Site icon ETHIO12.COM

የአሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ ጥምር ጥቃት ሰለባዎች ከወለጋ እስከ መርሳ- ደሴ ረጅሙ የሰቆቃ ጉዞ

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ ጸሀይነሽ ካሳው ሶስት ጉልቻ መስርተው መኖር ከጀመሩ ድፍን ሰላሳ ዓመታትን አስቆጥረዋል።

በትዳር ዘመናቸው የሁለት ዓመቷን  ህጻን ኢክራምን ጨምሮ ሶስት ልጆችን አፍርተዋል።

 ዘመናትን ባስቆጠረ ኢትዮጵያዊነት ከኦሮሞ ህዝብ ጋር ወልደው ተዋልደው በጋብቻ ተጋምደው የኖሩ እናት ናቸው። ዛሬ አሸባሪው ህወሃት በፈጠረው መንገድ በማንነታቸው ዛሬ መከራ በዝቶባቸዋል።

ከእለታት አንድ ቀን አንድ አዲስ እንግዳ ክስተት ተፈጠረ፤ ጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በጉሊሶ ወረዳ የዲላጎ ጎላቃዋ ቃራ ቀበሌ የአማራ ማንነት ያላቸው አርሶ አደሮች መላዕከ ሞትን በያዙ እኩይ ታጣቂዎች አስቸኳይና አስገዳጅ ስብሰባ ተጠሩ።

የስብሰባው አጀንዳ ያልተረዱ ምስኪን አርሶ አደሮችም ወንድ ሴት ሳይለዩ ግማሾቹ በጥርጣሬ ገሚሶቹ በመደናገር ለስብሰባ ወደተጠሩበት አዳራሽ ገቡ።

በቅጽበት ነገሮች ሁሉ ተለዋወጡ፤ አብሮ ዘመናትን ካሳለፈው የኦሮሞ ህዝብ በወጡና እኩይ አላማ ባነገቡ የአሸባሪው ሸኔ ታጣቂዎች ከ200 በላይ ንጹሃን አርሶ አደሮች በማንነታቸው በግፍ ተጨፈጨፉ።

ወይዘሮ ጸሀይነሽ ካሳው የሆነውን እንዲህ ያስታውሳሉ “ጥቅምት 22 ቀን ምሽት ለስብሰባ ተጠራን ከስብሰባው እንደገባን በታጠቁ ሰዎች በሩ ተዘጋብን ዛሬ እንገላችኋላን እናንተ እስከዛሬ ኖራችሁ ከዚህ በኋላ ሀብት ንብረት ሳትሉ ወደ ሀገራችሁ ብለውን በመቅጽበት የጥይት ላንቃ ከፈቱብን”።

ከተከፈተው የተኩስ እሩምታ ግማሾቹ ባሉበት ተኙ። ቆመው የነበሩት ደግሞ የጥይት ሲሳይ ሆነው በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ሲያስታውሱ ሲቃ ይተናነቃቸዋል።

“እረ እባካችሁ አትግደሉን እያሉ ሲለምኗቸው የሚለመነው ፈጣሪ ነው” የሚል ምላሽ የሚሰጡት የአሸባሪው ሸኔ ገዳይ ቡድኖች በህይወት የተረፉት በሶስት ደቂቃ ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።

ከሞት የተረፉ መካከል ወይዘሮ ጸሀይነሽ የሁለት ዓመቷ ህጻን ኢክራምን ይዘው በማሽላ ማሳ ውስጥ ተጠልለው እንዲያድሩ ተገደዱ።

አሸባሪው ህወሓትና በአምሳሉ ጠፍጥፎ የሰራው አሸባሪው ሸኔ ርካሽ ጋብቻቸው ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም፤ አሸባሪው ህወሓት ከስልጣን ከተወገደ በኋላ በእኩይ ተግባራቸው የፈጠሩት ጥምረት የጫጉላ ሽርሽር ላይ ያሉ ሙሽሮች አስመስሏቸዋል።

በአሸባሪው የህወሓት የመንፈስ ልጅ አሸባሪው ሸኔ ለዓመታት የገነቡትን በላባቸው ያፈሩትን ሀብት ንብረት ጥለው የሞት ሰለባ ሲሆኑ፤ ከሞት የተረፉት እጅና እግራቸውን ይዘው ወደ አማራ ክልል እንዲሰደዱ ግድ ሆኖባቸዋል።

ወይዘሮ ጸሀይነሽን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ማንነት ያላቸው የወለጋ አርሶ አደሮች በግፍ ተፈናቅለው ለመመጽወት እጃቸውን ወደ መንግስት ዘረጉ፤መዳረሻቸውንም በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ አደረጉ።

የአሸባሪው ሸኔ ማንነት መሰረት ያደረገ ጭፍጨፋ ከፈፀመ በኋላ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በመርሳ ተጠልለው በመንግስት እርዳታ ሲደረግላቸው ቆይቷል።

የስድስት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ አረጋሽ አሊና ወይዘሮ ደመቅ ሁሴንም እንደ ወይዘሮ ጸሀይነሽ ሁሉ ነዋሪነታቸው ወለጋ ቢሆንም “ለ200 ሰው ሁለት መቶ ጥይት አናወጣም” ከሚሉ ጨካኞችና እብሪተኞች ግድያ ተርፈው መርሳ መድረሳቸውን ይገልፃሉ።

በዚያች ክፉ ቀን ተፈናቅለው አማራ ክልል መርሳ የመጠለያ ኑሮን እየገፉ ነበር። ከወለጋ በአሸባሪው ሸኔ ሃብታቸው ተዘርፈው የቀረው ተቃጥሎባቸው ህይወታቸው በተዓምር ያተረፉት እነዚህ ንጹሃን ዜጎች ዛሬም የመከራ ቀንበሩ ከትከሻቸው ላይ አልወረደላቸውም።

ሁሉም ነገር በህይወት ከመኖር በታች ነው ብለው የደረሰባቸውን ግፍ ችለው በመርሳ መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ እናቶችና ህጻናት ሌላ መፈናቀል ገጥሟቸዋል።

የአሸባሪ ሸኔ የመንፈስ አባት አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ ክልል ሰርጎ በመግባት ህፃናትን ጨምሮ ንጹሃንን ገድሏል፣ ሴቶችን ደፍሯል፣ ሀብት ንብረት ዘርፎ ወደ ትግራይ ወስዷል፤ ማጓጓዝ ያልቻለውን አውድሟል። የአሸባሪው ህወሓትና ሸኔ ጥምረት እነ ጸሀይነሽን ለሁለተኛ ጊዜ ህጻናትን ይዘው እንዲፈናቀሉ አስገድዷቸዋል።

ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ አማራ ክልል መርሳ ከዚያም ወደ ሀይቅ እና ደሴ መሰደድ የህይወት እጣ ፋንታቸው ሆኖባቸው “ፍርድ ከፈጣሪ” ይጠባበቃሉ።

የሞቀ ቤትና የሞላ ንብረት የነበራቸው እነዚህ እናቶችና ህጻናት ማንንና ምን እንደበደሉ ሳያውቁት በአሸባሪው ህወሓት የሀሰት ትርክት መከራ ያያሉ።

ለጥፋት ሲሆን ተፈላልገው የማይተጣጡት አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በዜጎች ላይ ያደረሱት ግፍ የከፋ መሆኑን አንደበታቸው ይመሰክራል።

ከአሸባሪው ሸኔ አሰቃቂ ግድያ የተረፉት ተፈናቃዮች ህይወትን ለማዳን ህጻናትን ይዞ ከአንድ መጠለያ ጣቢያ ወደ ሌላ መጠለያ ጣቢያ መባዘን ተስፋ እንዳስቆረጣቸው ይናገራሉ።

Via ENA

Exit mobile version