Site icon ETHIO12.COM

ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ 30 የዓለም ሀገራት በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚደረገውን የአንድ ወገን ማዕቀብ ተቃወሙ

የአንድ ወገን አስገዳጅ እርምጃዎችን (unilateral sanctions) መጠቀም ከተባበሩት መንግስታት ቻርተር እና ዓለም አቀፍ ሕግ ፣ ከብዙ ወገንተኝነት እና ከዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መሰረታዊ መርሆዎች ጋር ይቃረናልብለዋል

ቻይና እና ሩሲያን ጨምሮ 30 የዓለም ሀገራት በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚደረገውን የአንድ ወገን ማዕቀብን በመቃወም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደብዳቤ ጽፈዋል።

ሀገራቱን በመወከል ደብዳቤውን ለተመድ ያስገቡት በተመድ የቻይና ቋሚ ተወካይ አምባሳደር ዣን ጁን ናቸው። የኮቪድ-19 በዓለም ሀገራት፣ በተለይ ደግሞ በታዳጊ ሀገራት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ልማት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑ በደብዳቤው የተገለጸ ሲሆን፣ ሁሉም የተመድ አባል ሀገራት ዓለም አቀፍ ወረርሽኙን በዓለም አቀፍ ትብብር እና አብሮነት ላይ ተመሥርቶ መከላከል እንደሚገባ ተመልክቷል።



“የተመድ ቻርተር ውስጥ የተካተቱትን ዓላማዎች እና መርሆዎችን መከተል እና ቻርተሩ በሚያዝዘው መሠረት ሀገራት እርስ በርስ የመተባበር ግዴታቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን” ብለዋል ደብዳቤውን የጻፉት አባል ሀገራቱ “የተመድ ቻርተርን ዓላማዎችና መርሆዎችን እንዲሁም ባለብዙ ግንኙነትንና መሠረታዊ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን ያካተተውን ዓለም አቀፍ ሕግን በተቃረነ መልኩ በታዳጊ ሀገራት ላይ የሚወሰዱ አስገዳጅ የተናጠል እርምጃዎች በእጅጉ ያሳስቡናል” ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዒላማ በተደረጉ ታዳጊ ሀገራት ላይ የሚወሰዱ አስገዳጅ የተናጠል እርምጃዎች በሀገራቱ ላይ ከባድ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሰብአዊ ጫና የሚያስከትሉ በመሆኑ ሀገራቱ ሰብአዊ መብትን ለማሻሻልና ለመጠበቅ የሚያደርጉትን ጥረት በእጅጉ እየገደቡ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የተቃውሞ ደብዳቤውን ለተመድ የላኩት አባላት፦ አንጎላ፣ አንቲጓ እና ባርቡዳ፣ ቤላሩስ፣ ቦሊቪያ፣ ቬኒዙዌላ፣ ቡሩንዲ፣ ካምቦዲያ፣ ካሜሩን፣ ቻይና፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኩባ፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ዶሚኒካ፣ ግብፅ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ፣ ኤርትራ፣ ኢትዮጵያ፣ ኢራን፣ ላኦስ፣ ናሚቢያ፣ ኒካራጓ፣ ፓኪስታን፣ የሩሲያ ፌዴሬሽን፣ ሴይንት ቪንሰንት እና ግሬናዲንስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ስሪላንካ፣ ፍልስጤም፣ ሱዳን፣ ሶሪያ እና ዚምባብዌ ናቸው።

Exit mobile version