Site icon ETHIO12.COM

በዋጋ ንረት ማባባስ ከ14 ሺህ 600 በላይ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ- 85 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የዋጋ ንረት በማባባስ የኑሮ ውድነት እንዲፈጠር ባደረጉ 14 ሺህ 662 የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱን የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።

ተቋማቱ ላይ እርምጃው የተወሰደው ሀገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ በመጠቀም ሰው ሠራሽ የኑሮ ውድነት በመፍጠር ሀገሪቱን ለመዝረፍ ያሰቡ ሰዎችን ለማስቆም በተደረገ ጥረት መሆኑን የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዴንጌ ቦሩ ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ንግድ ቢሮ የኅብረተሰቡን ኑሮ አለመረጋጋት ውስጥ ያስገባውን የዋጋ ንረት ለመቆጣጠር እና መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ በምርቶች ላይ የሚደረገውን የዋጋ ጭማሪ ለማስቆም እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥቷል።

እንደ ኦቢኤን ዘገባ፣ እስካሁን 166 ሰዎች ላይ ክስ መመሥረቱን እና 14 ሰዎች ከ6 ወር እስከ 2 ዓመት በሚደርስ እስራት እንዲቀጡ መደረጉን አቶ ዴንጌ ተናግረዋል።

የኢኮኖሚ አሻጥርን መፍጠር አሸባሪው ቡድን በሀገር ላይ እየፈፀመ ካለው ጦርነት ያልተናነሰ በመሆኑ ምርቶችን በሚደብቁ፣ ፋብሪካዎችን በሚያዳክሙ፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሚያደናቅፉ እና የዋጋ ንረትን በሚፈጥሩ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በበዓላት ወቅት ግብይት የሚጨምር በመሆኑ ኅብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ መጪውን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ የግብርና እና የፋብሪካ ምርቶች ኤግዚቢሽን እና ባዛር በክልል ደረጃ መዘጋጀቱን የቢሮው ኃላፊ አቶ ዴንጌ ቦሩ ገልጸዋል።

በአሶሳ ከተማ የጸጥታ ችግር ለመፍጠር ተንቀሳቅሰዋል በሚል የተጠረጠሩ 85 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ


በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ የጸጥታ ችግር ለመፍጠር በመንቀሳቀስ የተጠረጠሩ 85 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ፡፡ የከተማው ወጣቶች ፀረ-ሰላም ሃይሎች ጥፋት እንዳያደርሱ ተደራጅተው ሠላም እያስጠበቁ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

የአሶሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተጠርጣሪዎቹ የከተማውን የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ የተጣለውን የሰዓት እላፊ ገደብ ጥሰው ሲንቀሳቀሱ በመገኘታቸው ተይዘዋል።

ተጠርጣሪዎቹ የተያዙት በአገር መከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ፣ በክልሉ ልዩ ሃይልና በነዋሪዎች የተቀናጀ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል አማካኝነት መሆኑን የገለጹት ኮማንደር ቡሽራ፤ ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የአሸባሪው ህወሓት ርዝራዦች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የ53ቱ የባንክ ሂሳብ፣ ተሸከርካሪዎችና ሌሎች ንብረቶች በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መታገዳቸውን ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪዎቹን ለሕግ ለማቅረብ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ኮማንደር ቡሽራ አስታውቀዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ሰላምና ጸጥታን ለማናጋት የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በአንድነት እየታገለ መሆኑን ተናግረዋል።

EBC NEWS

Exit mobile version