Site icon ETHIO12.COM

አሸባሪው ትህነግ አገር እያጠፋ ነው፤ ሰባት ሺህ ትምህርት ቤቶች አውድሟል፤ አፋር ክልል መልሶ ማጥቃት አወጀ

 አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት ምክንያት 7 ሺህ ያህል ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ። ይህ የተገለፀው ሀገር አቀፍ የአጠቃላይ ትምህርት ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

የትምርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ አሸባሪው ቡድን በትግራይ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ተማሪዎችንና ከ48 ሺህ በላይ መምህራንን ከትምህርት ስርዓት ውጭ አድርጓል ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈም ተማሪዎችን ወደ ጦርነት እየማገደ መሆኑንም ተናግረዋል።

አሸባሪው ቡድን ግጭቶችን ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በማስፋፋት ትምህርት ቤቶችን አውድሟል። ባለፈው አንድ ወር ብቻ በአፋር ክልል 88 ሺህ ተማሪዎች ይማሩበት የነበሩትን 455 ትምህርት ቤቶች በአሸባሪው ቡድን መውደማቸውን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ደግሞ 140 ትምህርት ቤቶችና ሁለት የመምህራን ኮሌጆች ሙሉ በሙሉና በከፊል መውደማቸውን አስረድተዋል። በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎችና የውጭ አጋር ድርጅቶችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው ሽብርተኛው ህወሓት ተማሪዎችን ለውትድርና በመመልመል ከፍተኛ አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ነው የገለጹት።

አፈ ጉባኤው ቡድኑ በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ የከፈተውን ጥቃት በማያዳግም መልኩ በመፍታ አካባቢዎቹን በአጭር ጊዜ ወደልማት ማስገባት ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የትምህርት ዘርፉን የማዘመንና የማሳደግ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም የ2013 አመት ምህረት የትምህርት ዘርፍ አፈጻጸምና የቀጣይ ትኩረት አቅጣጫዎች መቅረባቸውን ሃላፊዎችን ጠቅሶ የዘገበው ፋና ነው።

በሌላ ዜና የአፋር ክልል ምክር ቤት የአሸባሪው ህወሓትን ወረራ ለመቀልበስ የተጀመረው መልሶ ማጥቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ወሰነ። ህወሓት የፈፀመውን ወረራ የመቀልበስና የሽብር ቡድኑን የመደምሰስ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአፋር ክልል ምክር ቤት መውሰኑን የክልሉን ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ጠቅሶ ኢቢሲ ዘገበ።

ምክር ቤቱ 6ኛ የስራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ባለበት በአሁኑ ሰዓት አሸባሪው ህወሓት በአፋር ህዝብ ላይ የፈፀመውን ወረራና የዘር ማጥፋት ለመቀልበስ ብሎም የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ በህዝቡ፣ በሚሊሻውና በልዩ ሀይሉ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች አበረታች እንደሆኑ በጉባኤው ላይ ተገልጿል፡፡

ቡድኑ ተነቅሎ እስኪጠፋ እርምጃው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የአፋር ክልል ሕዝብ፣ ሚሊሻ፣ ልዩ ሃይልና መለከላከያ ወረራውን በመቀልበስ በትህነግ ሃይል ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሳቸውና በርካታ መሳሪያና ተዋጊዎችን መማረካቸው በተደጋጋሚ መገለጹ ይታወሳል።

Exit mobile version