Site icon ETHIO12.COM

ደሴ ተፈናቃይ የመቀበል አቅሟ አለቀ – ውደ ኮምበልቻ

“… የተፈናቃዮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑና ደሴ ከተማ ከዚህ በኋላ ተፈናቃዮችን መቀበል ስለማትችል ወደ ኮምቦልቻ እየላክናቸው ነው ” ሲሉ የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሰኢድ የሱፍ አስታወቁ።

ደሴ በጦርነት ምክንያት ከሰሜን ወሎ ዞን የተፈናቀሉ ዜጎች እያስተናገደች መሆኑ ይታወቃል፤ የተፈናቃዮች ቁጥር ግን ከተማዋ ከምታስተናግደው አቅም በላይ በመሆኑ ወደ ኮምቦልቻ ከተማ እየተላኩ ነዉ።

በአሁን ሰዓት ከሰሜን ወሎ ዞን በርካታ አካባቢዎች በጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎች በደሴ እና ኮምቦልቻ ተጠልለዋል።

የደሴ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ሲኢድ የሱፍ ለኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ሬድዮ በሰጡት ቃል ፥ በደሴ ከተማ በመንግስትና በግል ትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር 275 ሺህ መድረሱን አመልክተዋል።

ምክትል ከንቲባው እንዳሉት የተፈናቃዮች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑና ደሴ ከተማ ከዚህ በኋላ ተፈናቃዮችን መቀበል ስለማትችል ወደ ኮምቦልቻ እየተላኩ ነው።

ከተፈናቃይ ዜጎች ቁጥራቸው እየጨመረ መምጣት አንጻር ደሴ ከተማ የቦታ እጥረት አጋጥሟልም ተብሏል።

ከሰሜን ወሎ የተፈናቀሉ 275 ሺ ዜጎች በመንግስት የተመዘገቡት ብቻ ናቸው ያሉት አቶ ሰኢድ፣ ከቤተሰብ ጋር የተጠለሉት ቁጥር በዉል እንደማይታወቅና ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከተፈናቃይ ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ የእርዳታ ተደራሽነት ችግር መኖሩን የተናገሩት ምክትል ከንቲባዉ፣ እስካሁን ዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች ግን ወደ አካባቢው እንዳልሄዱም አረጋግጠዉልናል።

Credit : Ethio FM 107.8

Exit mobile version