ETHIO12.COM

የሸኔን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች አጎራባች ወረዳዎች የሸኔን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 22 ግለሰቦች በቁጥጥርሥር መዋላቸውን የሲዳማ ክልል ሠላምና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቲዮስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ከሽብር ቡድኑ ሸኔ ተልዕኮ በመቀበል በሲዳማና ኦሮሚያ ክልሎች የጸጥታ ችግር ለመፍጠር የሞከሩ ናቸው።

ግለሰቦቹ በጉጂና ሲዳማ ማህበረሰቦች መካከል የጥፋት ተልዕኮ በመቀበል ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አሰረድተዋል።

ከእነዚህ ውስጥ የተሰጣቸውን የመንግስሥት የሥራ ሃላፊነት ወደጎን በመተው አለመረጋጋት እንዲከሰት ሲሰሩ የነበሩ አመራሮች እንደሚገኙበትም አመልክተዋል።

የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመዘንጋት ተኩስ በመክፈት ሁከቱ እንዲባባስ አስተዋጽኦ የነበራቸው ፖሊሶች ጭምር መያዛቸውንም አስታውቀዋል።

ግለሰቦቹ የብሔር ብሔረሰቦች መናገሻ በሆነችው ሀዋሳ የብሄር ግጭት ለማስነሳትና የሻሸመኔ ከተማን ማበጣበጥ ዓላማ አድርገው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር አቶ አለማየሁ ተናግረዋል።

የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሲዳማ ክልሎች ማህበረሰብን ያሳተፈና በተቀናጀ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

ቢሮው በሁሉም ቀበሌዎች ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ በተዋቀረው የማህበረሰብ ፖሊስ አገልግሎት በመታገዝ እየሰራ መሆኑንም አሰታውቀዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ተወካይ ኮሎኔል ግርማ አየለ በበኩላቸው፤ የአሸባሪዎቹ ህወሀትና ሸኔ ቅጥረኞች ሰሞኑን በሲዳማ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ያደረጉትን እንቅስቃሴ መምከኑን ገልጸዋል።

በተለይ በምስራቅ ጉጂ መንገድ የመዝጋትና መሰል ድርጊቶች በመፈጸም አካባቢው የጸጥታ ችግር ያለበት ለማስመሰል የተሞከረ ቢሆንም ሕዝቡና የጸጥታ ሃይሎች በወሰዱት እርምጃ አብዛኛዎቹ መደምሰሳቸውን አስታውቀዋል።

ከአካባቢው የሸሹትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ክትትል በመደረግ ላይ እንደሚገኝም ኮሎኔል ግርማ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ከአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተልዕኮ በመቀበል ሀዋሳና አከባቢውን ለማተራመስና የሽብር ድርጊት ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 37 ግለሰቦች ከአንድ ወር በፊት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ አስታውሷል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version