Site icon ETHIO12.COM

ጦርነቱን በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ተገለጸ፤ በሁለት ግንባሮች የትህነግ ሰራዊት መበተኑ ተሰማ፤

የአሸባሪው ህወሓት ኃይሎች በፀጥታ መዋቅሩና ህዝቡ መካከል ያለውን መተማመን ለመሸርሸር የሐሰት ፕሮፓጋንዳ እያሰራጩ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ። ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ ተመለከተ።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ መላው ህዝብና የፀጥታ መዋቅሩ ከመቼውም በተሻለ ተናበው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ሚኒስትሩ ለፀጥታ አካላትና ለህዝቡ መናበብ ዋና ማሳያ አድርገው ያነሱት በግንባር እየተገኘ ያለውን ድልና በዜጎች ጥቆማ በቁጥጥር ስር እየዋሉ ያሉትን የሽብር ቡድኑ አባሪ ወንጀለኞች ነው።

ለሽብር ማስፈፀሚያ ሊውሉ የነበሩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች እንዲሁም ተመሳስለው የተሰሩ የፌደራልና የክልል ልዩ ኃይሎች የደንብ ልብሶች በህብረተሰቡና በፀጥታ መዋቅሩ የጋራ ትብብር ሊያዙ መቻላቸውን ተናግረዋል። ከፈተኛ መጠን ያለው የፌደራል፣ የአፋርና የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ልብስና ጣቃ ጨርቅ መያዙን አመልክተዋል። ባለቁና በግንባታ ላይ ባሉ ህንጻዎች ውስጥ ከፍተኛ ግምት ያለው የጦር መሳሪያና የጸጥታ ሃይሎች መለያ ልብስ እንዲሁም በአንድ ምስኪን ስም እሰክ ሰማኒያ ሚሊዮን ብር የሚደርስ የሂሳብ አካውንትን ጨምሮ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘን መያዙን አስታወቀዋል።

ሕዝብ በሙሉ ቁርጠኛነት ከጸጥታ አካሉ ጋር ሆኖ በመተቆምና በመስራቱ አሸባሪው ሃይል ያሰበው እንደከሸፈ ያወሱት ዶ/ር ለገሰ፣ መንግስት ለሕዝቡ ታላቅ አክብሮትና ምስጋና እንዳለው ተናግረዋል። ይህ መናበብና ተግግዞ ለአገር ህልውና የመስራት ባህል ሊቀጥል እንደሚገባም አመልክተዋል።

በግንባር እየተገኘ ባለው ድልም ከ10 ሺህ እስከ 15 ሺህ የሽብር ኃይሎች በወገን ኃይል እየተደመሰሱና ከጥቅም ውጪ መደረጋቸውንና በክፍለ ጦር ደረጃ ያደራጃቸው የሽብር ቡድኑ ኃይሎችም እንዲበተኑ መደረጉን ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የሽብር ቡድኑ በሚሌ እና ወረኢሉ ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የማጥቃት ሙከራዎች በወገን ኃይል ተመክተው ሳይሳኩ መቅረታቸውን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው አንስተዋል። ሃይሉም አዛዥ አልባ ሆኖ መበታተኑን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኑ በጦርነት ያጣውን ድል ዜናና ወቅታዊ አቋሙን ለመደበቅ በትግራይ ያልተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ደጋግሞ እያነሳ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖው እንዲበረታ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ላይ ማተኮሩን ሃላፊው ተናግረዋል። በትግራይ ጄኖሳይድ ስለመፈጸሙ የሚያሳይ ምልክት እንደሌለ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መበት ኮሚሽንና የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ ባደረጉት ማጣራት ይፋ ማድረጋቸውና ሪፖርቱም ተቀባይነት ማግነቱ አይዘነጋም። አሁን ላይ ትግራይ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ ባለመሆኑና ቡድኑ በወረራ በያዛቸው የአፋርና አማራ መሬት ላይ በሚደረግ የህልውና ዘመቻ ” ተገደልኩ” ብሎ አቤቱታ ማሰማት ቀልድ መሆኑንን በርካቶች እየገለጹ ነው።

በአዲስ አበባ ከሽብር ኃይሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ዜጎች በብሔራቸው ተለይተው በቁጥጥር ስር እየዋሉ እንደሆነ በሽብር ቡድኑና በውጭ ኃይሎች የሚናፈሰው ወሬም ፍጹም ሐሰት መሆኑን ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን የጠቀሰው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከሽብር ቡድኑ ጋር ግንኙነት የሌለው አንድም ሰው በቁጥጥር ስር እንዳልዋለ አስረድቷል።

ዶክተሩ ትህነግ ብሎ ጋምቤላ፣ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ሃደሬ ወይም ሌላ ብሄር እንደሌለ አመልክተው፣ ትህነግ የተደራጀውና በህቡዕ ያደራጀው በዘር ላይ ተመስርቶ በመሆኑ መንግስት በማስረጃ እርምጃ ሲወስድ ” በብሄሬ ተጠቃሁ” የሚል ለቅሶ እንደሚያሰማ፣ ይህም በምንም መለኪያ ተቀባይነት እንደሌለው አውስተዋል።

በተቃራኒው የአሸባሪው ህወሓት ኃይሎች በወረራ በያዟቸው የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ከ7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በሽብር ቡድኑ ከበባ ውስጥ ሆነው ግፍ እየተፈፀመባቸው መሆኑን ሚኒስትሩ አስታወቀዋል። ቤታቸው ድረስ መጥቶ የወረራቸው አካል የሚፈጽመው ግፍና የጅምላ ጭፍጨፋ በዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች ሽፋን እንደማይሰጠው፣ በላሊበላና ላስታ እንዲሁም ዋግ በረሃብ ሰዎች እየሞቱ እንደሆነ እየታወቀ ዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ዝም ማለቱ ያሳዘናቸው ” እኛ ምን በደልን” ሲሉ በዋሽንግቶን፣ ካናዳ፣ ሎንዶንና ብራስልስ ድምጻቸውን ማሰማታቸውም የሚታወስ ነው።

ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም በሽብር ቡድኑ ከበባ ውስጥ የሚገኙ ከ7 ሚሊዮን በላይ የአማራ እና የአፋር ክልል ነዋሪዎች እየደረሰባቸው ያለውን ግፍ እና መከራ ከአድሏዊነት ነፃ ሆኖ ሊያወግዘው እንደሚገባ በመግለጫው ላይ ተነስቷል። በተደጋጋሚም እየተነሳ ነው።

ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ለወገን ኃይልና ለተፈናቃዮች እያደረጉት ያለው ድጋፍ መቀጠሉን ያነሱት ሚኒስትሩ፣ የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ የቀደሞ ሰራዊት አባላትና ወጣቶችን ጨምሮ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዘማቾች የመከላከያ ሠራዊት እና ልዩ ኃይሎችን እንዲቀላቀሉ በማድረግ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በሌላ ተመሳሳይ ዜና አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኀይል በዋግኸምራ በኩል ያሰማራው ኃይሉ በአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ጥምረት ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት ተመትቶ መመለሱን የአማራ ማስ ሚዲያ አስታውቋል።

ሕዳር 8/2014 ዓ.ም ከሳመሬ ተነስቶ ወደ ጋሸና ያቀና የነበረ የትግራይ ወራሪ ኃይል በአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ተመትቶ ሙትና ቁስለኛ ሆኖ የተረፈው ወደ ኮረም አቅጣጫ ተበታትኗል።

በተመሳሳይ ዛሬ ሕዳር 9/2014 ዓ.ም አበርገሌ አካባቢ የነበረውን ኃይሉን አሰባስቦ ከሰቆጣ ወደ ቀውዝባ አሰፍስፎ ሲመጣ ተደምሷል። የራያ ፋኖ እና ጢነኛ በመቀሌ አላማጣ ቆቦ ወልድያ መስመር እንዳያልፍ የእግር እሳት የሆነበት የትግራይ ወራሪ ኃይል፣ የመቀሌ አበርገሌ ሰቆጣ ላሊበላ ወልድያ ደሴ መንገድ በዋግ ትንታጎች ተቆርጦበት መውጫ አጥቷል።

በዋግኸምራ ግንባር በርካታ አካባቢዎች በአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ቁጥጥር የገቡ ሲሆን የትግራይ ወራሪ ኃይል የሚያደርጋቸው ስምሪቶች በተደጋጋሚ እየከሸፉበት እንደሚገኝ ከግንባር ምንጮች እንደነገሩት ገልጾ አሚኮ አመልክቷል።

ትህነግ “ጀግናው የትግራይ ሰራዊት በጋሸና፣ በወረኢሉ፣ በአጣየና በሚሌ ግንባሮች ደማቅ አንፀባራቂ ድል በማስመዝገብ የማጥቃት እርምጃውን አጠናክሮ ወደፊት እየገሰገሰ ይገኛል” በሚል ከሁለት ቀን በፊት ካወጣው መግለጫ ሌላ ይህ እስከታተመ ድረስ ያለው ነገር የለም። በውቀቱ በሚሌ ግንባር በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ በማቅረብ ትህነግ ሚሌ እንደገባ ተደርጎ የተወራው ወሬ ሃሰት መሆኑን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ከጅቡቲ እየመጡ መሆናቸውን በመግለጽ ምስክርነት ሲሰጡ ነበር። ወረኢሉ ተያዘች የተባለውም ሃሰት እመሆኑንን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች መናገራቸው አይዘነጋም። በግንባር ቅርብ ሆነው እየሰሩ ያሉት አቶ ዩሱስፍ ኢብራሂምም ደሴና ኮምቦልቻን የምንይዝበትን ቀን በጣቶቻችን እየቆጠርን ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን እንደሰጡ መዘገባችን ይታወሳል።

Exit mobile version