Site icon ETHIO12.COM

የአሜሪካን ዓለም ዓቀፍ ተራድኦ ድርጅት USAID የሰሞኑን ተናዳፊነቱን ትቶ ለስለስ ያለ መግለጫ ሰጥቷል

ሰራተኞቹን በሙሉ ከኢትዮጵያ ለማስወጣት ዝግጅቱን አጠናቆ የመጨረሻውን ውሳኔ ከነጩ ቤተመንግስት እየጠበቀ ያለው USAID ዛሬ ያወጣው መግለጫ የአቋም ለውጥ ይሆን? ድርጅቱ ከኢትዮጵያ እንደሚወጣ ዳይሬክተሯ ሰሞኑን በገደምዳሜ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የአሜሪካንን ዋጋና ጥቅም እንዲያውቁት በሚል ድርጅቱን ከኢትዮጵያ ነቅሎ ማውጣት ይኖርብናል ማለቷን ሰምተናል።

ዛሬ እርዳታ መስጠታችንን እንቀጥላለን የሚል መግለጫ በድርጅቱ የተሰጠው ምክንያቱ ምን ይሆን ታዲያ? ሰሞኑን አከታትሎ ሲያሟርትብንና ዜጎቹ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ በማሳሰብ ሽብር ሲፈጥር የከረመው የአሜሪካው ኤምባሲም ስራችንን ቀጥለናል ሲል ገልጿል።

ይህ የአቋም ለውጥ የመጣው ምናልባት በአራት ምክንያቶች ሊሆን ይችላል። አንደኛው በአሜሪካን ጫናና ማስፈራሪያ የሚሰበር የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ መንግስት እንደሌለ የነጩ ቤተመንግስት ሰዎች ፈትነው፣ ሞክረው፣ አይተው በማረጋገጣቸው ይሆናል።

ሁለተኛው የጦር ሜዳው ወቅታዊ ሁኔታ ለአሜሪካን እንደጠበቀችውና እንዳቀደችው ባለመሆኑ አካሄዷን መቀየር ግዴታ ሆኖ ስላገኘች እንደሆነም ይገመታል። ሶስተኛው የትላንቱ መሬት አርድ የኢትዮጵያውያንና የኤርትራውያን ተቃውሞ ሊሆን ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ትዕይንተ ህዝብ የሚኖረውን ተጽዕኖ አሜሪካኖቹ በቀላሉ የሚያዩት አይደለም። ሌላው የኢትዮጵያ መንግስት ዛሬ በጠዋቱ ያወጣው ኮስተር፣ መረር ያለ መግለጫም ለUSAID የዛሬ መግለጫ መውጣት ምክንያት እንደሚሆን መገመቱ ያስኬዳል።

የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት የዛሬ መግለጫ በእርዳታ ስም ፖለቲካችንን መፈትፈት አትችሉም ዓይነት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፈ ነው። በእርግጥ እንዲህ መቆጣት ተገቢና አስፈላጊ ነው። እንደውም ዘግይቷል።

ኢትዮጵያ እየሆነባት ባለው የምዕራባውያን አይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት ብትቆጣና ብታስጠነቅቅ አይፈረድባትም። ከመቆጣት ባለፈም ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎችን እስከመውሰድም መድረስ እንዳለባት ይታመናል። የእነሱ ነገር ለከት ያጣ ሆኗል። ንቀት ድፍረታቸው ቀዩን መስመር አልፏል። ዝምታችንን ደግሞ ከፍርሃት ቆጥረው እናታችን ላይ ሊወጡ ደርሰዋል።

በመናገር የምናጣው ካለም ኪሳራውን መቀበሉ ይሻላል። እናም የዛሬው መግለጫ ቢያንስ ቁጣችንን ያሳውቃቸዋል ። ልካችንን አሳይተን ልካቸውን እንዲያውቁት ያደርጋል። የUSAID የዛሬው አቋም የኢትዮጵያ መንግስት ማስጠንቀቂያን ተከትሎ የተለወጠ ይሆናል የሚል ግምት መስጠት ይቻላል።

በነገራችን ላይ የዓርብ ሌሊቱ የመቀሌ ድሮን ጥቃት በህወሀት መንደር የፈጠረው መደናገጥ ለምን ይሆን? ተባራሪ ወሬዎችን ገታ አድርጎ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ የደረሰውን ነገር ማጣራትና ህዝብ እንዲያውቀው መደረግ ቢችል ጥሩ ነው።

የውጭ ጋዜጠኞች ስለጉዳይ በቲውተር ላይ እየጻፉ ነው። ጥቃቱ በደረሰበት አከባቢ ሰው እንዳይንቀሳቀስ መዘጋቱን በመጥቀስ የደረሰው ጉዳት ምን ሊሆን ይችላል ሲሉ እየጠየቁም ነው።

ከተንቤን ዋሻ ወዲህ ከእይታ ተሰውሮ የነበረው የህወሀት ምክትል ሊቀመንበር ዓለም ገብረዋህድ ድንገት ዛሬ ይፋዊ በሆነ መድረክ ላይ ታይቷል መባሉም ያለምክንያት አይደለም። የሚሰጡ መላምቶችን በርክተዋል። የዓርብ ሌሊቷ ድሮን ህወሀትን ጉድ አድርጋ ይሆን?

እንበርታ!

Messay Mekonnen

Exit mobile version