Site icon ETHIO12.COM

” በመንጋ የመጣው ሃይል እየተመከተ ነው፤ የተደራጀ ንቅናቄ”

❝የተከፈተብንን ጥቃት ለመመከት መፍትሔው የተደራጀ ንቅናቄ ነው❞ ሲል የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት አስገነዘበ። ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውም እንደሚከተለው ቀርቧል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ አሸባሪው የትህነግ ቡድን አለኝ የሚለውን ኃይል በማሰባሰብ በአፋርና በአማራ ክልሎች ባሉት ግንባሮች መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩ ይታወቃል። በዚህ ጥቃት በርካታ ንጹሐን ዜጎችን ገድሏል፤ ንብረት ዘርፏል፤ የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጋዝ አርከፍክፎ አቃጥሏል፤ በእነዚህ አካባቢዎች ሁሉም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲገቱ አድርጓል።

የተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ እንዳይደርሳቸው አድርጓል። የሐሰት ፕሮፖጋንዳንም እንደ ዋነኛ መሳሪያው በመጠቀም ላይ ይገኛል። ጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን፣ የአማራና አፋር ልዩ ኃይልና ሚሊሻዎች በመንጋ የመጣውን ጠላት ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በመሆን በሚያኮራ መልኩ እየመከቱ ይገኛሉ። በተለይም ዘራፊው ቡድን በውጫሌ፣ ተሁለደሬ፣ ወረባቦ ደላንታና ጭፍራ ግንባሮች ጦርነት የከፈተ ቢሆንም የጸጥታ ኃይሉና የኅብረተሰቡ የጋራ ጥምረት ይህንን ወራሪ ኃይልና ሰርጎ ገቦችን በጀግንነት እየመከተ ይገኛል።

በሌሎች ግንባሮች ሽንፈትን እያስተናገደ የሚገኘው የጁንታው ቡድን ያለውን ኃይል ኹሉ አሰባስቦ ወደ ወሎ አምጥቷል። ይህ ደግሞ የመጨረሻ ጥረቱ ነው። ዓላማውም ሕዝቡን ማስጨነቅና ማሸበር እንጂ ማሸነፍ አይደለም። ይህንን የሽብር ቡድኑን የጥፋት እንቅስቃሴ ለመመከት የደቡብ ወሎና የአፋር ሕዝብ በተለይም ወጣቶች እያደረጉ ያሉት አኩሪ ተጋድሎ እጅግ የሚደነቅ ነው። ለፀጥታ ኃይሎች ደጀን ከመሆን ጀምሮ በየሸጡ የሚሽሎኮሎኩ የጠላት ኃይሎችን በመመከት፤ በየአካባቢው ለስለላ የተሰማሩ ፀጉረ-ልውጦችንና ሰርጎ ገቦችን ተከታተሎ በመያዝ ታሪክ የማይዘነጋው ተጋድሎን እየፈጸሙ ይገኛሉ።

ጠላት ይህንን የሕዝብ አኩሪ ተጋድሎ ጥላሸት የሚቀቡ አፍራሽና ሐሰተኛ ፕሮፖጋንዳዎችን እየነዛ ነጻ አካባቢዎችን እንደተያዙ በማስመሰል ሕዝብን ለማሸበር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል። ኅብረተሰቡ በዚህ በጠላት አፍራሽ ፕሮፖጋንዳ ሳይረበሽ የጀመረውን ሀገር የማስቀጠል ተጋድሎ በተደራጀ ንቅናቄ መመከት፤ አካባቢና ቀዬውንም ነቅቶ መጠበቅ ይኖርበታል።

ከጦርነት አካባቢ ውጪ ያሉ ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለዚህ ታሪካዊ ተጋድሎ አጋርነታቸውንና ደጀንነታቸውን እንደ እስከዛሬው ኹሉ እንዲያረጋግጡም መንግሥት ጥሪ ያቀርባል። ከመደበኛ የጦርነት አካሄድ በተቃራኒ የመጣን ኃይል ማንበርከክ የሚቻለው የተደራጀ ሕዝባዊ ንቅናቄን በመፍጠር ነው። የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት

Exit mobile version