በትህነግ ሽንፈት ዋዜማ- የአሜሪካ ወታደሮች ከወር ተኩል በኋላ ወደ ጅብቲ ይጓዛሉ

ከሁለት ጠቅላይ ግዛቶች የተውጣጡ አንድ ሺህ ወታደሮች ያካተተ “ግብረኃይል” ከአንድ ወር ተኩል በኋላ ወደ አፍሪካ ቀንድ እንደምታዘምት አሜሪካ አስታወቀች። ግብረኃይሉ “ቀዩ ዘንዶ” በሚል ስያሜ የሚጠራ ሲሆን በዜናው ጦሩ “ወደ ኢትዮጵያ ይሄዳል” በሚል የተነሳ ጉዳይ የለም። የተሰጠውም ተልዕኮ ለአፍሪቃ ቀንድ ግብረኃይል ተጨማሪ ድጋፍ ለመስጠት ነው ተብሏል።

ቅዳሜ ኅዳር 18፤ 2014 ዓም (ኖቬምበር 28፤ 2021) በተካሄደ ሥነሥርዓት ከ800 በላይ የሚሆኑ የቨርጂኒያ ግዛት ብሔራዊ አባላት ዘብ የተሸኙ ሲሆን ወደ 200 የሚጠጉ የኬንታኪ ግዛት ብሔራዊ ዘብ አባላት እንዲሁ ሽኝት ተደርጎላቸዋል፡፡

ይህ ከአሜሪካ የተላከው ግብረኃይል በምስራቅ አፍሪካዊቷ ጅቡቲ ከተቀመጠው የአፍሪካ ቀንድ ጥምር ግብረኃይል ጋር የሚቀላቀል ነው፡፡

ቤድፎርድ ከተባለችው የቨርጂኒያ ግዛት የተላከው ግብረኃይል ከኬንታኪው ጋር በመቀላቀል ወደ ቴክሳስ ግዛት በመሄድ ከ30 እስከ 45 ቀናት የሚወስድ ተጨማሪ ሥልጠና ይወስዳል፡፡ ይህ ሥልጠና ካበቃ በኋላ ነው ወደ ጅቡቲ ወታደሮቹ የሚላኩት፡፡

በዕለቱ የተሸኙት ወታደሮች ቤተሰቦቻቸውን በለቅሶ በተሰናበቱበት ወቅት “ሽኝት ቀላል ነገር አይደለም፤ ሁልጊዜ በጣም አስቸጋሪ ነው፤ በቤተሰቤ ሕይወት ውስጥ ቁልፍ የሆኑ ኩነቶች ያመልጡኛል” በማለት የግብረኃይሉ አዛዥ ሌተና ኮሎኔል ተናግረዋል፡፡

“ለቨርጂኒያ ብሔራዊው ዘብ 10 ዓመት ሳገለግል ይህ የመጀመሪያዬ ነው ወደ ውጭ አገር ስላክ” በማለት መጋቢ ሃምሳ አለቃ ካትሪን ተናግራለች፡፡ ከተጋቡ ሁለት ወራት የሆናትን ሚስቱንና ወላጆቹን ስሜት እየተናነቀው የተሰናበተው ሌላኛው ወታደር “ለዘመቻ መላክ በጣም ይደብራል፤ አባቴም ወታደር ስለነበር ሁኔታውን ይረዳል፤ ለሚስቴ ጥሩ እንክብካቤ ያደርግላታል ብዬ አስባለሁ” ብሏል፡፡

ዜናውን የተከታተሉ እንደሚሉት እነዚህ ወታደሮች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ እና ውጊያ የሚያደርጉ አይደሉም፤ በዜናው እንደተጠቀሰው ጅቡቲ ለሚገኘው ኃይል ድጋፍ ለማድረግ ነው፡፡ ነገርግን ወደ ኢትዮጵያ እንግባ እንኳ ቢሉ ለሕይወቱ ቅንጣት ከማይሳሳ መከላከያ ሠራዊት፣ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ጋር ነው በአገሩ መልከዓምድር የሚገጥሙት ብለዋል፡፡

ትህነግ ወደ ሚሌ ሊያደርግ ያቀደውን ጉዞ በጭፍራም ይሁን በባቲ መስመር እንዳይሳካ ሆኖ በከፍተኛ ሽንፈት ላይ ባለበት ወቅት ይህ የአሜሪካ ግብረኃይል ለዘመቻ መላኩ የትህነግን ክስረት የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በአንጻሩ ትህነግን ለመታደግ ቢሆን ኖሮ ቢቻል ከዚህ በፊት ባይሆን አሁን በፍጥነት መላክ ነበረበት፡፡ ሆኖም ከአንድ ወር በኋላ መላኩ በዜና ዘገባዎችም እንደተገለጸው አሜሪካ የራሷን መከላከያ ኃይል ለማጠናከርና ካስፈለገም የዜጎቿን ደኅንነት ለማስጠበቅ የላከቸው ኃይል እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

የቨርጂኒያው ኃይል የተሸኘበት ቤድፎርድ የተባለችው ከተማ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበራት ሕዝብ ብዛት 3200 የነበረ ሲሆን በወቅቱ ብዙ ወታደር ያጣች ከተማ ነች፡፡ እኤአ በ1944ዓም 150ሺህ የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ፈረንሳይ ከዘመቱ በኋላ እዚያ በደረሱበት የመጀመሪያ ቀን 4500 ወታደሮች ሲሞቱ ከእነዚያ ውስጥ 19ኙ ከቤድፎርድ ከተማ ቨርጂኒያ ግዛት የተላኩ ነበሩ፡፡ በጦርነቱ በአጠቃላይ 35 ወታደሮች ከከተማዋ ብቻ ሞተዋል፡፡

የዛሬ 28 ዓመት የሶማሌውን አንጃ መሪ ጄኔራል ፋራህ አይዲድን በቁጥጥር ሥር ለማዋል ከተላኩ የአሜሪካ ወታደሮች 19ኙ በሶማሊያ ኃይል ተገድለው 73ቱ ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል፡፡ ከተገደሉት መካከል የተወሰኑት በሞቃዲሾ መንገዶች ላይ በመጎተታቸው አካላቸው ተቆራርጦና በጣም ከፍተኛ እንደደረሰባቸው የሚታወስ ነው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

Leave a Reply