ጠላቶች ሃሳብ አመንጪነት በባንዳ ዜጎቻቸው ህይወታቸው ሊቀጠፍ በቅቷል። 

ዛሬም በኢትዮጵያ የለውጥ አመራር ላይ በስመ ሰብአዊ መብት የሚደረገው ጫናና የጣልቃ ገብነት ሙከራ የአፍሪካውያን ጠላቶች በማነንታቸው በሚኮሩና ቀጣናዊ ትስስርን ማስፈን በሚጥሩ አመራሮች ምን ያህል እንደሚደነግጡና ለማጥፋትና ለማኮላሸት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ልብ ልንለው ይገባል!

በፍቃዱ ከተማ 

አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013

Exit mobile version