“ወደ ጦር ግንባር አልሄድም፣ ትምህርት እፈልጋለሁ ብሎ መቅረት በአሸባሪው ህወሓት ያስገድላል”

የድል ዜናየካራ ቆሪ አርጡማ መገንጠያን ተከትሎ ወደ ሰንበቴ የመጣ የጠላት ሃይል አዋይቱ ፍልውሃ ላይ አብዛኛው ተደምስሶ 80 በላይ ተማርኳል ቀሪውንም እያሳደደው ይገኛል።

የ16 ዓመቷ ታዳጊ ዳናዊት ፍጹም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነበረች፤ ይሁንና በአሸባሪው ህወሓት አስገዳጅነት ትምህርቷን አቋርጣ በታጣቂነት ተመልምላ በጦርነት ውስጥ ገብታለች።

“ወደ ጦር ግንባር አልሄድም፣ ትምህርት እፈልጋለሁ ብሎ መቅረት ያስገድላል” የምትለው ታዳጊዋ፤ “ተገደን በዘመትንበት ውጊያ እጄን ለመከላከያ ሠራዊት ሰጥቻለሁ” ብላለች።

የሽብር ቡድኑ ህወሓት እንደ ታዳጊ ዳናዊት ያሉ ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናትን በጦርነት በመማገድ ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀል እየፈጸመ መሆኑ ይፋ ከሆነ ውሎ አድሯል።

የሽብር ቡድኑ በአማራና በአፋር ክልሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ህፃናትን አሰልፎ ወደ ጦርነት እሳት በመማገድ የጥይት ማብረጃ አድርጓቸዋል።

በወሎ ግንባር በርካታ የአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎቹ የተደመሰሱ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ እጃቸውን ለመከላከያ ሠራዊት ሰጥተዋል። የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የተመለመሉት በፍላጎታቸው ሳይሆን ተገደው እንደሆነ ነው ተናግረዋል።

እንደ ታዳጊ ዳናዊት ተገዶ ወደ ጦር ግንባር መምጣቱን የሚናገረው የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ምርኮኛ ብስራት ሃጎስ “አሸባሪው ህወሓት ረሃብን የጥፋት ተልዕኮውን ለማሳካት ለሚሰለፉ ታጣቂዎች መመልመያ አድርጎታል” ብሏል።

ከተፈናቃዮች መጠለያ ውስጥ ተገዶ መመልመሉን የገለጸው ብስራት “መዝመት ወይንም በረሃብ መሞት” የሚል ምርጫ እንደሚቀርብላቸው ተናግሯል።

እርዳታ ተከልክሎ ለረሃብ እንደሚዳረግ በማመን “ረሃብ ከሚገድለኝ እየተዋጋሁ ብሞት ይሻለኛል ብዬ ወጥቻለሁ” ያለው ብስራት፤ “እኔ ዕድለኛ ሆኜ እጄን ለመከላከያ ሠራዊት ሰጥቻለሁ” ብሏል። ተገዶ በገባበት ጦርነት የገጠመውን ሲገልጽም “አብረውኝ የነበሩ ብዙ ጓዶቼ የጥይት እራት ሲሆኑ በዓይኔ አይቻለሁ” ብሏል።

ብስራት የሽብር ቡድኑ የሚመለምላቸው የትግራይ ወጣቶችና ህፃናት ሳይወዱ በግድ ወደ ጦርነት እንደሚማገዱ ዓለም ሊያውቀው ይገባል ነው ያለው። የትግራይ እናቶችም ትግራይ ባዶ ምድር እንዳትሆን የሽብር ቡድኑን በቃህ ሊሉት እንደሚገባ በመግለጽ መልዕክቱን አስተላልፏል።

ብስራት ‘ወልድያን የሆነ ቡድን፣ ደሴን ደግሞ ሌላው ይዟል፤ እናንተ ደግሞ አዲስ አበባን መያዝ አለባችሁ እየተባልን ተታለናል’ ሲል ነው የተናገረው።

‘መንግስት አቅም አንሶታል እኛን መዋጋት አይችልም’ ብለው አታለውን ከገባን በኋላ ያለው እውነት ግን የትግራይ ወጣቶችን ማስፈጀት ብቻ ነው በማለት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply