Site icon ETHIO12.COM

በአፋር የተረጂዎች ቁጥር ጨምሯል፤ በአማራና ትግራይ በምግብ እጥረት ህይወት እያለፈ ነው

የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ጽ/ቤት በክልሉ ውስጥ የተፈናቃይ ተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አስታውቋል። ጦርነቱ ተስፋፍቶ በቀጠለባቸው ባለፉት 3 ሳምንታት በአፋር የተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 300 ሺህ ማሻቀቡን ፅ/ቤቱ ለዶቼቨለ ሬድዮ በሰጠው ቃል ገልጿል።

የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን ለሬድዮ ጣቢያው በሰጡት ቃል ፥ ” ጦርነት ቀጠና ውስጥ የዞን 2፦ በርሃሌ አለ፤ እንዲሁም ከዞን 2 ጀምሮ ያለው፦ እዋ፤ አውራ እንዲሁም ጭፍራ፤ ዞን አንድ ደግሞ ሐዳር እያለ ወደ ዞን አምስትም ይሻገራል። ስለዚህ በአጠቃላይ አሁን ያለን የተፈናቃይ ቁጥር ከ300,000 በላይ ይደርሳል ” ብለዋል።

በዚሁ ጦርነት የተፈናቀሉትን የተሻለ ደህንነት ወዳለበት አከባቢዎች እንዲጠጉ እየተሠራ መሆኑን ተገልጿል። ጭፍራ አከባቢ የነበሩት 60 ሺ ገደማ ተፈናቃዮች ወደ ሚሌ አቅጣጫ 50 ኪ.ሜ. ያህል ርቀት ላይ በተገነባ መጠለያ እየተረዱ መሆናቸውን ፅ/ቤቱ አሳውቋል። ለተፈናቃዮቹ ለመድረስ መንግሥት እና የርዳታ ተቋማት ድጋፍ እያደረጉ ቢሆንም፤ በቂ እንዳልሆነ ተገልጿል። እስከ ከሚሴ አዋሳኝ ወረዳዎች ከ1.3 ሚሊየን የማያንስ ሕዝብ የጦርነ ገፈት ቀማሽ መሆኑንም የአፋር ክልል አደጋ ስጋት ጽ/ቤት ለሬድዮ ጣቢያው አሳውቋል።

በአማራ ክልል ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የከፋ ችግር ላይ ናቸው

የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን፥ ” አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራቸው አካባቢዎች የሚገኙ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለከፋ የምግብና የመድሃኒት ችግር በመዳረጋቸው የበርካታ ዜጎች ሕይወት እያለፈ ነው ” ሲል አሳወቀ።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ሕወሓት በወረራቸው አካባቢዎች በችግር ላይ ለሚገኙ ዜጎች የመድሃኒትና ምግብ ድጋፍ እንዲያቀርቡ ተደጋጋሚ ጥሪ ቢቀርብላቸውም ድጋፉን አላቀረቡም፡፡ በዚህም ምክንያት በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ከ5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለከፋ የምግብና የመድሃኒት ችግር በመዳረጋቸው የበርካታ ዜጎች ሕይወት እያለፈ መሆኑን ኮሚሽኑ አሳውቋል።

በዋግኸምራ እና ሌሎች አካባቢዎች በርካታ ማኅበረሰብ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆኑ በሴፍትኔት ፕሮግራም ይረዳ ነበር ፤ ቡድኑ አካባቢዎችን ከወረረበት ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ምንም ዓይነት የምግብና የመድሃኒት አቅርቦት የለም። በዋግኸምራ፣ በመቄትና በሌሎችም ቦታዎች እየተገኙ ባሉ መረጃዎች በርካታ ወገኖች በረሃብና በመድሃኒት እጦት ሕይወታቸው እያለፈ መሆኑን የሚያመላክቱ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በትግራይ ሕጻናት ለምግብ ዕጥረት ተጋልጠዋል

የትግራይ ጤና ቢሮ ባለፉት ወራት ባካሄደው ጥናት ከአንድ መቶ በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በምግብ እጥረት ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉን ይፋ ማድረጉን ከመቀሌ የጀርመን ሬዲዮ ዘጋቢ ዜና አመልክቷል። በምግብ እጥረት የተጎዱ በርካታ ሕጻናትም መቐለ በሚገኘው ዓይደር ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና መከታተላቸውን እና እየተከታተሉ መሆኑን የሆስፒታሉ ጤና ባለሙያዎች እንደገለጹለት አመልክቷል።

ዜናዎቹ ከተለያዩ ሚዲያዎች የተወሰዱ ናቸው

Exit mobile version