ETHIO12.COM

ሠላም ለማምጣት የሚደረግ ድርድር ፍኖተ ካርታ በግርማ ሰይፉ ማሩዕይታ!

ሠላም እና እርቅ ምንድን ናቸው? ሠላም እና እርቅ በአገራችን ለማምጣት የሚደረጉ ድርድሮች እንዴት መሆን ይኖርባቸዋል? በሠላምና እርቅ ዙሪያ ለዓለም ለተከሰቱ ግጭቶች መፍትሔ ሲሰጡ የነበሩ ልሂቃን ኢትዮጵያ እንዳላት እሙን ነው፡፡ አርቅ ሠላምና የማህበረሰብ ግጭቶች አፈታት በተመለከተ እንደ ፕሮፌስር ሕዝቂያስ አስፋ የመሰሉ ምሁራን አሉን፡፡

የሠላምና እርቅ ትርጉሞች እና መንገዶች የሚል መፅኃፍም አበርክተውልናል፡፡ ድርድር በየትም የሠላም ማስፈን እሣቤ ውስጥ ወንጀልን ለመደበቅ፤ ወንጀለኞችን ለማስመለጥ ወይም ከወንጀላቸው ለማንፃት የሚደረግ መድረክ አይደለም፡፡ ሠላምን ለማምጣት የሚደረግ ድርድር ፍትሕን ወደጎን አደርጎ ጎልበተኛን ማባባያ መድረክ አይደለም፡፡

አሁን አገራችን ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አገራዊ ዕርቅ በማድረግ ሠላም ማምጣት፤ የዜጎችን ሞትና እንግልት ማሰቆም የቅድሚያ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ቢሆንም፤ ይህ የሚሆነው ግን በአገር ሉዓላዊነት ላይ እየቆመሩ፤ ፍትሕን በመጨፍለቅ ወንጀለኞችን በማባባል የሚሆንበት አንደም ምክንያት ሊኖር አይገባም፡፡


ድርድር ያስፈልጋል የሚሉና የሠላም ደቀመዝሙር ካልሆንን የሚሉ አጅግ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይሁን እንጂ አንዳቸውም ሠላም ለማምጣት የሚደረግ ድርድር የሚካሄድበትን ትክክለኛ ፍኖተ ካርታ ሳይሰጡን፤ ሠላም የሚመጣው በድፍኑ በድርድር ነው ይሉናል፡፡

ሠላም እና ድርድር የሚሉ አማላይ ቃላትን በመጠቀም ብቻ ሠላም አይመጣም፡፡ ይልቁንም እብሪተኞችን ወደ ሠላም መድረክ እንዲመጡ የሚመኩበትን ሀይል ለማጥፋት/ለማዳከም ሲሉ ምትክ የሌለውን የሕይወት ዋጋ የሚከፍሉ በወሣኝ ግንባሮች ላይ የሚገኙ የአገር መከላከያ ሠራዊት ዋጋ የሚያሳንስ ይመስለኛል፡፡ ይህ ፅሁፍ ዓላማው በምንም መመዘኛ በሀቅ ለሠላምና ድርድር የሚፈልጉ አካላትን ለማንኳሰስ ወይም ለመንቀፍ አይደለም፡፡ ይልቁንም የሚሉትን ሠላም ማምጫ የድርድር “ፍኖተ ካርታ” እንዲያቀርቡ ለመገፋፋት ተግባራዊ ፈተና ለማቅረብ ነው፡፡
የውጭ ሀይሎች በአገራችን ኢትዮጵያ ሠላም እንዲመጣ ፍላጎት አለን ብለው ጣልቃ ለመግባት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ በእርግጥ የእኛ ሠላም መሆን ያሳስባቸዋል? ብሎ መጠየቅ አይከፋም፡፡ በዓለማችን እብሪተኞች ሳይንበረከኩ ሠላም የተገኘበት አንድ ምሣሌ ሊሰጡን አይችሉም፡፡ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በአስራ አንድ ሰዓት፤ በአስራ አንደኛው ቀን በዓመቱ አስራ አንደኛ ወር የጀርመን እብሪተኛ ለሠላም እጅ የሰጠው በጉልበት ነው፡፡ ዛሬ እኛን ሠላም በጦርነት አይገኝም፤ የምትለን አሜሪካ በመጨረሻው ሠዓት በዚህ ጦርነት ውስጥ ወሣኝ ሚና ነበራት፡፡ ዛሬም ዳቦ እያሳዩ ክብራችንን ሊወስዱ የሚፈልጉ የውጭ ሀይሎች ሠላም ሊያመጡልን አይችሉም፡፡ ይህን አውቀን መንቀሳቀስ ይኖርብናል፡፡
ኢትዮጵያዊ የሆነ ሠላም እንዲመጣ የሚደረግ ድርድር አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ድርድር የሚካሄድበት አውድ ምን የሚመስል ነው? ብሎ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በአገራችን ትህነግ/ህወሓት ባለፉት 30 ዓመት ያደረገውን ነገር ሁሉ ትተን፤ ከጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ወዲህ ያሉትን ብቻ ብንመለከት የሚከተሉትን ወሳኝ ኩነቶች እናገኛለን፡፡
• ትሕነግ በጥቅምት 24 2013 በሰሜን ዕዝ ላይ “መብረቃዊ” ያለውን ጥቃት ፈፅሞ ዋናውን አገራዊ ተቋም በሰው ሀይልም በቁስም በማውደም በዓለም ታሪክ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል፤
• በማይካድራ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በመፈፀም በሺዎች የሚቆጠሮ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፉ ሲሆን፤ ይህን ድርጊት የፈፀሙት “ሳምሪ” በመባል የሚታወቅ ትህነግ ያደራጀው የወጣት ሀይል መሆኑ ተረጋግጧል፡፡
• በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጠረውን ሕገወጥ ድርጊት ለመቀልበስ በተደረገው ዘመቻ፤ በትግራይ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር አድርጓል፤
• ከሰኔ 22 2013 ጀምሮ መንግሥት በተናጥል በወሰደው የተኩስ አቁም ተከትሎ እራሱን መልሶ ለማደራጀት እድል ያገኘው የትሕነግ/ህወሓት ሀይል ወደ አማራና አፋር ክልል ወረራ በማካሄድ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰ ሲሆን፤ በአፋር 107 ሕፃናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ በመጠላይ ውስጥ ያሉ ሲቪሎችን በማጥቃት ወንጀል ፈፅመሟል፡፡
• በትግራይ የሚገኙ ጊዚያዊ መንግሥቱን ደግፈዋል ያሉዋቸውን ተጋሮዎች ያለምንም የፍርድ ሂደት ረሸነዋል፡፡
• በወረራ በተቆጣጠሩት የአማራና አፋር ክልል አካባቢ እንስሳትን በጥይት እየደበደቡ ገድለዋል፤ የሲቪል መኖሪያዎችን እና የጤና ተቋማትን አውድመዋል፡፡
• የክልል ሀይል ሊታጠቅ ከሚገባው በላይ (በሕገ መንግሥት ድንጋጌ ውጪ) በመታጠቅ የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ ድርጊቶችን በተደጋጋሚ ፈፅሟል እየፈጸመም ይገኛል፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩትን የአገር ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የጣለ፤ የዜጎችን ስብዓዊ መብት የጣሰ ከፍተኛ የአገር ሀብት ያወደመ የወንጀል ተግባር ከፈፀመ ሀይል ጋር ድርድር እንዴት መቀመጥ ይኖርብናል? ብሎ ማስብ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ልክ ነው፤ አገራችን ኢትዮጵያ ሠላም ትሻለች፤ የሠላም ትሩፋት ዜጎች እንዲቋደሱ መሥራት የሁሉም ሠላም ወዳድ አካላት ርብርብ ይፈልጋል፡፡ ሠላምን ለማምጣት ግን “አንተም ተው፤ አንተም ተው!!” በሚል ባህላዊ መንገድ መሞከር ብዙ ርቀት የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ማንኛውም ለሠላም ድርድር እራሱን ያጨ አካል ከላይ የተነሱትን ሁኔታዎች በቅጡ በማስተዋል፤ ወንጀለኛውን መለየትና ተጠያቂ ማድረግ የግድ የሚል ይሆናል፡፡ ይህን አለማድረግ አገሩን ሊጠብቅ በቀበሮ ጉድጓድ እና በካምፕ የነበረን ሠራዊት በድቅድቅ ጨለማ በአንድ ጊዜ ከመቶ በላይ ቦታዎች ላይ ጭፍጨፋ አካሂዶ “መብረቃዊ” ያለውን ጥቃት እውቅና መስጠት እና ቤተሰቦቻቸውን እንደሌሉ መቁጠር ነው፡፡ በሌላ ጊዜም ተመሳሳይ ድርጊቶችን ከማበረታታቱም በላይ ውንብድናን እንደመሸለም ነው፡፡ በአፋር የተጨፈጨፉ ሕፃናት በትግራይ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች፤ በማይካድራ በማንነታቸው ተለይተው የተጨፈጨፉ ዜጎችን ምንም አይድለም ቻሉት ብሎ እንደማላጋጥ ነው፡፡ ወንጀል መሸፈን እና ወንጀለኞችን ነፃ ማውጣት ነው፡፡
በእኔ እምነት በኢትዮጵያ የሚደረግ ሠላም ለማምጣት የሚደረግ ድርድር ሊያሟላቸው የሚገባ መሰረታዊያን የሚከተሉት መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

  1. የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና ኢትዮጵያዊነት በማያንኳስስ ሁኔታ መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህን ለማንኳሰስ የሚደረጉ መቧደኖቹን የፌዴራሊስት ሀይል ወይም ሌላ ተመሳሳይ ስብስብን ሊቀበል አይገባም፡፡
  2. ወንጀለኞችን በጥፋተኝነት ተጠያቂ የሚያደርግ እና ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎችና ቤተሰቦች ተገቢውን እውቅና እና ካሣ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡
  3. ተጎጆዎችን ያሳተፈ የይቅርታና አርቅ መድረክ በተከታይነት ሊኖረው ይገባል፡፡
  4. ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በምንም ሁኔታ በፕሮፓጋንዳ የሚታጀቡ፤ ፍትህን የሚያዛቡ እና ዘላቂ ሠላም እንዳይመጣ ጥላቻ የሚዘራባቸው ሊሆኑ አይገባም፡፡
    እነዚህን መሠረታዊያን ከግምት በማስገባት የሠላም እና እርቅ ለማካሄድ የሚደረጉ ድርድሮች የሚከተሉትን ተግባራት ማከናወን ይኖርበታል፡፡
  5. የትሕነግ አመራሮች በዋና ተዋናይነት ክስ የተመሰረተባቸው ጥፋታቸው መጠን በሂደት በመረጃ የሚጣራ ሆኖ ከላይ ለተፈጠሩት ወንጀሎች በተጠያቂነት እጃቸውን ለመንግሥት እንዲሰጡ፤ ትህነግ እና የትህነግ አርማ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ አገልግሎት ላይ እንዳይውል ማገድ፡፡
  6. ከዋና አመራር ሰጪነት ውጪ ያሉ የትሕነግ/ህወሓት አመራሮች እና አባላት ምዕረት ተደርጎላቸው በአካባቢያቸው የፈፀሙት ወንጀል ካለ በአካባቢ ደረጃ በሚፈጥር የሠላምና እርቅ ጉባዔ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ፤
  7. እጃቸውን የሚሰጡ አመራሮች በገለልተኛ አካላት ክትትል የሚደረግበት ምቹ የማረፊያ ቦታ እንዲዘጋጅላቸው እና የፍርድ ሂደታቸውን ያለምንም ተፅዕኖ እንዲከታተሉና እንዲከላከሉ እድል የሚፈጥር እንዲሆን ማድረግ፤ማስረጃ ያልተገኘባቸው በአፋጣኝ ነፃ እንዲሆኑ ማድረግ፤
  8. የፍርድ ሂደቱ በማንኛውም መመዘኛ ገለልተኛ እንዲሆን አስፈላጊ ከሆነ እና ተከሳሹች ከፈለጉ ገለልተኛ አካላት የሚታዘቡት እንዲሆን ማድረግ፤
  9. የጥፋተኝነት ውሳኔ እና ፍርድ ሲሰጥ የሞት ፍርድ የሚሆን ከሆነ መንግሥት፤ የቅጣት ማቅለያዎችን በማድረግ ለሠላም እና ለጥፋተኞችም የመፀፀቻ እድል የሚሰጥበትን እድል እንዲያመቻች ማድረግ፤
  10. መንግሥት የደረሱትን ጥፋቶችን ያለምንም ማጋነን፤ በትክክል እንዲሰንድ እና ለሕዝብ ይፋ መማሪያ እንዲሆን በጥቅምት 24 ለተጨፈጨፉ የመከላከያ ሀይል አባላትን እርሱን ተከትሎ ለተከሰቱት ውድመቶች መታሰቢያ በሚቋቋም የሠላም ማዕከል ውስጥ እንዲኖር ማድረግ፤ አና
  11. በትግራይ ክልል በአስቸኳይ ምርጫ ተካሂዶ፤ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስኪመሰረት ጊዚያዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም፤ ክልሉን ከማንኛውም የጦር መሣሪያና ታጣቂዎች እንቅስቃሴ ነፃ በማድረግ ሠላም ማስፈን፡፡
    በእኔ እምነት ወንጀለኞችን ለመበቀል ያላለመ፤ ተጠያቂነት የሚያሰፈን ለአገራቸው ሕይወታቸውን ለመስጠት ለተሰለፉ የሠራዊት አባላት መስዋዕትነት ክብር የሚሰጥ ፍኖተ ካርታ ይመስለኛል፡፡ የተሻለ የምትሉት ፍኖተ ካርታ ካላችሁ ጀባ በሉን፡፡ እንወያይበት እናዳብረው፡፡
    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
    ቸር ይግጠመን
    ግርማ ሰይፉ ማሩ
Exit mobile version