Site icon ETHIO12.COM

ሐኑን!

ልጅነቷን ቦርቃ ካደገችበት፤ አፍላነቷን ፈንድቃ ከጎመራችበት፤ በድብብቆሽ ትኩስ፣ የሚፋጅ የመጀመሪያ ፍቅርን ካጣጣመችበት መኖሪያ ቤት የገዛ እህት ወንድሞቿ አስወጥተው ሜዳ ላይ ሲወረውሯት መጠጊያ ዘመድም ሆነ ቤተሰብ አልነበራትም። በርሃ ላይ ለብቻዋ እንደበቀለች ዛፍ ብቸኛ ነች። መሄጃ የላትም። ቢጨንቃት፣ ቢጠባት አብራት ከተማረችው የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ቤተሰብ ጋር በፈጣጣው ሄደች። ግን የግድ ቋሚ ማረፊያ ያስፈልጋታል። ስታወጣ፣ ስታወርድ ከአንድ ስምና ስልክ ቁጥር በስተቀር አዕምሮዋ ማሰብ ያቆመ ይመስል ሌላ አማራጭ ጠብ ሊልላት አልቻለም። ምርጫ አልነበራትም። ደወለች። ይጠራል። ፍርሃት ሰውነቷን አርዶ ልቧ በሃይለኛ መምታቱን ቀጥሏል።
ደው…ድው…ድው…!
መቼ ነበር ልቧ እንደ አሁኑ ተንጦ የሚያውቀው።
አዎ… አስታወሰች።
የዛን ዕለት…

•••

ከዕለታት በአንዱ ቀን ሰውነቱ ቀጠን ያለ መልኩ ጠይም ወጣት ቤታቸው መጣ። ለሐገሩ እንግዳ፣ ቀድሞ የተያዘለት አዲስ ቤት ተከራይ እንደሆነ ተርድታለች። አስተውላው አይኗን ሰበረች። ቆንጆ ነው። ከውስጧ የደስታ ምንጮች ሲንፎለፎሉ ተሰማት።

ወጣቱ መልከ-መልካም ቤታቸውን ተከራይተው አገልግሎት የሚሰጠው ባንክ ስራ አስኪያጅ እንደሆነና እና ስሙም አብራሃም እንደሚባል ተረዳች። በምሳ ሰአት አባቷ በረንዳ ላይ ጫት መቃማቸው፣ እሷም ከአጠገባቸው ሆና ቡና፣ ሻይ ማፍላት፣ መከደም የተለመደ ሕይወታቸው ነበር። አብራሃም ምሳ ለመብላት ሲመጣ “ቡና ውሰጂለት” መባሏ ለመተዋወቅና ለመግባባት በር ከፈተላት። አባቷ በሌሉ ጊዜ ያለ ቡና መለስ ቀለስ ማለት ጀመረች።

ድንገት አንድ ዕለት ጆሮዋን ለማመን እስክትጠራጠር ድረስ አብራሃም እሷን ማግባት እንደሚፈልግ ያበስራታል። አስቡት እንደሚወዳት አይደለም፣ ሚስቱ እንድትሆን ነው የጠየቃት። የሆነ ነገር ሰውነቷን ውርር አደረጋት። በጣም ደስ አላት። ፈገግታ፣ በፈገግታ ሆነች። እንደ እሳት የሚፋጅ የአኩኩሉ ፍቅራቸውን አሀዱ አሉ። አባት አግራቸው ወጣ ከማለቱ ዘላ የአብራሃም ቤት። አባት ሰላት እየሰገዱም ሆነ ስልክ እያወሩ ዘላ ፍሬን ያስለቀቃት ቤት። መጨዋወት… መቀላለድ… መላፋት… ሲቀጥል ደግሞ መሳሳም የሰርክ ስንቋ ሆኑ።

እያለ፣ እያለ ተጓዘና አንድ ማለዳ የአባቷን እግር መውጣት ጠብቃ ገና ያልነቃው የአብርሃም አልጋ ውስጥ ተገኘች። ሌሊቱን ሲጥል ያደረው ከባድ የዝናብ ጎርፍ በሁለቱ አዲስ ፍቅረኞች መኻልም እስከዛሬ ሲከማች የነበረው የስሜት ደመና ነገሮችን ከመሳሳም እርከን እንዲሻገሩ ሁኔታውን አመቻቸ። ልቧ በፍጥነት ድው፣ ደው ሲትል በአፏ ለማምለጥ የምትፍጨረጨር ትመስል ነበር። ውስጧ የሚንተከተክ እሳተ ጎመራ ያለ ይመስል ሰውነቷን ላብ አጠመቃት። በጣምም ፈራች።

ደው…ድው…ደው…!

በሕይወቷ ፈፅሞ ሊደበዝዝ የማይችል የትዝታ ሰበዝ፣ ምስለ-ሕሊና ታትሞ ቀረ። ሕመም ያረበበት ደስ የሚል ስቃይ። ያልሰከነ ጣፋጭ የስሜት ማዕበል። ሁለት አካሎች፣ ሁለት ነፍሶች ሊገልፁት በማይቹሉት ኃይል እንደ አንድ የሚወሃዱበት። እያነቡ መደሰት፣ እያቃሰቱ መሐሴት፣ እየጮኹ መርካት። እናም ሐኑን ለመውደዷ እና ለማፍቀሯ ምልክት እንዲሆን ለአብራሃም የሕይወቷን ውድ ቅርስ ሴትነቷን አሳልፋ ሰጠችው።

አብራሃም ባይተዋርነቱ ለቆት ቤተኛም ሆነ። ቤታቸው ወጣ ገባ ማለት ጀመረ። ቡና መምጣቱ ቀርቶ ጎራ እያለ መጠጣት፣ ከአባቷ ጋር ጨዋታ ማውጋት ልማድ አደረጉት። አባቷም በጣም ወደዱት። በጣም አመኑት። እንቁ ልጃቸውንም ምን ያህል ዋጋ እንደከፈሉባት እና እንደሚሳሱላት አጫወቱት።

•••

የሐኑን አባት ድሬዳዋ ውስጥ አለ የሚባል የናጠጠ ሐብታም ነው። ዱንያ ሞልታ የፈሰሰችለት። ከሐኑን በላይ ከሌላ እናት የተወለዱ ስምንት ልጆችን አፍርቷል። ለቤት ሰራተኝነት ብላ ቤታቸው ከገባችው እናቷ ሐኑን ሲወልዱ የሞቀው ትዳርና ቤተሰብ ለመለያየት በቃ። ጠቅልለው እናቷ ጋር ከተሙ። የበፊት ሚስታቸው እንዲሁም ጤና አልነበራቸውም፣ ይሄን ሲሰሙ ሆስፒታል ገቡ። ሕመማቸው ተባብሶ ሕይወታቸው ሊያልፍ ቻለ።

የአባቷ ልጆች እህት ወንድሞቿ የእናታቸው ገዳይ የቤተሰባቸው ሳንካ አድርገው እንደጠላት አቄሙባት። እንደደመኛም ቆጥረው ለመጉዳት ማሰባቸውም አልቀረም። በዚህ ምክንያት ሐኑን ምንም በማያገባትና በማታውቀው ዳፋ ትምህርቷን አቋርጣ ቤት ተቀመጠች። ከአባቷ ጋር ካልሆነ በስተቀር ወደ ውጭ ከማንም ጋር እንድትወጣ የሚፈቅዱላት አይደሉም። አብርሃም እምነት ተጣለበት። ገበያ ስትሄድ ወይም ወደ ውጭ ስትወጣ የአጃቢነቱን ይሁንታ አገኘ።

•••

ሐኑን የፍቅርን ደስታ ገና ማጣጣም እንደጀመረች ክው፣ ድርቅ የሚያደርግ መርዶ ሰማች። አብርሃም የሚሰራበት ባንክ ቤት መልሶ ወደ አዲስ አበባ አዘዋወረው። እንዳይሄድ ተማፀነችው፣ ለመነችው። ቢበዛ በሁለት ወራት ውስጥ ተመልሶ መጥቶ አግብቷት ይዟት እንደሚሄድ ቃል ገብቶላት ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ።

ሐኑን በየቀኑ በስልክ ብታገኘውም ናፍቆቱና ፍቅሩ እያደር ፀናባት። ሁሌም ምንም የማይገባትን በጣም ስራ እንደበዛበት ነው የሚናዘዝላት። በሁለት ወራት ውስጥ ለመመለስ ቃል የገባው ሰውዬ ሶስት ወራት እንደዋዛ አለፉት። ቀናቶቹ እንዳይደርሱ የለም፣ ደረሱና በመጨረሻ መጣ።

በቀጣዩ ቀን አመሻሽ ላይ ከአባቷ ጋር ሳሎን ተቀምጠው አንድ ሶስት፣ አራት እንግዶች ቤታቸው መጡ። ሐኑን ለሽምግልና የተላኩ እንደሆኑ ስላወቀች ወደ ጓዳ ገብታ ጆሮዋን አስልታ ማድመጥ ጀመረች። የሚባባሉትን፣ የሚመላለሱትን ንግግር ይሰማታል። ድንገት ግን መኻል አናቷን የተመታች ይመስል አንገዳገዳት፣ ብዥ አለባት። ጋብቻ ጠያቂው አብራሃም መሆኑን አባቷ ሲሰሙ በሐይማኖታቸው ልዩነት አሻፈረኝ አሉ። እሺ እንዲሉ ዱአ ያዘች። ግን አባቷ ቢባሉ፣ ቢሰሩ በእምቢታቸው ስለፀኑ ሽማግሌዎቹም በመጡበት አግራቸው ምስስ ብለው ሄዱ።

ጣፋጭ ፍቅርን እንደ እናቲቱ ወፍ በአፏ ያቀመሳት የምትወደው፣ የምትንሰፈሰፍለት የልቧ ንጉስ ምሽቱን ስልክ ደውሎ “ይዤሽ ልጥፋ” ቢላት አሻፈረኝ አለችው። አባቷ ከሷ በስተቀር ማንም እንደሌለውና እንደዛ ከባድ መሰዋዕትነት ከፍሎላት ድጋፍ በሚያስፈልገው ሰአት ልትከዳው እንደማትችል፣ ከሆነ ግን ፀፀቱ እረፍት እንደማይሰጣት እና እርግማኑም እንደሚከተላት ልቧ ተሰብሮ እያዘነች ነግራው ቢችል እንዲረሳት አሳሰበችው።

ሐኑን በሁለት አፅናፎች መሃል ስትዋልል እንቅልፍ በአይኗ ሳይኳል ለሊቱ ተዳርሶ ብርሐን በቀኑ ለመሳም እየተንደረደረ መሆኑን የወፎች ዜማ አበሰረ።

ሕይወት ትቀጥላለች። ጊዜም አይቆምም ይጓዛል። ከፊቷ ፈገግታ የማይጠፋው ሐኑን ዝም አለች። ቁዝም፣ እዝን። አሰልቺ ቀናቶች፣ ድግግሞሽ ዕለታት፣ አዝጋሚ ሰአታት፣ ደባሪ ሌሊቶች…! ጨው አልባ ሕይወት ሆኑባት። ግን ለአባቷ ምንም ክፉ ፊት አታሳያቸውም። በጣም ትጠነቀቃለች። እንደነበረችው መሆኗን ለማሳየት ትጥራለች። በውዴታ ሳይሆን በግዴታ ስለሆነ ግን አጨንቁሮ ላስተዋላት ያስታውቅባታል።

አብርሃምን መርሳት እንደሚገባት አመነች። እንደ ባልቴት በስራ ተወጠረች፣ ስልኳን ዘጋች። ትዝታ የሚባለውን የማይጨበጥ መንፈስ ብሎክ ቋት ውስጥ አስገብታ ከረቸመችበት። እንክብካቤዋን እና ፍቅሯን ለአባቷ አደረገች። በመጠኑም ቢሆን የተሻሻለች መሰለች።

ቀናቶች ኮበለሉ። የድሮው አለፈ፣ አዲስ ነገር መጣ። አባቷ ታመሙ። ፀናባቸው። ቀን ሳታርፍ፣ ለሊት ሳታንቀላፋ ተንከባከበቻቸው። ሆስፒታል ደግመው ደጋግመው ቢሳለሙም ሊሻላቸው ቀርቶ ባሰባቸው። አባቷ በህመማቸው ላይ ሆነውም ሀሳብና ጭንቀታቸው መጠጊያ ለሌላት ልጃቸው ነበር። እሳቸው ከሌሉ ወንድሞቿ በሕይወት ካስተረፏት ያለምንም ቤሳቤስቲን ሜዳ ላይ እንደሚጥሏት ያውቃሉ። እኔ ከሞትኩ እንዴት ትሆናለች ብለው ሐሳብ ገባቸው። ማረፊያ ለሌላት አንዲት ልጃቸው በጣም አዘኑላት፣ ተከዙላት። ጋሻና መከታ የሚሆናትን ጋብቻ መከልከሌ ስህተት ነበር ወይ ብለው ሊፀፅታቸው ልባቸውን ኮረኮረው። አይ በዲናችን (ሐይማኖት) መሠረት ከጀሃነም እሳት ነው የታደኳት ብለው ሐሴት ሊያደርጉም ዳዳቸው። ከመሃል ቤት ሆነው ግን ከአንዱ ዛፍ ሳይጠለሉ ነፍሳቸው ባከነች።

በመጨረሻ ውዷ ልጃቸው በሕልም ተመስላ በጆሮዋቸው አንድ ነገር ስታንሾካሽክላቸው እንደ ክር የሰለለ ድምፅ ይሰማቸዋል። አብርሃምን ከልቧ እንደምታፈቅረው እና እሱን ፍለጋ እንደምትሄድ ከሚያንገላታቸው ሕመም ጋር እየታገለሉ በከፊል ተረድተዋታል። አልተቃወሙም። የቅያሜ ፊትም አልተነበባቸውም። እንዲችው በዝምታ ስሜት አልባ ፊታቸው እንደታቀፉ እስከወዲያቸው አንቀላፉ።

•••

“ሄለው!”
ይላል ሊሞሸር የሳምንታት ዕድሜ የቀሩት ከወዲያኛው ጫፍ በኩል ያለው የአብርሃም ድምፅ። ድምፁ ባይመልሳት ኖሮ ሐኑን ጭልጥ ብላ በትዝታ ጋሪ ነጉዳ ነበር።
እንደ ሕልም፣ እንደሰመመን…

አባቷ እንደሞቱና ወንድሞቿ ከቤት እንዳስወጧት፣ ምንም መውደቂያ እንደሌላት፣ ቢጨንቃት እሱ ጋር እንደደወለች አንድም ሳታስቀር ልቅም አድርጋ አጫወተችው።

ከዛስ ምን ይፈጠር ይሆን???
የተቀረውን ከመጻሕፉ…

ቸር_ጊዜ – አንተነህ ዘ ሠላም

“ከዕለታት ግማሽ ቀን፣ ሐኑን” በአሌክስ አብርሐም https://t.me/Bookshelf13

Exit mobile version