Site icon ETHIO12.COM

“ትህነግ በሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ተክኗል”

የአፍሪካ ቀንድ የደኅንነት ጉዳዮች አጥኚና ካናዳ የሚገኘው ባልሲሊ የውጭ ግንኙነቶች ትምህርት ቤት ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ዠራልድ በአፍሪካ ቀንድ ከሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ጋር በመሆን በደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ፣ ሶማሊያና ኢትዮጵያ በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ የጥናት ስራዎችን የሰሩ ናቸው።

ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ዠራልድ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ሃሳብ ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋር ቃለምልልስ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል። በዚህ ቃለምልልሳቸው ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በመሬት ላይ የሚካሄድ ብቻ ሳይሆን ትርክትን ለመቆጣጠር የሚደረግ የመረጃ ጦርነት ጭምር መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህ ረገድ ለ27 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው አሸባሪው ህወሓት በሚያስተጋባው መረጃ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ወደ አንድ ወገን ብቻ ላጋደለ ትርክት እንዲጋለጥ ማድረጉን አብራርተዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ‘የኢትዮጵያ መንግስት እርዳታ ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገባ አግዷል’ በሚል በተደጋጋሚ ይወቅሳል፤ “ሆኖም በሌላኛው ወገን ላይ ምንም ዓይነት ወቀሳ ሲያደርስ አይሰማም” የሚሉት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ዠራልድ ሰብአዊ ቀውሱ ከትግራይ ተሻግሮ ወደ አማራና አፋር ክልሎች እንዲስፋፋ ካደረገ በኋላ እንኳን የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቡድኑን እኩይ ድርጊት ሊያወግዝ አልፈቀደም። በኢትዮጰያ መንግስት ላይ የማዕቀብ ማስፈራሪያ ሲደርስ የህወሓት ተዋጊዎች ህፃናትን ለውትድርና ሲያሳትፉ የሚያሳይ በቂ መረጃ ቢኖርም የቅጣት እርምጃም ሆነ ውግዘት አልደረሰበትም ሲሉ ፕሮፌሰር አን ገልጸዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ለአስር ጊዜ ያህል ስብሰባዎችን ማካሄዱን የሚያነሱት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ዠራልድ፤ በአህጉር ደረጃ ወይም በቀጠናው ባሉ ጎረቤት ሀገራት መካከል ሊካሄዱ የሚገቡ እንደህዳሴው ግድብ ያሉ ጉዳዮችን ግራ በሚያጋባና በሚያሳስብ ሁኔታ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ሲመጡ እያየን ነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ መንግስትን እርምጃ በተመለከተ ማንኛውም የምዕራቡ ሀገር እንደዚህ ዓይነት የታቀደና ቀድሞ የተዘጋጀ ጥቃት በብሔራዊ መከላከያ ሰራዊቱ ላይ ቢደርስ ሊያደርገው የሚችለው ነው በማለት ያብራሩት ፕሮፌሰሯ፤ እንዲያውም የምዕራብ ሀገራት የጎረቤት ሀገራት ወታደሮችን ልከው ወይም በጸጥታ ትብብር አሊያም ደግሞ የደህንነትና የድንበር ጥበቃ በማድረግ እንዲተባበሩ ሊጋብዙ ይችላሉ ሲሉ ይናገራሉ። የሀሰተኛ መረጃ ስርጭት ለሽምቅ ውጊያ እጅግ ጠቃሚ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ዠራልድ ህወሓት ደግሞ በዚህ የተካነ ነው ይላሉ።

ለዚህም እንደማሳያ የተጠቀሙት አሸባሪው ህወሓት ደርግን ለመጣል ተመሳሳይ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ተጠቅሞ እንደነበር ነው። ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ሁኔታ እንድትወጣ ከተፈለገ በዋናነት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚጠቀምባቸው እንደመግለጫ ማውጣት፣ ማውገዝ፣ ሰላም አስከባሪ ሃይል ሀገርን እንዲያረጋጋ መጠበቅ ወይም ማእቀብ መጣልን የመሳሰሉ መሳሪያዎች በድጋሚ ሊያስብባቸው እንደሚገባ ቪኦኤን ጠቅሶ ኢዜአ ዘግቧል።

Exit mobile version