Site icon ETHIO12.COM

መከላከያ ሙሉ ማጥቃት ጀመረ- ትህነግ “ያለ ቅድመ ሁኔታ አደራድሩኝ” እያለ ነው

ከግንባር የሚሰማው መረጃ እረፍት ይነሳል። በትግራይ ዜጎች እጅግ ለከፋ ረሃብ እየተጋለጡ መሆኑና በረሃብ የሞቱ ስለመኖራቸው እየተገለጸ ነው። ምክንያቱ ለትግራይ ተወላጆችም ግራ ያጋባው የአማራ ክልልና የአፋር ክልል ወረራን ተከትሎ የተፈጠረው ሰብአዊ፣ ቁሳዊና ታሪካዊ ሃብት ውድመት ፣ እንዲሁም መፈናቀል ያስከተለው ጣጣ ቢዘረዝሩት የሚያልቅ አልሆነም። መጨረሻው ባይታወቅም ለዚህም ይመስላል መንግስት ጦርነቱን እልባት ለመስጠት የመጨረሻ ደውል መደወሉን ያበሰረው።

ኢትዮ12 ከሁለት ሳምንት በፊት ጀነራል ጻድቃን ” በቃን” ሲሉ ወታደራዊ ዘመቻው ቆሞ እርቅ መጀመር እንዳለበት ማሳሰባቸውን ከዛ ቀደም ባለው ሳምንት ደግሞ የትህነግ አመራር የቆላ ተምቤንን ምሽግ ዋና ቢሮው ለማድረግ መውሰኑንን የድርጅቱን የአሜሪካ ወኪሎች ዋቢ ያደረጉ የመረጃ ምንጮችን ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል።

ዛሬ መከላከያ ሚኒስቴው በሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አማካይነት ይፋ እንዳደረገው የጸረ ማጥቃት እርምጃው ተጠናክሮ ቀጥሏል። ሰራዊቱ ወደፊት እየገሰገሰ ነው። ሃላፊው “የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊታችን ፣ የጀመረውን ሽብርተኛውን ጠራርጎ የመደምሰስ ማጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል” ሲሉ አስታውቀው የሚወሰደውን እርምጃና ውጤት በየቀኑ ለሕዝብ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።

በትናትናው ዕለት የሙት፣ ቁስለኛና ምርኮ ይፋ ያደረጉት ሌተናል ጀነራል ባጫ ” ቀጣትይን የድል ብስራት አከታትለን እናስታውቃለን” ሲሉ ጥቃቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ምልክት ሰጥተው ነበር።

በተመሳሳይ ቀን ሁርሶ የመድበኛ ውትድርና ስልጠና የጨረሱ ተመራቂዎች ፊት ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ” አሸባሪ ሆኖ ተፈጠሮ፣ አሸባሪ ሆኖ አገር መርቶ፣ አሸባሪ ሆኖ የሚሞት” ሲሉ የገለጹትን የትህነግ ሃይል በእንቅርት መስለው በዘዴና በብልጠት እንደሚነቀል አመልክተው ነበር።

ዛሬ ማለዳውን የመከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው “አሸባሪው ህወሃት የመንግስትን የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔን እና ለትግራይ ህዝብ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ አሻፈረኝ በማለት በአማራና አፋር ክልል ወረራ በመፈፀም እጅግ ዘግናኝ ግፎችን ሲፈፅም ቆይቷል”

የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ “የመከላከያ ሰራዊታችን እስትራቴጂክ ቦታዎችን ይዞ በመከላከል ቁመና ራሱን ለቀጣይ ግዳጅ ሲያዘጋጅ ቆይቷል። አሁን ላይ ከመከላከል ቁመና ወደ ፀረ-ማጥቃት በመሸጋገር ሽብርተኛው ወረራ ከፈፀመባቸው ቦታዎች ሁሉ ጠራርጎ ለማውጣትና ለመደምሰስ ጀግናው ሠራዊታችን ማጥቃት ጀምሯል” ሲሉ በይፋ አስታውቀዋል።

“በዚህ ፀረ-ማጥቃት ፣ በአሸባሪው የህወሃት ኃይል ላይ የሚወሰደውን እርምጃ በየቀኑ እየተከታተልን ዘገባዎችን/ዜናዎችን የምናስተላልፍ መሆኑን ለመላ ህዝባችን ማብሰር እንወዳለን” ሲሉ ኮሎኔሉ ተናግረዋል። “ኢትዮጵያ በልጆቿ መሰዋትነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች” ሲሉም ሙሉ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ማጥቃት መጀመሩን ይፋ ከማስታወቅ ውጭ ሌላ ዝርዝር ባይገለጽም አሁን ላይ ከግንባር የሚሰማው ዜና መከላከያ መቀለን ለመቆጣጠር በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ነው። የጦሩ የተለያዩ አመራሮች ለመንግስት ሚዲያ እያስታወቁ ያለው አንድ ሃቅ ቢኖር የትህነግ ሃይል ተከቦ ክፉኛ እየተመታ መሆኑንን ነው። ከዚህም በላይ የትህነግ ሰራዊት ሳይታሰብ በድንገት አማራና አፋር ክልል ዘለቆ በወረረበት ወቅት ፈጸመው የተባለውና በሚዲያዎች ይፋ የሆነው ተጋባሩ ሕዝብን ከዳር እዳር በማስቆጣቱ በረገጠው ቦታ ሁሉ የህዝብ ክንድ እያረፈበት ነው።

” ጠላት እየተንደረደረ እጃችን ገባ” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንደተናገሩት፣ የአማራ ክልል መሪና የዞን አስተዳደሮች ደጋግመው እንዳሉት የትህነግ ሃይል በወረራ ከያዝቸው ቦታዎች ሲወጣ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት አርሶ አደሮች ምስክር ሆነዋል።

የኢትዮ12 የአዲስ አበባ ተባባሪ የኤምባሲ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳለው ትህነግ በግንባር መሸነፉን በማረጋገጣቸው የእርቅ መድረክ ለማዘጋጀት ለመንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብም፣ ዋናዎቹን እስከሚይዙ ድረስ እየተለሳለሱ ማስቸገራቸውን አመልክተዋል።

ትህነግ ከሃምሳ በላይ አገራትን፣ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መደራደር እንደሚፈልግ ጠቅሶ ተማጽኖ ማቅረቡ ይፋ በሆነበት በአሁኑ ሰዓት፣ በተመሳሳይ በረሃብ የሞቱ ወገኖች መኖራቸው እየተሰማ ነው። ትህነግ በረሃብ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን በተደጋጋሚ እያስታወቀ፣ ጎን ለጎን ድርድር እየተየቀ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ለሰሞኑ ጥያቄ መልስ ባይሰጥም በግርድፉ አፈር እየላሰ የሚነሳውን ትህነግን አምኖ ለመደራደር እንደሚችግረው አስታውቋል። ጭራሹኑም ከአሸባሪ ጋር ድርድር ብሎ ነገር እንደማይኖር ነው ያስታወቀው።

ከመንግስት ወገን አስተማማኝ የህዝብ ድጋፍ፣ የደጀን ጎርፍ፣ የስንቅና ትጥቅ፣ የክተተ ጥሪ የተቀበሉ ዜጎች ብዛት ሰፊ በመሆኗና ጦር፣ ሚሊሻው፣ ልዩ ሃይሉ እንዲሁም ወጣቱ በጋለ ስሜት በመነሳቱ ነጻ የወጡትን ቦታዎች ለአካባቢ ሚሊሻና ፖሊስ እየሰጠ መከላከያ ሙሉ ትግራይን በቀናት ውስጥ እንደሚቆጣጠር ተሰምቷል።

ትህነግ በሁለት ሳምንት ውስጥ አዲስ አበባን እንደሚቆጣጠር በተደጋጋሚ እያስታወቀ በጀመረው ግስጋሴ መግፋት አለመቻሉ ሳይሆን ከያዝቸው ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ለቆ መውጣቱን፣ ከፈተኛ የሰው ሃይል ጉዳት እንዳጋተመው መገለጹን አስመልክቶ ይፋዊ መግለጫ አልሰጠም። ይሁን እንጂ ” ለሰላም ስል ተኩስ አቆማለሁ” ብሏል።ድርድር እንደሚፈልግ አስታውቋል። ቅድመ ሁኔታ የሚባል ነገር እንደማያቀርብም አመልክቷል። ለዚህም ይመስላል የአፍሪካ ሕብረት ትህነግን አሸባሪ ያለው ፓርላማ እንዲያነሳለት ጥያቄ አቅርቧል።

መስከረም 24 ቀን አዲስ መንግስት እንደሚመሰረት ይፋ ሲደረግ አቶ ጌታቸው ረዳ እዛ እንደማይደረስ በሽሙጥ በፌስ ቡካቸው ላይ አስፍረው ነበር። ” ደሴ ናፈቀችኝ” ሲሉም ግጥምም ደርድረው ነበር። ከደሴ የሚሰማው ዜና ህዝቡ አካባቢውን ለመጠበቅ እያደረገ ስላለው ዝግጅትና ወኔ የምስጋና መሆኑ በግንባሩ ምን እየሆነ እንደሆነ አመላካች ሆኗል። በዋግ ሙሉ በሙሉ የትህነግ ሃይል ተመቶ መውጣቱን አዋጊ መኮንኖቹ መናገራቸውና ማጥቃቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ዛሬ መከላከያ በይፋ ጥቃት መጀመሩን ከማወጁ በፊት ኮረምና ማይጨው ተቆርጠው መከላከያ እጅ መግባታቸውን አሶሲየትድ ፕሬስ ዘግቦ ነበር። በዚህ መነሻ የመንግስት ሃይል ያለበት ቦታና መቀለ መካከል አንድ ከተማና አንድ አነስተኛ መንደር ብቻ ነው ያለው።

ሁሉም ሆኖ እርቅና ሰላም ቢቀድም የሚሉ ወገኖች አሁንም ቢሆን ወደ ድርድር መመለስ አስፈላጊ መሆኑንን ያምናሉ። ድርድሩ ግን በየትኛውም ወገን ወንጀል የሰሩና ሕጻናትን ያስጨፈጨፉ፣ መከላከያን ያረዱትን ወደ ህግ ማቅረብን ለአፍታም የሚዘነጋ ሊሆን አይገባውም።

Exit mobile version