Site icon ETHIO12.COM

በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ ኬላዎች ላይ በሚካሄድ ጥብቅ ፍተሻ ሰርጎገቦች እየተያዙ ነው

በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ ወቄ፣ ፍላቂት ገረገራ፤ እና ኮኪት አካባቢዎች በሚገኙ ኬላዎች ላይ በሚካሄድ ጥብቅ ፍተሻ በየቀኑ ከሁለት እስከ ሶስት ሰርጎ ገቦች እየተያዙ መሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያነጋገራቸው አስተያየት ሰጪዎች አረጋግጠዋል።

ዘጋቢዎቻችን በሰሜን ወሎ ዞን ወቄጣ ኬላ ፍተሻ ሲያካሂዱ ያገኗቸው ሚሊሻ ጌታያ አዳነ በጥብቅ የኬላ ፍተሻው አሸባሪ ቡድኑ አማራ ክልልን ከወረረ በኋላ የተሰጡ አዳዲስ መታወቂያዎችን የያዙ ሰርጎ ገቦች፣ ሁለትና ሶስት አይነት መታወቂያ ያላቸው ጸጉረ ልውጦች እንዲሁም ህገወጥ መሳሪያ የያዙና የሽብር ቡድኑ ሰላዮች በኬላ ፍተሻዎች ላይ መያዛቸውን ገልጸዋል።

አካባቢው ከገረገራ ወደ ጋሸና በሚወስደው አውራ ጎዳና የሚገኝ ዋና መተላለፊያ መንገድ በመሆኑ የወራሪው ቡድን ሰርጎገቦች እንዳያልፉ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በኮኪት ኬላ ፍተሻ ያገኘናቸው ወጣት አለበል አረጋና ወጣት ጥላሁን ጌታዬ፤ ለፍተሻው ስራ 20 ወጣቶች በመደራጀት ቀንና ሌሊት ጭምር በበጎ ፈቃደኝነት እየሰራን ነው። በአሁኑ ሰዓት ማንንም ማመን ስለማያስፈልግ የትኛውንም አይነት መንገደኛ እያስቆምን ስለህጋዊነቱ ማጣራት እናደጋለን። ወጣቱ ተደራጅቶ የኬላ ፍተሻውን በማጠናከሩ በየቀኑ ሁለትና ሶስት ሰርጎ-ገቦች እየተያዙ መሆኑን ገልጸዋል።

በፍላቂትና ገረገራ ከተማ አስተዳደር ነዋሪ የሆኑት አቶ ሲሳይ መቆያ በበኩላቸው፤ “ወጣቶቹን ላግዝ ብዬ በኬላ ፍተሻው ላይ ተገኝቻለሁ። ከዚህ በፊት በነበሩ ልምዶች የሐይማኖት አባት አሊያም የተቸገረች ሴት በመምሰል ሊያልፉ የሞከሩ ሰላዮች ተይዘዋል” ብለዋል።

በመከላከያ ሠራዊት የ51ኛ ክፍለጦር የ4ኛ ሬጅመንት አዛዥ ሻለቃ ደስታ አመንቴ ወጣቶችና ሚሊሻዎች በኬላ ፍተሻ ስራው ከመከላከያ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ ይገኛል ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በጌትነት ተስፋማርያም (ወቄጣ) (ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version