Site icon ETHIO12.COM

በወሎ ግንባር የትህነግ አዋጊ ጀነራል መገደላቸው ተሰማ ፣ 358 የአሸባሪው ታጣቂዎች ተያዙ

በወሎ ግንባር የአሸባሪዉ ትህነግ ቡድን አዋጊ ጄኔራልን ጨምሮ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላቱ መደምሰሳቸውን፣ እንዲሁም 358 የአሸባሪው ሕወሓት ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰይድ መሀመድ አመልክተዋል። ቡድኑ በጎኃ ንጽሃንን መጨፍጨፉም ታውቋል። በወሎ ግንባር የተሰለፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት በአሸባሪውና ወራሪዉ የትህነግ ቡድን ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሳቸው ተገለጸ። ቪኦኤ አማርኛ ከትናት በስቲያ ትህነግ ወደፊት እየገሰገሰ ነው ሲል አቅጣቻውን ሳይገልጽ ሪፖርት መስራቱ ይታወሳል።

በአማራ ሕዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም ንጹሃንን እየገደለ፣ ንብረት እየዘረፈና መሰረተ ልማት እያወደመ ያለዉን የሽብር ቡድን ለማፈራረስና ከነአካቴዉ ለመቅበር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በየአቅጣጫዉ እየተፋለሙት ይገኛሉ፡፡ የመላዉ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ጠላት የሆነዉን የትህነግ የሽብር ቡድን ለማፈራረስና ለመቅበር በቁርጠኝነት እየተሠራ መሆኑን በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰሜን ፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክቶሬት ምክትል አዛዥ ኮማንደር ምትኩ ዳባን ጠቅሶ አማራ ማስሚዲያ ኮርፖሬሽን አስታውቋል።



በወሎ ግንባር የተሰለፉ የፌዴራል ፖሊስ አባላት አሸባሪውንና ወራሪውን ቡድን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡት መሆኑን ኮማንደር ምትኩ አስረድተዋል፡፡ አሽባሪዉ የትህነግ ቡድን በደረሰበት አካባቢ ጥፋት ፈጽሟል ያሉት ኮማንደር ምትኩ፣ ቡድኑ በወረባቦ ወረዳ ጎሃ በተባለች አነስተኛ ከተማ ንብረት መዝረፉን እና ማውደሙን ነግረውናል፡፡ አሸባሪ ቡድኑ በከተማዋ ንጹሃንን በግፍ መግደሉንም ገልጸዋል፡፡

በጎኃ አካባቢ በተደረገ ዉጊያ የአሸባሪዉ ትህነግ ቡድን አዋጊ ጄኔራልን ጨምሮ በርካታ የሽብር ቡድኑ አባላት መገደላቸዉንም ነው ያረጋገጡት፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የሰሜን ዳይሬክቶሬት ዲቪዥን አራት ፈጥኖ ደራሽ ሻለቃ ምክትል አዛዥ ኢንስፔክተር ሀሰን አብዱ በበኩላቸው ወራሪዉ ቡድን ወደ አፋር ክልል እና ደቡብ ወሎ ዞን ሰርጎ ለመግባት ቢሞክርም የወገን ኀይል ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸዉን ቦታዎች በመያዝ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስበት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ከአማራ ሚሊሻ እና ከፋኖ ጋር በመቀናጀት አኩሪ ድል እያስመዘገበ መሆኑንም አዛዦቹ አስታውቀዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስ ሀገርን ከመፍረስ ለመታደግና ወራሪ ቡድኑን አሳዶ ለመደምሰስ እና መስዋእትነት ለመክፈል ከመቸውም ጊዜ በተሻለ ዝግጁ መሆናቸዉን ኮማንደር ምትኩን የገለጸው ዘገባ ያስረዳል።

በተመሳሳይ ዜና በደቡብ ወሎ ዞን 358 የአሸባሪው ሕወሓት ሰርጎ ገብ ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ። የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ሰይድ መሀመድ በዞኑ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚህም የሕወሓት አሸባሪ ቡድን አባላት በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ሰርገው በመግባት ጥፋት ለመፈፀም ያደረጉት ጥረት በአካባቢው ማኅበረሰብ ንቃት ከሽፏል ብለዋል። በተለይም ወጣቶች አካባቢያቸውን ሌት ተቀን በንቃት በመጠበቃቸው 358 የሽብር ቡድኑ ሰርጎ ገቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ነው የገለፁት።

አሸባሪው ሕወሓት በተለይም “የአማራን ሕዝብ እረፍት እነሳለሁ ኢትዮጵያንም አፈርሳለሁ” ብሎ ተነስቷል ሲሉ ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው በዓሉን ሽፋን አድርጎ ሽብር ለመፍጠር እየሞከረ በመሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል። በመሆኑም የዞኑ ሕዝብ በዓሉን ሲያከብር ሰላሙን በመጠበቅ “ፀጉረ ልውጦችን” በንቃት መከታተል አለበት ነው ያሉት።

የሽብር ቡድኑ የግለሰብ፣ የሕዝብና የመንግሥት ተቋማትን ዘርፎ ለመውሰድ በአካባቢው 400 በላይ ተሽከርካሪዎችን አሰማርቶ እንደነበርም ጠቅሰዋል። የሽብር ቡድኑን አረመኔነት የተረዳው የወሎ ወጣት፣ ሚሊሻው እንዲሁም አርሶ አደሩ ከሌሎች የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን መፋለማቸውን ተናግረዋል።100 ብር ለወገኔ በሚል የድጋፍ ማሰባሰቢያ በዞኑ ለአገር ኅልውና ዘመቻው ከ151 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሃብት በዓይነትና በገንዘብ መሰበሰቡንም አክለዋል ሲል ዋልታ አመልክቷል።

Exit mobile version