Site icon ETHIO12.COM

የትዳር አጋሮቻቸው በክብር የተሰውባቸው እናቶች

ካሰች ጌታሁን በደቡብ ጎንደር ጋይንት ወረዳ ነፋስ መውጫ ከተማ የቀበሌ 01 ነዋሪ ናት፡፡ በነፋስ መውጫ ከተማ በየዋህነቱና ቅንነቱ የሚታወቀውን ባለቤቷን የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች ነጥቀውባታል፡፡

ባለቤቷ ተመስገን ነጋሽ የሚበል ሲሆን፤ በትዳር ዓለም ከሶስት ዓመት በላይ ቆይተዋል፡፡ የዳሽን ባንክ ነፋስ መውጫ ቅርንጫፍ ጥበቃ የነበረው ባለቤቷ፤ አሸባሪው ወደ አካባቢው ሲገባ ሥራውን አጠናቅቆ ለተረኞች ለማስረከብ ሲጠባበቅ በአሸባሪው ጥቃት ምከንያት ተረኛው ጠባቂ ሳይመጣለት ቀረ፡፡

ወደ ነፋስ መውጫ ሲደርሱ የመጀመሪያውን ጥቃት የሰነዘሩት ዋናው መንገድ ላይ በሚገኘው ዳሽን ባንክ ላይ ነበር፡፡ በጊዜው ሁሉም ሰዎች ከአካባቢው ሲሰወሩ ብቻውን ሆኖ የመከላከል ሥራውን ሰርቷል፡፡

“አደጋ እንዳይደርስብህ ለቅቀህ ውጣ!” ሲባል “ተቋም ትቼ አልወጣም” በማለት፤ አሸባሪውን ፊት ለፊት ገጥሞ መስዋዕት ለመሆን ወሰነ፡፡ አሸባሪው ተቋሙ ላይ ተኩስ ሲከፍትም ፊት ለፊት ገጠማቸው፡፡ ባገኘው አጋጣሚ በአካባቢው ሲያወጋ የነበረውን የጠላት መሪ ጨምሮ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁትን ገድሎ እርሱም መስዋእት መሆኑን ባለቤቱ በስፍራው ለሚገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች ነግራቸዋለች፡፡

የአሸባሪው ታጣቂዎች ቢሳካለቸው ተመስገንን ማርከው ሎሌ ለማድረግ ነበር ምኞታቸው፡፡ ነገር ግን እርሱ ጀግናና ልበ ሙሉ በመሆኑ “ለእናንተ እጄን አልሰጥም” ብሎ ነው ከአሸባሪው ተጣቂዎች ጋር ተፋልሞ የተሰዋው፡፡

የአሸባሪው ታጣቂዎች የመጡት ለዘረፋ ጭምር በመሆኑ አላሳልፍ ሲላቸው ገድለውታል፡፡ ጀግናውን ክብር አሳጥተው እንደ ውሻ መንገድ ላይ ሊቀብሩት ሲሉ ባለቤቱ ደርሳባቸው ብታስጥላቸውም፤
በቀብሩ ጊዜም ነጠላ አዘቅዝቃ እንዳታለቅስና ለለቅሶ የሚገባውን የአገሯን ባህል አንዳትከውን ጭምር ከልክለዋት እንደነበር ባለቤቱ ካሰች ታስታውሳለች፡፡

ተመስገን ህይወቱን የሰዋው ለአገሩ ነው የምትለው ካሰች፤ ሊያጠፉ የመጡትን ታግሎ ከተቋም በፊት ራሱን አስቀድሞ መሰዋቱ ክብር እንደሆነም ትናገራለች፡፡

ሟች በወር አንድ ሺህ ሰባት መቶ ብር እየተከፈለው በሚያገኘው ገቢ ነበር ቤቱን የሚመራው፡፡ ኑሯቸው በኪራይ ቤት ውስጥ ሲሆን ባለቤቱም ሥራ የላትም፡፡

በእርግጥ የተመስገን መሞት ባለቤቱን ቢጎዳም፤ ለአገር ታሪክ ጽፎ አልፏል፡፡ ይህ አሰቃቂ ግድያ እየፈጸመ ማህበረሰቡን የሚያሸብረው ጁንታ ከኢትዮጵያ ምድር እንዲጠፋ ግን ካሰች ተማጽኖዋን አቅርባለች፡፡

አሸባሪው ህይወት ማጥፋት ብቻ ሳይሆን የሥነ ልቦና ጉዳትም አድርሷል የምትለው ካሰች፤ አካባቢው ላይ ገብተው ሴቶችን እንደደፈሩ ገልጻለች፡፡ የተደፈሩ ህጻናትም በደረሰባቸው ሰቆቃ ማንንም ሰው የማየት ሞራል እንደሌላቸውና ያዩትን ሁሉ ጁንታ ነው በማለት ላይ መሆናቸውን ነው የተናገረችው፡፡

“ድንጋጤውና ጾታዊ ጥቃቱ ከቤተ እምነት አስቀርቷቸዋል፡፡ ከጓደኞቻቸው ጋርም አይገናኙም፡፡” ብላለች፡፡

የአሸባሪው ህወሓት ጥቃት ሰላባ የሆነቸው ሌላኛው ግለሰብ ነጻነት ለጋስ፤ በነፋስ መውጫ የአቢሲኒያ ባንክ የጥበቃ ሥራ ላይ የነበረውን የልጇን አባት ክንድዬ ተሰማ የተባለውን ባለቤቷን እንዳጣች ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ገልጻለች፡፡

ባለቤቴን ከሚሰራበት ቦታ አግተው ወስደውታል የምትለው ነጻነት፣ በአሁን ወቅት የት እንዳደረሱት አይታወቅም ስትል ትናገራለች፡፡ የሶስት ዓመት ህጻን ልጃቸው ጠዋት ማታ “አባቴን አሳዪኝ” እያለች እንደምተውተውታትና ከባድ የሞራል ስብራት እንደገጠማት እያነባች ድምጿን አሰምታለች፡፡

“ባለቤቴን ገድለውት ከሆነ ሬሳውን ይስጡኝ፤ በህይወትም ካለ ለህጻኗ ሲሉ ይመልሱልኝ “ስትልም ተማጽናለች፡፡

በአዲሱ ገረመው – (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version