Site icon ETHIO12.COM

“መውጪያ አጥተው በአራቱም አቅጣጫ ”

ከአፋሩ ግንባር ከጥቂት የመጠራረግ ስራ በቀር ህወሓት እንዳይመለስ ሆኖ ተደቁሷል። ጋይንት ላይ እንደተምች እየተርመሰመሰ ለቀናት ያስቸገረው የህወሀት ጀሌ የዘረፈውንም፣ ይዞ የመጣውንም ትቶ ወደጋሸና አቅጣጫ እየሸሸ ነው። ማምሻውን እንደሰማሁትም ጋሽናን ለቆ፣ በመጣበት መንገድ ወደ ሰሜን አቅጣጫ እየፈረጠጠ ነው። ጥንቃቄ የሚፈልጉና ይፋ ለማድረግ ገና ያልተደራጁ መረጃዎች ስላሉ እንጂ ህወሓት ዘው ብሎ እንደገባው፣ በቀላሉ እንዳይወጣ ሆኖ የተመታባቸው፣ አሁን በመከላከያ ሰራዊቱ እጅ የገቡ ስትራቴጂክ ቦታዎች አሉ።

ምናልባት የአሜሪካው መልዕክተኛ ፊልትማን የኢትዮጵያን መሬት ከመርገጣቸው በፊት ነገሮች ተለውጥው ይዘው የሚመጡትን በትር ወደ ሳምሶናይት ቀይረው ጥሩ ማኪያቶ ጠጥተው ሊመለሱ ይችሉ ይሆናል። ማን ያውቃል? ጠ/ሚር አብይ አህመድ መልእክተኛውን መቀሌ ላይ ተቀብለዋቸው አብረው ጥህሎ ሊበሉም ይችሉ ይሆናል።

ህወሓት ጭንቅ ጥብብ ብሎታል። የሃይል መበታተን ቀውስ ተፈጥሯል። በትላንትናው ዕለት ብቻ 10 በሚሆኑ ግንባሮች ጦርነት ከፍቶ ወገብ ዛላው ተቀንጥሶ ተሸኝቷል። እዚህም እዚያም ሃይሉን ለጥጦ ለመዋጋት የቀየሰው ስልት ዋጋ እያስከፈለው ነው። ህወሓት 6ሚልዮን የትግራይን ህዝብ እንዳለ ቢያሰልፍ እንኳን ሊያሸንፈው የማይቻለውን ጦርነት ነው የጀመረው። እንደዚህ ዓይነት ጦርነት ትንንሽ ጊዜያዊ ድሎችን ሊያስገኝ ይችል ይሆናል። በዘላቂነት አሸናፊ ሊያደርግ ከቶም የሚያስችል አይደለም።

የህወሀት ሃይል ያለውን አቅም አሟጦ ተጠቅሟል። መግፋት የሚችለውን ያህል ገፍቶ ሄዷል። ከእንግዲህ ለጥ ያለ ሜዳ እንኳን ቢገጥመው ወደፊት መሄድ የሚያስችል የሎጀስቲክም ሆነ የሰው አቅም የለውም። እስከአሁን ባደረገው ጫና የኢትዮጵያ መንግስትን አቋም ማስቀየር ካልቻለ ከእንግዲህ ምንም ተአምር ቢፈጠር ያቀደውን ሊያሳካ አይችልም። ባትሪው ደክሟል። ቻርጅ ማድረግ የሚችልበት ምንም እድል የለውም።

የኢትዮጵያ መከለከያ ሰራዊት ለህወሀት የጦርነት ስልት የሚመጥን አሰላለፍ ሲያዋቅር ለሳምንታት ቆይቶ አሁን ወደ እርምጃ ገብቷል። ከአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሺያዎች ጋር በመቀናጀት ካለፈው ሀሙስ ሌሊት ጀምሮ በመከላከል ቁመና ላይ ሆኖ እየወሰደ ባለው ማጥቃት ህወሀትን አፈር ከድሜ እያስጋጠ ነው። መግባቱንስ ገባችሁ፣ እንዴት ልትወጡ ነው? የሚል ጥይቄ ሲነሳ መዳረሻችን አዲስ አበባ ነው ሲሉ ቆዩ። እንግዲህ አሁን መውጪያ አጥተው በአራቱም አቅጣጫ እንደ እህል እየተወቁ ነው።

እንደሰማሁት አሁን በእጃቸው ከሚገኙ ከተሞች ሳይደመሰሱ ለመውጣት ሽምግልና መላክ ጀምረዋል። ሆኖም ግን በቆረጣ ተገብቶ የተያዙ ቦታዎች ላይ የህወሀት ሀይሎች በተበታተነ ሁኔታ በአንስተኛ ሃይል ተሸንሽነው የሞት ሽረት ትንቅንቅ እያደረጉ ነው። ብዙም የሚሳካላችው አይሆንም። ይህንንም እነሱ የተረዱት ይመስላሉ። ከወዲሁ መጠነቋቆልና መወነጃጀል ጀምረዋል። ሽጉጥ ተማዘው እርስ በእርስ ተጠፋፉ የሚል ዜና ልንሰማ የምንችልበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።

የጠሚ/ር አብይ የዛሬው ጽሁፍ በድል ዋዜማ ከመሪ የሚጠበቅ ወሳኝ መልዕክት ነው። መሬት ላይ እየተደረገ ያለው ጦርነት ምን መልክ እንዳለው ከመጠቆም ባሻገር ወኔና ተስፋ የሚሰጥ ድንቅ መልዕክት ነው። በዚህን ወቅት፣ ሀገር የመጨረሻ የህልውና ትግል ውስጥ ስትገባ መሪዎች የሚያተላልፉት መልዕክት ለጠላት ከሚሳየል በላይ የሚያፈረከርክ ይሆናል። ለወገን ሃይል ደግሞ የሞራል ስንቅ፣ የወኔ ምርኩዝ፣ የእልህኝነት ማቀጣጠያ ነዳጅ ሆኖ ያገለግላል። የጠሚ/ር አብይ የዛሬው መልዕክት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊኒስተን ቸርችል ታሪካዊ ተብሎ ዘውትር የሚጠቅስላቸው የመጨረሻው ሰዓት መልዕክትን ያስታውሰናል።

የናዚ ጀርመን ጦር ድባቅ ተመትቶ እንዲፈረጥጥ ያደረገው የእንግሊዝ ጦር በቸርችል ጠንካራና ቀስቃሽ ንግግር ወኔ ተላብሶ፣ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ እንደነበረ ታሪክ ይነግረናል። የጠሚ/ር አብይ የዛሬው መልዕክትም ኢትዮጵያን ለማዳን ለህዝብ የቀረበ ስሜት የሚነካ ነው። በዚህ አጋጣሚ ጠሚ/ር አብይን ለልደታቸው እንኳን አደረስዎት እላለሁ። በዚህ የታሪክ ሁነኛ ምዕራፍ ኢትዮጵያን ለመምራት ተሰይመዋልና እንደጸሎትዎ፣ እንደምኞትዎና ጥረትዎ ኢትዮጵያ መልካም ሆና እንዲያይዋት እኔም እመኝልዎታለሁ።

መሳይ መኮንን

Exit mobile version