“አሻባሪው ህወሃት የአፍሪካ ቀንድን በማተራመስ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ተልዕኮ ለማስፈፀም ሞክሯል”

  • ከፍተኛ ዲፕሎማት ፕሮፌሰር ሻፊቅ ዩሱፍ ኦማር

አሸባሪው ህወሃት የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን በማጋጨት በቀጣናው አለመረጋጋት እንዲኖር ሲሰራ መቆየቱን በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ፕሮፌሰር ሻፊቅ ዩሱፍ ኦማር ተናገሩ።

አንዳንድ ምዕራባውያን በቀዝቃዘቀው ጦርነት ሶቭየት ህብረትን ካፈረሱ በኋላ ወደ አፍሪካ በመዞር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጣልቃ የመግባት ፖሊሲን ሲያራምዱ ቆይተዋል።

ፕሮፌሰር ሻፊቅ ዩሱፍ ኦማር እንዳሉት፥ አንዳንድ ምዕራባውያን በአፍሪካ ጉዳዮች ጣልቃ በመግባት ሀገራትን እስከማፈራረስ ደርሰዋል።

ለአብነትም የሊቢያው መሪ ሞአመር ጋዳፊ አፍሪካን አንድ የማድረግ ንቅናቄን በማራመዳቸው ያልተደሰቱት አንዳንድ ምዕራባውያን በአገራቸው ጉዳይ ጣልቃ ገብተው ጋዳፊን በማስገደል ሀገሪቱን እንዳልነበረች አድርገዋል ነው ያሉት ዲፕሎማቱ።

“ጣልቃ በመግባት የአፍሪካን ስትራቴጂካዊ እቅዶች በተፅጥኖ ስር አስገብተው ተፈፃሚ እንዳይሆኑ አድርገዋል” ሲሉ የአንዳንድ ምዕራባውያንን ድርጊት ኮንነዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ውስጥ አሸባሪ ሃይሎችን በመፍጠር ቀጣናውን ሲያተራምሱ ቆይተዋል ብለዋል።

በነዚህ አካላት ድጋፍ ወደ ስልጣን የመጣው አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ዘመኑ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ለምዕራባውያን አሳልፎ መስጠቱን ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ሲመጡ በህወሃት አገዛዝ የነበረው የጥገኝነት ፖሊሲ እንዲያበቃ እና ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል የማድረግ አሰራር መተግበር መጀመሩ አንዳንድ ምዕራባውያንን አስደንግጧል ይላሉ ሻፊቅ ዩሱፍ።

ይህን ያልወደዱት ምዕራባውያን የራሳቸውን ጥቅም የሚያስፈፅምላቸውን አሸባሪውን ህወሃት ወደ ስልጣን ለማምጣት እንደሚፈልጉና ለዚያም እየሰሩ እንደሚገኙ አክለዋል።

ከዚህም ባሻገር ቀጣናውን ለማዳከምና ባለመረጋጋት ውስጥ ለማስቀጠል በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል ግጭትን ከመፍጠር ጀምሮ በኤርትራ ላይ የማእቀብ ናዳ እንዲወርድባት የአሸባሪው ህወሃት ሚና ቀላል አልነበረም ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራውያን ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠሩ ደግሞ ምዕራባውያንን አስደንግጧቸዋል ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሃት የምዕራባውያንን ተልዕኮ ለማስፈፀም በስልጣን ዘመኑ በሶማሊያ የምርጫ ጉዳይ ጭምር ጣልቃ በመግባት በተላላኪነት አገልገሏል ብለዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን በእነሱ መንገድ ያልተጓዙ ሀገራትን ለማፍረስ እና ለማዳከም ከአልቃኢዳ ጀምሮ አሸባሪ ሃይሎችን የመመስረት እና የመደገፍ ልምድ አላቸው ብለዋል።

በአፍሪካ ቀንድ ያላቸውን ፍላጎት ለማሟላትም ለወኪሎቻቸው አሸባሪው ህወሃትና አልሸባብ ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን አብራርተዋል።

See also  የሱዳን ጦር ሠራዊት የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዳይሾም ምዕራባዊያን አገራት አስጠነቀቁ

አፍሪካውያን ይህንን በአንድነት በቃችሁ ብለው ከተነሱ የምዕራባውያን ስጋት ፈጣሪነት እንደሚያከትምም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply