Site icon ETHIO12.COM

የህወሀት የጥፋት ግስጋሴ ፍሬን ይዞ የኋላ ማርሽ በማስገባት ላይ ይገኛል

ዛሬ መልካም መረጃዎች በርክተው ደርሰውኛል። ቆቦና ዋጃ እየሆነ ያለው ልብ የሚያሞቅ ነው። ጀግኖቹ ስራቸውን እየሰሩ ነው። የወልዲያ ጉዳይም መስመር ይዞ ተስፋ በሚሰጥ እንቅስቃሴ ትግሉ ቀጥሏል። የአፋር ምድር ለህወሀት የሚፋጅ ረመጥ መሆኑ ሰሞኑን ዳግም እየተመሰከረ ነው። ሚሌን ቋምጦ የተነሳው የህወሀት ጀሌ አፈር ከድሜ በልቷል። የህወሀት የሚሌ ህልም – ቅዥት ሆኖ ቅስም በሚሰብር ውጤት ለጊዜው ተገትቷል። ባቲ የተሰገሰገው ጀሌ ለዳግም የሚሌ ዘመቻ ቁስሉን አክሞ፣ ስብራቱን ጠግኖ መምጣቱ አይቀርም። የአፋሮቹ ምህታታዊ ምትና የመከላከያ ሰራዊቱ ብርቱ ክንድ ሁለተኛ ሙከራቸውንም ሰባብሮ ከእንግዲህ ወደሚሌ ፊታቸውን አዙረው እንዳያዩ ማድረጉ አይቀርም።

ደሴንና ኮምቦልቻን የተመለከተው የዛሬው መረጃም ስለአከባቢዎቹ ከህወሀት ፕሮፖጋንዳ ባሻገር ያለውን ትክክለኛ ስዕል እንዳገኝ አድርጎኛል። ሁለቱ ከተሞች አሁንም ሙሉ በሙሉ በህወሀት ቁጥጥር ስር አይደሉም። ኮምቦልቻ የኢትዮጵያ ሰራዊት እንደሚገኝ አረጋግጫለሁ። በቁጥር ከ50 የማይበልጡ የህወሀት ታጣቂዎች ከፊል የከተማዋ ክፍል ውር ውር የሚሉ ሲሆን ከቀናት በፊት ገብተው የነበሩት ብዛት ያላቸው ጀሌዎች ዘረፋና ውድመት ከፈጸሙ በኋላ ወደባቲ ሄደዋል። በኮምቦልቻ ነዋሪ የሆኑ የህወሀት ደጋፊዎች ታጥቀው በዘረፋውም ሆነ በግድያው መሪ ተዋናይ እንደነበሩ ይነገራል።

ሰሞኑን የኢትዮጵያ ሰራዊት በከተማዋ ባደረገው ልዩ ኦፕሬሽን በምርኮ ተይዘው የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደራዊ ኦፊሰሮችን ማስለቀቅ እንደታቸለ ካገኘሁት መረጃ ለማወቅ ችዬአለሁ። አሁንም ከተማዋ ውስጥ አንዳንድ ቦታዎች የሚታዩት የህወሀት ደጋፊ ሆነው ከውስጥ ሲሰሩ ቆይተው መሳሪያ አንስተው ጎረቤቶቻቸው ላይ ተኩሰው የገደሉት ናቸው። የኢትዮጵያ ሰራዊት በቀጣይ ከተማዋን ነጻ እንደሚያደርግ ይጠበቃል።

ደሴም ያለው እውነት በአብዛኛው ተመሳሳይ ነው። ህወሀት ከፊል የከተማዋን ክፍል ይዞ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ሃይሎች ጋር ውጊያ በመግጠም ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ችያለሁ። በደሴና ኮምቦልቻ መሃል እንዲሁም ዙሪያ ገባውን የአየር ሃይል ስኬታማ ጥቃት በዛሬው ዕለት ማድረጉም በሚቀጥሉት ቀናት ነገሮች ሊለወጡ እንደሚችሉ ምልክት የሰጠ ነው። አንድ የህወሀት ኮሎኔል በዚሁ በደሴ ውጊያ መማረኩም በአከባቢው የህወሀት እድሜ ከቀናት ሊያልፍ እንደማይችል የሚያመላክት ነው። ከሚሴ ላይ ያለው ሁነት ደግሞ ለፖለቲካ ማዳመቂያ ከመሆን ያለፈ ወታደራዊ ጠቀሜታው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።

ህወሀቶች ከሸኔ ጋር ተገናኙ፣ በጋራ መንግስትን ሊያጠቁ ነው የሚለው ፕሮፖጋንዳ የኢትዮጵያን ህዝብ ስነልቦና ያሸብራል በሚል በህወሀትም ሆነ በአዝማቾቹ የምዕራብ መንግስታት እንዲራገብ ተፈለገ እንጂ ይህን ያህል አየር ይዞ የሚያስጮሁት ድል አይደለም። በከሚሴ የሸኔ መዋቅር ጠንካራ አይደለም። በትንሽ ሀይል አድፍጦ ጥቃት ለመሰነዘር የተደራጀ እንጂ ራሱን ችሎ፣ ሰፋ ያለ ቁመና ኖሮት የሚንቀሳቀስ ቡድን አይደለም። ህወሀት ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታው ሸኔን እንደማገዶ ተጠቀመው። ታሪክ ራሱን ደገመ።

አሁን እንደሚሰማው ሸኔና ህወሀት በከሚሴው ጉዳይ ለገላጋይ ያስቸገረ ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል። የድል ሽሚያው ለተካረረ አለመግባባት ዳርጓቸው መሳሪያ ሊያማዝዝ ወደሚችል ጥል እየገቡ ነው። ሸኔ ተክዷል የሚል ተቃውሞ በሸኔ መንደር ተጠናክሮ ወጥቷል። ህወሀቶች አመል ሆኖባቸው በከሚሴ የኦሮሞ ተወላጆችን ንብረት ዘርፈው እየወሰዱ መሆኑ ደግሞ የጫጉላው ጊዜ ሳያበቃ ወደፍቺ ሊያመሩ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው። የኦሮሞን ህዝብ ለህወሀት የክፋት ተልዕኮ አሳልፎ የሰጠው ሸኔ ከሁለት አንድ ያጣ ሆኖ ቀርቷል።

ነገሮች እየተለወጡ መሆናቸውን ግልጽ ምልክቶች እያየን ነው። የህወሀት የጥፋት ግስጋሴ ፍሬን ይዞ የኋላ ማርሽ በማስገባት ላይ ይገኛል። አዎን! ኢትዮጵያ ለጊዜው አጎንብሳ ይሆናል እንጂ አልተሰበረችም። ነገ የእኛ ነው። ነገ የኢትዮጵያ ነው። እንበርታ!

መሳይ መኮንን

Exit mobile version