Site icon ETHIO12.COM

ከብርሸለቆ ውትድርና ማሰልጠኛ ተመርቀው ለግዳጅ የተዘጋጁት ባልና ሚስት


በትዳር ዓለም ለአንድ ዓመት ያህል የቆዩት ሮዛ አህመድ እና ኤሊያስ አባሜጫ የኢትዮጵያ ነገር አይሆንላቸውም።

ጣፋጭ ጊዜያቸውን በቤታቸው ቁጭ ብለው ሲያሳልፉ የነበሩት ጥንዶቹ የእናት ሀገርን የሕልውና ጥሪ ሲሰሙ ልባቸው ለዘመቻ መነሳሳቱን ይናገራሉ።

“እኛስ ለምን መከላከያ ሠራዊቱን ተቀላቅለን ሀገራችንን አናገለግልም?” የሚል ሃሳብ ያድርባቸዋል።

ጥንዶቹ በጉዳዩ ላይ በበቂ ሁኔታ ከመከሩ በኋላ ጅማ ዞን በሚገኝ አንድ ጣቢያ ሄደው ለውትድርና እንደተመዘገቡ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘጋቢዎች ተናግረዋል።

የአጋጣሚ ነገር ሆነና ጥንዶቹ ለውትድርና ስልጠናው ወደብርሸለቆ ማሰልጠኛ አንድ ላይ ገቡ።

አሁን ላይ ጥንዶቹ ስልጠናቸውን አጠናቀው በመሰረታዊ ወታደርነት በመመረቃቸው ለዘመቻ ዝግጁ ሆነዋል።

“ከዚህ በኋላ ዓላማችን ሁሉ የሀገር ጠላት የሆነውን ከሃዲ ቡድን ማጥፋት ነው፤ ከድል በኋላ ሀገር ሰላሟን ስታገኝ ያኔ እኛም ስለልጆች እና ስለቀጣይ እቅዶቻችን ማሰብ እንጀምራለን” ብለዋል።

ጥንዶቹ የትዳር አጋሮች ለሀገር ሕልውና በጀግንነት ለመፋለም ለሕይወታችን አንሳሳም ሲሉ በወኔ ለግዳጅ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

EBC

Exit mobile version