Site icon ETHIO12.COM

የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት ሀሙስ ስብሰባ ይቀመጣል

በአሜሪካን አጋፋሪነት፣ በእንግሊዝና አየርላንድ አጃቢነት ም/ቤቱ በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲነጋገር አጀንዳ ተይዞለታል። ከወዲሁ በአሜሪካና በአውሮፓ ህብረት በኩል ነጥብ ለማስቆጠር ሩጫው ተጀምሯል።

አሜሪካን በኤርትራ ጀነራል ላይ ማዕቀብ በመጣል የሀሙሱ ስብሰባ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር ጥረቷን ቀጥላለች። ከአውሮፓ ህብረት ጋር በመሆንም የኤርትራ ጦር ወደ ትግራይ እየጎረፈ ነው የሚል ክስ አንጠልጥላ ብቅ ብላለች።

ልሳኖቿ የሆኑትና የምዕራቡን ሀገራት የፖለቲካ አጀንዳ በ’ነጻ ሚዲያ’ ስም የሚያራግቡላት ታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ለሳምንታት ከከረሙበት ዝምታ ወጥተው ያቺኑ የማትቀየር ዜና ቃላትና አረፍተ ነገር እያስተካከሉ ማላዘን ጀምረዋል።

አሜሪካን በጸጥታው ም/ቤት ተስፋ አልቆረጠችም። ከ8 ጊዜያት በላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ የተሰበሰበው ምክር ቤቱ የእነአሜሪካንን ሩጫ ከንቱ ቢያደርገውም ለ9ኛ ጊዜ አንዳች ውጤት ይገኛል ብለው በጀርባና በፊት ለፊት ግፊታቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

የአሜሪካን የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪነት ከምላስ ካራቴ ማለፍ አልቻለም። ፍትህና ርትዕ መጻሀፍት ላይ የቀሩ ጌጦች ሆነዋል። ነጻነት፣ ዲሞክራሲ የህገመንግስት ማጣፈጫ ቃላት እንጂ ከዚያ የዘለለ በመሬት ላይ የሚመነዘሩ ሊሆኑ አልተቻላቸውም።

አሜሪካ በጭፍን ለህወሀት ቡድን እያሳየች ያለችው ድጋፍ ስለብቸኛዋ ልዕለ ሀያል ሀገር ለዘመናት ውስጣችን የታተመውን መልካም እሴቶች ፍቀን እንድናስወጣ እያስገደደን ነው። በፊት እንኳን ከአንጀትም ባይሆን “አሳስቦኛል” የምትል ማስታገሻ መግለጫ እያወጣች ታሞኘን ነበር።

ዘንድሮ ያንንም የለበጣ መግለጫዋን ነፍጋን አይን ያወጣ፣ ይሉኝታ ያጣ ድጋፍ ለህወሀት ማሳየቷ የሚያስገርም፣ የሚያስደነግጥ ነገር ሆኖብኛል። ሰሞኑን የእሷን በልዩ ሁኔታ የተዘጋጀን፣ በብርታት ሰጪ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ ብስኩት እየበሉ የአማራንና የአፋር አከባቢዎችን የወረሩትን የህወሀት ታጣቂዎችን በተመለከተ ኢትዮጵያውያን በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ጉዳዩን አንስተው ሲያንቆራጠጧት ጊዜ የሰጠችው መልስ የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም የሚል መልዕክት ያዘለ ነበር።

ሆነም ቀረም እነአሜሪካን ከሀሙሱ የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የሚጠብቁት ውጤት አይኖርም። እንደተለመደው ቻይናና ሩሲያ አጀንዳውን ገድለው ይቀብሩታል። የአፋር ህጻናት በሕወሀት የጥይት አረር ተቃጥለው ሲያልቁ ትንፋሽዋን ውጣ የተደበቀችው የአሜሪካዋ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ሀሙስ ዕለት በኢትዮጵያና ኤርትራ መንግስታት ላይ የእርግማን ማዓት፣ የማስፈራራያ ናዳ ማውረዷ የሚጠበቅ ቢሆንም የምትለውጠው ነገር እንደሌለ ግልጽ ነው። ኢትዮጵያ ግን ይህን መድረክ እንደከዚህ ቀደሞቹ ተከላካይ ሆና፣ ምላሽ ሰጥታ ብቻ መውጣት የለባትም።

ቢያንስ ከመጨረሻው ስብሰባ ወዲህ የህወሀት ቡድን የፈጸማቸውን መጠነ ሰፊ ጥቃቶች በፎቶግራፍና ቪዲዮ አስደግፋ ለዓለም የምታሳውቅበትን እድል መጠቀም ይገባታል። የአፋር ህጻናት ላይ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ መግለጽ ይኖርባታል። አጋምሳ ወሎ በጅምላ የተገደሉ የአማራ ተወላጆችን ጉዳይ ለጸጥታው ምክር ቤት ማሳወቅ አለባት።

የዓለም ዝምታ፣ የእነአሜሪካን በልዑዋላዊ ሀገር ጣልቃ ገብተው እያደረጉ ያሉትን ሀገር የማፍረስ ተግባር ማጋለጥ ግድ ይላል። በአሜሪካን ብስኩት ከርሳቸውን በሚሞሉ የህወሀት ታጣቂዎች ንጹሃን እየተጨፈጨፉ መሆኑን በመግለጽ የሀሙሱን መድረክ መጠቀም ይገባል የሚል እምነት አለኝ።

በተረፈ የጦር ግንባሮች ወቅታዊ ሁኔታ የህወሀት ጀንበር ለመጥለቅ መቃረቧን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ማንሳት ያስፈልጋል። ህወሓት እየገጠመው ያለውን ሽንፈት ለማድበስበስ በቅርቡ በዳግም ጋብቻ የተጣመረውን ሸኔን በባዶ ፕሮፖጋንዳ እየነፋው ባልተፈጸመ ድል ደጋፊዎቹን እያጃጃላቸው እንደሆነ እየተነገረ ነው።

ሸኔ ከተሞችን ተቆጣጠረ፣ መንገድ ቆረጠ የሚሉ መሬት ላይ ያልተደረጉ፣ በህወሀቶች ጭንቅላት ውስጥ በተፈጠሩ ድሎች የገጠመውን ኪሳራ እንዲሸፍኑለት እየተሟሟተ ይገኛል። ምን ለምን አብረህ አዝግም ዓይነት ጥምረት የፈጠሩት ሁለቱ ጸረ ኢትዮጵያ ሃይሎች የደጋፊዎቻቸውን ተስፋ በባዶ የድል ዜና ለማለምለም ከሰሞኑ በከፍተኛ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ተጠምደው እንዳሉም ሰምተናል።

ጊዜው ሲደርስ አባትና ልጅ፣ ፍቅር እስከመቃብራቸውን ፈጽመው፣ ታሪካቸውን በጥቁር መዝገብ ላይ ትተው እስከወዲያኛው እንደሚሰናበቱን አልጠራጠርም።

መሳይ መኮንን

Exit mobile version