Site icon ETHIO12.COM

ተ.መ.ድና ኢሰመኮ፤ በትግራይ ክልል በጋራ ሲያከናውኑት የነበረው ምርመራ ተጠናቀቀ

የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፤ በትግራይ ክልል ባለው ውጊያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት፣ የሰብአዊነት እና የስደተኞች የህግ ጥሰቶችን በተመለከተ ሲያከናውኑት የነበረውን የመስክ ምርመራ አጠናቀቁ። የምርመራው የመጨረሻ ሪፖርት በመጪው ጥቅምት 22፤ 2014 ይፋ ይደረጋል ተብሏል። 

የዓለም ዐቀፉ እና የሀገር አቀፉ የሰብአዊ መብት ኮሚሽኖች ጥምረት፤ አዲስ አበባን ጨምሮ በትግራይ እና የአማራ ክልል ከተሞች ሶስት ወራት የፈጀ ምርመራዎችን ሲያካሂድ መቆየቱን ዛሬ አርብ፣ ጷጉሜ 5 በተሰራጨ መግለጫ ላይ ተገልጿል። ምርመራው የተከናወነባቸው ከተሞች መቐለ፣ ውቅሮ፣ ሳምረ፣ አላማጣ፣ ቦራ፣ ማይጨው፣ ዳንሻ፣ ማይካድራ፣ ሁመራ፣ ጎንደር፣ ባህር ዳር እና አዲስ አበባ መሆናቸው በመግለጫው ተመልክቷል። 

ምርመራዎቹን ያከናወነው ቡድን ከተጎጂዎች እና ምስክሮች፣ ከክልል እና ከፌደራል ባለሥልጣናት፣ ከሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከሕክምና እና ከፍትህ ባለሥልጣናት እንዲሁም በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ከ200 በላይ ቃለ ምልልሶችን አድርጓል ተብሏል። ቡድኑ በደህንነት ስጋት ምክንያት አንዳንድ አካባቢዎችን መድረስ ባይችልም ከአካባቢዎቹ የሸሹ ተጎጂዎችን እና ምስክሮችን ማነጋገሩም ተገልጿል። ከዚህ በተጨማሪም ሰነዶችን፣ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን፣ ፎቶግራፎችን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን መመርመሩም ተነግሯል።  

በትግራይ ክልል ስላለው የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ እና በጥምር ምርመራው የተከናወኑ ስራዎችን በተመለከተ፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባሽሌት በሚቀጥለው ሳምንት ሰኞ ለተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ማብራሪያ እንደሚሰጡም በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።   

የምርመራ ሂደቱን በተመለከተ ኮሚሽነር ባሽሌት ሲናገሩ “በርካታ የደህንነት እና የሎጂስቲክስ ችግሮች ቢኖሩም የጋራ ቡድናችን በትግራይ ውስጥ ስላለው የሰብአዊ መብት ሁኔታ ተዓሚኒነት ያለው መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል፣ ውጤታማ የሆነ፣ ነጻና እና ገልለተኛ ምርመራ ለማድረግ ችለናል። የሰነድነው [ምርመራ] ጥሰቶች ለተፈጸመባቸው ተጎጂዎች መፍትሄ ለማበጀት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን አስተዋጽዖ ይኖረዋል” ብለዋል።  

ኮሚሽነር ዳንኤል በበኩላቸው ጥምር የምርመራ ቡድኑ ስራውን ሲያከናውን የቆየው፤ በጋራ ስምምነት ላይ በተደረሰባቸው የማጠቀሻ ደንቦች፣ የአሰራር ዘዴዎች እንዲሁም የስምሪት እና የመረጃ አሰባሰብ እቅዶች በመመራት እንደነበር አስረድተዋል። የምርመራ ቡድኑ “ጉዳት ባለማድረስ፣ በገለልተኝነት፣ በምስጢራዊነት፣ በታማኝነት እና በተረጋገጠ ተጎጂ ላይ ያተኮረ አቀራረብን በመተግበር መርህ ሲመራ ነበር” ሲሉም የአሰራር ሂደቱን አብራርተዋል።

የምርመራ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት የሰበሰባቸውን ዙሪያ መለስ መረጃዎች የመተንተን ስራን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል። በመጪው ጥቅምት ወር የሚወጣው የምርመራው የመጨረሻ ሪፖርት፤ በምርመራ የተደረሰባቸው ግኝቶችን፣ ድምዳሜዎችን እና ምክረ ሃሳቦችን የሚያካትት ነው ተብሏል። 

በሃሚድ አወል (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)


ዛጎል ቲዩብ- ማይካድራ – እናት፣ ሚስት፣ ልጅ … ፊታቸው ጭፍጨፋ ሲካሄድ ያዩትን ምስክርነት ይሰጣሉ፤ ይህንን ማስተባበል አይቻልም –


ማይካድራን ጨምሮ እንዲህ ያለው ግፍ ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚኅን አይታ ብቁ ኣይደለም
Exit mobile version