Site icon ETHIO12.COM

የፌዴራል አቃቤ ህግ በአቶ ደመላሽ አድማሱ ታምር በሁለት ጉዳዳዮች ላይ ክስ መሰረተ

የፌዴራል አቃቤ ህግ በአቶ ደመላሽ አድማሱ ታምር ላይ በዛሬው እለት ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የሙስና ወንጀሎች ችሎትሁለት ክሶችን መስርቷል፡፡

የዐቃቤህግ 1ኛ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 23 /2/ሀ/ እና /3/ ስር የተመለከውን ድንጋጌ በመተላለፍ፤ የሌላውን ሰው ጥቅም ለመጉዳት ወይም ለራሱ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ በ23/11/20013 ዓ/ም ከጠዋቱ 1፡20 አካባቢ ሲሆን በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ክልል ልዩ ቦታው ቦሌ ቡልቡላ መስጊድ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ጀጁ አስመጪ ቡልቡላ አንሷር መስጊድ ግቢ ውስጥ አከማችቶት የነበረውን እና ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ህገ-ወጥ ነው ተብሎ በመንግስት ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገበት የቡልቡላ ፖሊስ ጣቢያ የሚጠብቀውን ክብደቱ 1‚500 (አንድ ሺ አምስት መቶ) ቶን የዋጋ ግምቱ ደግሞ 147‚472‚946.75 (አንድ መቶ አርባ ሰባት ሚሊዮን አራት መቶ ሰባ ሁለት ሺ ዘጠኝ መቶ አርባ ስድስት ብር ከ ሰባአምስት ሳንቲም) የሆነን ብረት ገዝቸዋለሁ በማለት ከተከማቸበት ግቢ ለማውጣት እንዲያመቸው በብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ያልተፃፈና ከብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት ያልተሰጠ ሀሰተኛ የፈቃድ ደብዳቤ ለቡልቡላ ፖሊስ ጣቢያ በማቅረብ ብረቱን በመኪና እያስጫነ እያለ የተያዘ በመሆኑ በፈፀመው በሀሰተኛ መንግስታዊ ሰነድ መገልገል የሙስና ወንጀል ተከሷል።

የዐቃቤ ሕግ 2ኛ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሽ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀፅ 25/1/ እና /4/ ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ አንድ የመንግስት ሰራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በስራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን እንዲያደርግ ለማድረግ ከላይ በ1ኛ ክስ ላይ የተጠቀሰውን እና ህገ-ወጥ ነው ተብሎ በቡልቡላ ፖሊስ ጣቢያ ጥበቃ እየተደረገለት ያለውን እና የራሱ ያልሆነውን ብረት ገዝቸዋለሁ በማለት ከተከማቸበት ቦታ አውጥቶ ለመውሰድ እንዲያመቸው የፖሊስ ጣቢያው አዛዥ ለሆነው 2ኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር ንብረቱን የሚጠብቁትን የፖሊስ አባሎች እንዲነሱ ታደርግልኛለህ በማለት በሁለተኛ የዐቃቤ ህግ ምስክር ስም በአቢሲንያ ባንክ በተከፈተ የሂሳብ ቁጥር በ22/11/2013 ዓ/ም 500‚000 (አምስት መቶ ሺ ብር) ገቢ ያደረገ በመሆኑ በፈፀመው ጉቦ የመስጠት የሙስና ወንጀል ተከሷል።
ዐቃቤ ህግም ክሱን ያጠናክሩልኛል ያላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን ያቀረበ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ለጳጉሜ ሁለት ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Exit mobile version