Site icon ETHIO12.COM

የድል ምስጢር…


ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በአንድ ንግግራቸው እንዳነሱት * የሙቀጫ ልጅ* በሆኑባት ልጆቿ ምክንያት ሰሜኑ የአገራችን ክፍል ጦርነት ውስጥ መሆኑን በሌላም አካባቢ ያለው ማህበረሰብም መዘንጋት የለበትም፡፡ ሁሉም በሰላማዊ ወቅት ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ አንድ ነገር ማበርከትም ይገባል፡፡

በጦርንት ወቅት ሁሌም ለአገሪቱ ክብርና ለወገኑ ደህንነት ሲል የሚዋደቁ የአገር መከላከያና ፌዴራል ፖሊስና ልዩ ሃይሎቻችን ጨምሮ ሌሎች የጸጥታ አካላት ጠላትን የመመከት፤ አለፍ ሲልም የገዛ እናታቸውን ካልረገጡ ስራ የሰሩ የማይመስላቸውን አደብ የማስገዛት ስራ እየሰሩ ነው፡፡

ለእነዚህ ሃይሎች ድል አድራጊነትና ጀግንነት ደግሞ ምንጩ አንድና ግልጽ ነው፤ እርሱም ደጀንና ሰራዊቱ የሚቀዳበት ምንጭ የሆነው ህዝብ ነው፡፡ አንድ ሰራዊት ሁሌም ቢሆን ደጀን የሚሆነው፤ ስንቅና ትጥቅ የሚያቀብለውና ከሁሉም ከሁሉም ስነ ልቦናውን ከፍ የሚያደርግ፤ የሚያጀግን ህዝብ ያስፈልገዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በእነዚህ እኩያን ምክንያት ተገዳ የገባችበት ጦርነት ላይም፤ጀግናው የአገር መከላከያ ሰራዊታችን፤ የተቃጣብትን ታሪክ በደማቅ ቀለም የጻፈውን የከሃዲዎች የፈሪ ዱላ ተቋቁሞ፤ እራሱን አደራጅቶ በአስራ አምስት ቀን ውስጥ አጸፋዊ እርምጃ በመውሰድ እነርሱ የሚመኩበትን የጁንታ መሪዎች ገሚሱን ከአፈር ቀላቅሎ የቀረውን ወደ ህግ አቅርቦ ነበር፡፡ በዚህ ስራ ውስጥ የህዝባችን ደጀንነት የተጫወተው ሚና የላቀ እንደነበር ይታወቃል፡፡

ከዚያ በላይ መሄድና የክልሉን ህዝብ የጦርነት ስነልቦና ውስጥ ማኖር ተገቢ ስላለሆነ፤ ሁሉም የጽሞና ጊዜ ወስዶ እንዲያስብ የተናጠል ተኩስ አቁም ታውጆ ሰራዊቱ ክልሉን ለቆ እንዲወጣ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ድሮውንም ለህግ ተገዢ ያልሆነው እብሪተኛውና ሽብርተኛው ቡድንም በመንግስት የተደረሰውን የተኩስ አቁም ውሳኔን በመተላለፍ በየስፍራው የቀበረው የጦር መሳሪያ አቧራውን አራግፎ አፈር ልሶ በመነሳት ለህዝብ ሰላም ግድ አለመኖሩን በአማራና በአፋር ክልሎች ዘልቆ በመግባት ጦርነት ከመክፈቱም ባሻገር በህጻናት፣በአቅመ ደካሞች፣በሴቶችና በአዛውንቶች ላይ የባሩድ ጥይቱን አዘነበባቸው፡፡

በዚህ የጠላት እኩይ ሴራና ክፋት የተመለከተው የሁለቱ ክልል ህዝቦች፤ለመከላከያ ሃይሉ ደጀን፤ ስንቅና ትጥቅ አቀባይ ከመሆን ባሻገር፤ ግንባር ድረስ ከሰራዊቱ ጋር በመሰለፍ ድል አድርገዋል፡፡ይህን ወራሪ ሃይልም ህልሙን ቅዠት አድርጎበት ካሰበበት እንዳይደርስ ወደ ኋላ እንዲያፈገፍግ አድርጎታል፡፡

ከሰሞኑም የተለመደ ህዝብ የማሳሳት የቆዬ ልምዱን እየተጠቀሙ ያሉት “የሙቀጫ ልጆች’’ በወሎ ህዝብ ላይ፤ ደሴና ኮምቦልቻን እንይዛለን በሚል ቅዠት ጦርነት አውጀዋል፡፡ይህ ቅዠታቸውን የማይሳካ ያደረገው፤ የደሴና አካባቢዋ ህዝብና ከመላው አማራ ወደ ስፍራው እየተንቀሳቀሰ ያለው ህዝብ ነው፡፡

ጠላት ተመትቶ ወደ ኋላ እንዲመለስና ተስፋ ቆርጦ ዋይ ዋይታ እንዲያበዛ ያደረገው ትልቁ የድሉ ሚስጥር የህዝቡ ደጀንነትና እንደ ህዝብ የህልውና አደጋ ውስጥ ነን ብሎ መነሳት ነው፡፡

ዛሬና ትናንትም ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ወሎ እየተመመ ያለው ህዝብም፤ ለጠላት ትልቅ የሚያሰፈራ ጦር፤ ለወገን ሰራዊት ደግሞ የስነ ልቦና ስንቅ ነውና ይጠናከር እላለው፡፡

በአብዲ ኬ/ ቸር እንሰንብት

Exit mobile version