Site icon ETHIO12.COM

ከሽብር ዘመቻ ጋር በተያያዘ – መንግስት የአሜሪካ ኤምባሲ እንደሚዘጋ አሳሰበ፤ አፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ማብራሪያ ተጠየቀ

የአሜሪካ ኤምባሲ ይሰነዘራል ያለውን ጥቃት ዘርዝሮ ያሰራጨው ዜና ሕዝብና መንግስትን ክፉኛ አስቆጥቷል። የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ” ከፈለጋችሁ መንገዱ ክፍት ነው” በቀጥታ መልዕክት ያስተላለፉት ለአሜሪካ ኤምባሲ ነው። በሌላ በኩል የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በቅጥር ግቢው ውስጥ ስለተፈጠረው ግርግር ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቋል።

በትናንትናው ዕለት ኤንባሲው ለትህነግ ድጋፍ በሚሰጥ መልኩ ያሰራጨው የሽብር ዝግጅት መረጃ “አሸባሪ፣ አሳፋሪና ሃላፊነት የጎደለው ” ሲል በግልጽ የተቸው የመንግስት ኮሙኒከሽን አገልግሎት ” የአሜሪካ መንግስትም ሆነ ኤምባሲው ከዚህ ተግባሩ እንዲቆጠቡ” ብሏል። በዲፕሎማሲ ቋንቋ ምን አልባትም ኤንዳሲውን ለመዝጋት እንደሚገደድ ምልክት መስጠቱን ጉዳዩን የሚከታተሉ አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ሕዝብ በአሜሪካና እንግሊዝ ኤምባሲ ደጅ በመገኘት ” እጃችሁን አንሱልን፣ ተዉን” ሲሉ በሰላማዊ መንገድ የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰምተዋል። አሜሪካ ስጋት ካለባት ጠቅልላ ከአገር እንድትወጣም ጠይቀዋል። ሰልፈኞቹ አሜሪካ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ከመግባት እንድትቆጠብ ፣ ጣልቃ ገብነቱ ኢዴሞክራሳዊ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ አንደራደርም፣ ሐሰተኛ መረጃን የሚያሰሙ የሚዲያ አካላት ከድርጊታቸው ይቆጠቡ ሲሉ ጠይቀዋል።

ደራሲ ገስጥ ተጫኔ የደርግ ዘመን የወቅቱ የፕሮፓጋንዳ ሃላፊ የነበሩትና “ነበር” የተሰኘውን መጽሃፍ ደራሲ ትህነግ በዛን ወቅት በተመሳሳይ በውጭ ሃይሎች በሳተላይትና በልዩ ድጋፍ ይደረግለት እንደነበር፣ ዛሬ እንደሚያደርገው ሰርጎ ገቦችን አስቀድሞ በማስረግ ሰላማዊ ዜጎችን እያሸበረ አካባቢዎችን ይይዝ እንደነበር አስታውሰው ሕዝብ አንድ ሆኖ በመረጃ በመቅደም ሊካሽፍ እንደሚገባ ለኢቲቪ አስታውቀዋል። አያይዘውም ዛሬ ወታቱና ሕዝብ በአንድነት መነሳቱ እንዳስቀናቸው አስታውቀዋል።

የተለያዩ አገራት ኤምባሲዎች ዜጎቻቸውን ለማውጣት ያደረጉት የዛሬው ሙከራ ትህነግን ለመደገፍ እስካሁን የሄዱበት ርቀት ውጤት አልባ እንደሆነ ሲገባቸው ሀሳባቸውን መቀየራቸውን መንግስት በመግለጫው አስታውቋል።በዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት የሚደረገው ሙከራ ፍጹም ስህተትና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ በምግለጫው ተገልጿል፡፡

የአሜሪካ ኤምባሲ እንደዚህ ዓይነት መግለጫ ከማውጣት እንዲቆጠብ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ደሲሳ ያሳሰቡትም ከላይ በተባለው ምክንያት ሲሆን፣ ኤምባሲው ሌላ ተግባሩን ትቶ በየቀኑ አዲስ አበባንና ነዋሪዎቹን የሚያሸብር መረጃ ማሰራጨት ላይ መጠመዱ መንግስትን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን የሚወዱ አገራትንም ቅር አሰኝቷል።

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በአዲስ አበባ የሚገኙ ኤምባሲዎችን የማስፈራራት ስራ ከመስራት እንዲቆጠቡም በሰጠው መግለጫ የአፍሪካ ህብረትን፣ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆነ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ ኤምባሲው በጎንዮሽም ግፊትና ጫና እያደረገ መሆኑ ተመልክቷል። ይህ ሁሉ የሆነው አዲስ አበባ ሊገባ 30 ኪሎሜትር ቀረው የተባለው ትህነግ በተባለው ቁመና ላይ ባለመገኘቱና በግንባር ያለው ሁኔታ ባልተተበቀ ፍጥነት መቀየሩ ያስከተለው ቅሬታ እንደሆነም ተመልክቷል።

በተመሳሳይ ዜና የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በቅጥር ግቢው ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ ማብራሪያ እንዲሰጥ ተጠይቋል። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በተባበሩት መንግስታት አፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ ስለተፈጠረው ሁኔታ ኮሚሽኑን ማብራሪያ እንዲሰጠው መጠየቁን የዘገበው ዋልታ ነው።

በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በከተማዋ ረብሻ መፈጠሩንና የኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ እንደታወከ በማስመሰል የተቀነባበረ የቪዲዮ ምስል ዛሬ ከማለዳው ጀምሮ የማህበራዊ ትስስር ገጾች መነጋገሪያ ሆኖ ውሏል፡፡በጉዳዩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ጄላን አብዲ ሁኔታውን ኮሚሽናቸው እየተከታተለው መሆኑንና የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ማብራሪያ እንዲሰጥ መጠየቁን ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ተናግረዋል።

እንደ አሜሪካ ኤምባሲ ያሉና ሚዛን የሳተ አቋም እያራመዱ ያሉ አንዳንድ ተቋማት በአዲስ አበባ የሽብር ጥቃት ሊፈፀም ይችላል በሚል የበሬ ወለደ የውሸት ወሬ ሰራተኞቻቸው ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ እያስፈራሩ ይገኛሉ።ዛሬ በድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተሰራው የሁከት ድራማም የዚህ የውሸት ፕሮፖጋንዳ መጠቀሚያ አንዱ አካል ሳይሆን እንዳልቀረ ብዙዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡የፌደራሉ መንግሥት የአሜሪካ ኤምባሲ ሽብር ፈጣሪ መግለጫዎችን ከማውጣት እንዲቆጠብ ሲያሳስብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሚያሰጋ የሽብር ጥቃት የለም፤ ከፍተኛ ክትትልም እያደረግሁ ነው ብሏል።

የፊልም ትርኢቱን በቅርቡ ይፋ የሚደረግ ፊል ሲሉ ልክ እንደ አችር ማስተዋወቂያ ክሊፕ የተሰራ እንደሆን አድርገው የተሳለቁበት ብዙ ናቸው።

Exit mobile version