Site icon ETHIO12.COM

የጦርነቱ አበሳና ቀጣዩ ስጋት – በሰልባዎቹ አንደበት

የተ.መ.ድ. በመጪዎቹ ሦስት ወራት ቀድሞም የተከሰተ ረሐብ የበለጠ ይበረታባቸዋል የሚል ማስጠንቀቀያ ከሰጣቸው 23 አገራት አንዷ ኢትዮጵያ ነች። በትግራይ ዘጠኝ ወራት የዘለቀውና ወደ አማራ ክልል የተዛመተው ውጊያ ለእርሻ ሥራዎች ማነቆ በመሆኑ ባለሙያዎች ብርቱ ሥጋት አድሮባቸዋል። ውጊያ ባለባቸው አካባቢዎች ገበሬዎች ማሳቸውን ጥለው መሸሽ ጀምረዋል።

ሶስት ልጆቻቸውን ይዘው ትናንት ማክሰኞ በደቡብ ወሎ ዞን በምትገኘው የኮምቦልቻ ከተማ የገቡት የመርሳው ገበሬ አቶ መሐመድ ሁሴን ከአንድ በጎ ፈቃደኛ መኖሪያ ቤት መጠለያ ቢያገኙም ልባቸው አላረፈም። አቶ መሐመድ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ልጆቻቸውን ከሰሜን ወደ ደቡብ ከሚንደረደረው ውጊያ ለማትረፍ መንገድ ሲጀምሩ ልብስ አልያዙም፤ በቂ ገንዘብም በኪሳቸው አይገኝም። የሚከነክናቸው ግን መርሳ የቀሩት የአያታቸው እጣ ፈንታ ነው።

“ከእኔ ጋር የምትኖር አያት አለችኝ። እሷን ትቺያት ነው የመጣሁት። ይዢያት እንዳልመጣ መንቀሳቀስ አትችልም። በመኪና ይዤያት አልመጣ፤ ገንዘብ የለም፤ መኪና የለም። ዝግ ነው መንገዱ። እነዚህን ትናንሽ ልጆች መሸከም ራሱ በግድ ነው” የሚሉት አቶ መሐመድ “አሁን እዚያ በየቤቱ ትልልቅ መንቀሳቀስ የማይችሉ አዛውንቶች አሉ። እኛስ እሺ እነዚህን ልጆች ይዘን አመለጥን። እነዚያ ሰዎች ምንድነው የሚሆኑት?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

አቶ መሐመድ እንደሚሉት ከመኖሪያ ቀያቸው የተፈናቀሉት ሐራ በተባለ አካባቢ በኩል ወደ መርሳ የገቡ የትግራይ ኃይሎች ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው። እንደ አቶ መሐመድ ሁሉ ወልድያ፣ ውርጌሳ እና መርሳን ጨምሮ ውጊያው ከደረሰባቸው አካባቢው ከእርሻ እና ሌሎች ሥራዎቻቸው የተፈናቀሉ በኮምቦልቻ ከተማ በአንድ ግለሰብ ቤት ብቻ ቢያንስ 50 አባወራዎች መጠለላቸውን ዶይቼ ቬለ ለተፈናቃዮቹ መጠጊያ ከሰጡ በጎ አድራጊ ለመረዳት ችሏል።

“ማሽላ ኩትኮታ አለ። ደባላ የምታርምበት አረም አለ፤ ጤፍ አረም አለ። የእኔ የሚኮተኮት ማሽላ አለ። ማሽላው ራሱ ሰው የመደበቅ አቅም ደርሷል” የሚሉት አቶ መሐመድ እንዲህ በነሐሴ ውጊያ ከደጃፋቸው ባይደርስ ኖሮ ሥራ የሚበዛባቸው ባተሌ ገበሬ ነበሩ። በዘንድሮ ክረምት ግን የዘሩትን ማሽላ የሚኮተኩቱበት ዕድል የላቸውም። የተዘራውም ማሳ የውጊያ አውድማ ሆኗል።

“ትናንትና እንዳይሆን ነው ያደረጉት። መሀሉ ላይ ጥይት እየተኮሱ ማሽላው ራሱ ጠፍቷል። እየደረሰ የነበረውን ማሽላ አወደሙት። ምርት ለመስጠት የደረሱ ብዙ ነገሮች አሉ። እነሱ ሁሉ ወደሙ። የጁንታው ቡድን መደበቂያ፣ መሳሪያ መታኮሻ ሆነ። ተደብቆ መሳሪያ ይተኮስበታል፤ ጠቅላላ ማሽላው በመሳሪያ ከመሬት ላይ ጠፋ” እያሉ ተዋጊዎቹ በአካባቢው ከደረሱ በኋላ ደረሰ ያሉትን ጥፋት ዘርዝረዋል።

የትግራይ ኃይሎች ወደ በአማራ ክልል ወደሚገኘው የሰሜን ወሎ ዞን ከተሻገሩ በኋላ ገበሬዎችን ጨምሮ በርካቶች ኮምቦልቻ እና ደሴን ወደመሳሰሉ ከተሞች ሸሽተዋል።

ወደ አማራ ክልል የተስፋፋው ውጊያ የግብርና ሥራዎችን ከማስተጓጎል ባሻገር የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥላውን አጥልቷል። ባሕር ዳር፣ ኮምቦልቻ እና ደሴን  በመሳሰሉ ከተሞች በተወሰነ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ናቸው። የመንግሥት ተቋማትም በቅጡ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም። ከወልድያ በ12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የስሪንቃ የግብርና ምርምር ማዕከል በውጊያው ምክንያት ሥራ አቁሟል።

በማዕከሉ በተባባሪ ተመራማሪነት የሚያገለግሉት አቶ ስዩም አሰፌ እንደሚሉት የአማራ እና የትግራይ ክልሎች የውጊያ ቀጠና ከሆኑ ወር በላይ ሆኗቸዋል። አቶ ስዩም “ቀድሞ ሚያዝያ ላይ የተዘራ ማሽላ አለ። እንደገና ሐምሌ ሲገባም የሚዘራ ማሽላ አለ። ጤፍ ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ እስከ 20ዎቹ ነበር የሚዘራው። ሙሉ በሙሉ ራያም ላይ ጤፍ አልተዘራም። የጁ የሚባለውም አካባቢ አርሶ አደሩ ስላልተረጋጋ መዝራት አልቻለም። የገጠሩም የከተማውም ሰው ነው የፈለሰው። ስለዚህ አምራቹ ኃይል አሁን ምርት ላይ አይደለም ማለት ነው። አሁን አረም አለ፣ ማዳበሪያ መጨመር አለ፣ መኮትኮት አለ። አሁን ከዚያ ውጪ ነው። [ሰብሉ] በአረም ይበላል። ወደ ቆላው አካባቢ ስትሔድ፤ ሐራ እና ወደ ሶዶማ በእንስሳት እርባታ ሰፊ ቁጥር ነው ያላቸው። አሁን ከእነ እንስሳቶቻቸው ሁሉ የተፈናቀሉ አሉ። ስለዚህ አጠቃላይ ግብርናውን በጣም ነው የጎዳው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ሕዳር ላይ ተመርቶ የሚሰበሰበው እህል ሐምሌ እና ነሐሴ በብዛት የሚያልቅበት ነው። ሐምሌ እና ነሐሴ ፈጣን ሰብሎችን ዘርቶ መስከረም ላይ ድራሾት የሚባል ነገር አለ። ቶሎ የሚደርስ ጤፍ፣ አተር፣ ሐምሌ ላይ የሚደርሱ ሰብሎችን አርሶ አደሩ ይጠብቅ ነበር። ስለዚህ የምግብ እጥረቱ አሁን ጀምሮ ነው ያለው። ምክንያቱም አብዛኛው ተፈናቃይ አርሶ አደር ነው። አርሶ አደሩም የከተማውም ነዋሪ ከራያ አካባቢ ወልድያ ተፈናቅሎ መጥቶ ነበር። አሁን ጤፍ አልተዘራም። ወደ ኋላ ከነሐሴ አጋማሽ በኋላ ሽምብራ እና የተለያዩ የጥራጥሬ ሰብሎች የሚዘራበት ወቅት ነበር። አሁን ይኸም ትልቅ ችግር አለ ማለት ነው። በተለይ ምሥራቅ አማራ ዝናብ አጠር ነው። ዘንድሮ ደግሞ ጥሩ አጋጣሚ ነበር። የዝናብ ሁኔታው ቀድሞ ነው የገባው። ሰኔ የመጨረሻዎቹ ሳምንታት ጀምሮ እስካሁን ያለው የዝናብ ሥርጭቱ የተሻለ ነው። ስለዚህ ጥሩ ምርት የሚገኝበት ወቅት ነበረ። ነገር ግን ካሁኑ ጀምሮ ረሐብ ጀምሯል፤ ተፈናቃዮች መጠለያ የላቸውም። የእንስሳት መኖ ችግር ይኖራል። የተፈሉ ችግኞች እንኳ መትከል አልተቻለም።”

ሙሉውን ጀዲ ድብልው ያንብቡ

በጽሁፉ ባይገልጽም ከተጠቀሱት ቦታዎች ውስጥ አሁን የተለቀቁና መንግስት እጅ የገቡ አሉ።

Exit mobile version