Site icon ETHIO12.COM

‹‹በአሸባሪው ህወሓት ተይዘው የነበሩ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን የማጣራት ሥራ እየተሰራ ይገኛል››

– አቶ ረሻድ ከማል የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር

በአሸባሪው ህወሓት ቡድን ተይዘው የነበሩ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን በማጣራት ተመልሰው የአገርን ልማት በሚያግዝ መልኩ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ረሻድ ከማል ገለፁ፡፡

አቶ ረሻድ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ መንግሥት በህወሓት አሸባሪ ቡድን ያላግባብ ተይዘው የነበሩ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን በማጣራት ልማቱን በሚደግፍ ተግባር ላይ ለማዋል እየሰራ ይገኛል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ በሥልጣን ዘመኑ አንድም የልማትና መኖሪያ ቤት እንዳልገነባ የጠቆሙት ኃላፊው፤ ይልቁንም በተለያዩ መንገዶች ሲቀራመታቸው የኖሩ ቤቶች ለሽብር ተግባሩ የገቢ ምንጭነት ሲያውላቸው እንደነበር አመልክተዋል፡፡

የአሸባሪ ቡድኑ ድርጊት አገርን አሳልፎ ለውጭ ጠላት የሚሰጥ ተግባር ነው ያሉት አቶ ረሻድ፤ ድርጊቱ ለአገር ልማትና ለዴሞክራሲ ግንባታ ቆሜያለሁ ሲል ከኖረና የአገርን ፍሬ ከበላ አካል የማይጠበቅ እኩይ ተግባር እንደመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የአገር አንድነት እና ሉዓላዊነት አስጠብቆ ለማቆየት ሁሉም ድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

በዚህም አንድነትን በማጠናከር የአገር ሉዓላዊነትን ለማስደፈር የተሰማሩ የህወሓት አሸባሪ ቡድንን ጨምሮ የአገር አንድነት፣ ልማትና የዴሞክራሲ ግንባታ መሰናክሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ልናስወግዳቸው ይገባል ያሉት አቶ ረሻድ፤ ኢትዮጵያ ሰላም የሰፈነባት፣ የተከበረችና ሉዓላዊት አገር እንድትሆን ለአገር ዳር ድንበር መከበርና የሰላም ዘብ ከሆነው የመከላከያ ሠራዊቱ ጎን በመቆም የተጀመረውን የሕግ ማስከበር ተግባር ከዳር ልናደርሰው ይገባል፤ ይሄም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ግዴታ ነው ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ረሻድ ማብራሪያ፤ ለአገር ሉዓላዊነት መከበር ሕይወቱን እየገበረ ላለው የመከላከያ ሰራዊት በሁሉም ረገድ በመደገፍ አሸባሪውን ቡድን በተቀናጀ ክንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመደምሰስ ወደ ተጀመረው አገራዊ ልማት መዞር ያስፈልጋል፡፡

የተከፈተው ጦርነት በግንባር ብቻ አለመሆኑን እና ይልቁንም በዲፕሎማሲው መስክም የተከፈተ ጦርነት እንዳለ የጠቆሙት አቶ ረሻድ፤ የኑሮ ውድነት በማባባስ ሕዝቡ ተማርሮ በመንግሥት ላይ ጥላቻ እንዲያድርበትና አንድነቱ እንዲሸረሸር በማድረግ ተጽእኖ የማሳደር ሥራዎችም በጥፋት ኃይሎቹ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሕዝቡ እነዚህና መሰል የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ሴራዎችን በመገንዘብ ለአገር አንድነት ዘብ ቆሞ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቡድኑን መደምሰስ ይኖርበታል፡፡ የብጥብጥ፣ የመከፋፈልና የድህነት ምንጭ ሆኖ ለዓመታት አስሮት የነበረውን አሸባሪውን የህወሓት ቡድን በትብብር ማስወገድ አለበት ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አቶ ረሻድ፣ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ይሄን ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር ሁለንተናዊ ድጋፉን እያደረገ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ለጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊት 10 ሚሊዮን ብር እና ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞቹ የአንድ የወር ደመወዛቸውን 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፤ በድምሩ 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ረሻድ ከማል ለኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሎጂ አስረክበዋል።

ሙሳ ሙሀመድ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም

Exit mobile version