Site icon ETHIO12.COM

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው የሚኒስቴሮች ግብረ-ሀይል ስራውን በይፋ ጀምሯል

በሰሜን ኢትዮጵያ ባለው ግጭት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመመርመር የተቋቋመው የሚኒስቴሮች ግብረ-ሀይል ስራውን በይፋ ጀምሯል

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማስቻል እና ተጎጂዎችን መልሶ ለማቋቋም የሚኒሰቴሮች ግብረ-ሀይል ያቋቋመ መሆኑ ይታወቃል።

ይህ ግብረ-ሀይል በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና በተባበሩት መንግሰታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ቤት በጋራ በተደረገው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምርመራ ላይ የተመላከቱ ምክረ-ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የተጠቃለለ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሀ-ግብር በማጽደቅ ስራውን በይፋ ዛሬ (ህዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም) ጀምሯል።

ይህ ስትራቴጂ እና የድርጊት መርሀ-ግብር በግጭቱ ምክንያት የተፈጸሙ ሁሉንም ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚሸፍን ሲሆን መንግስት ከወሰደው የተናጠል ሰብዓዊ የተኩስ አቁም እርምጃ በኋላ በአፋር እና አማራ ክልል ተፈጸሙትንም ይመለከታል። ግብረ-ሀይሉ ስራውን በውጤታማነት ለማከናወን እንዲያስችለው የወንጀል ምርመራ እና ክስን፣ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳዮችን፣ የጾታዊ ጥቃቶችን እና የሀብት ማሰባሰብን አስመልክቶ ስራዎችን የሚያስተባበሩ አራት ኮሚቴዎችን አዋቅሯል።

እነዚህ ኮሚቴዎች እንደየቅደም ተከተላቸው በፍትህ ሚኒስቴር፣ በሰላም ሚኒስቴር፣ በሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር እና በገንዘብ ሚኒስቴር የሚመሩ ይሆናል። ከዚህ ጋር በተያያዘ የግብረ-ሀይሉን እና የተዋቀሩትን ኮሚቴዎች የቀን ተቀን ስራዎች ለማስተባበር፣ ለመከታተል እና ለማቀናጀት ይቻል ዘንድ ጽ/ቤት እንዲቋቋም ወስኗል።

ግብረ-ሀይሉ ለወንጀል ምርመራ እና ክስ ኮሚቴ የተፈጸሙ ጥሰቶችን አስመልከቶ ጠንካራ እና ግልጽነት ያለው የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ለማድረግ እንዲቻል አስፈላጊው የሞያ ነጻነት ያለው ልዩ የወታደራዊ እና መደበኛ ጥምር የወንጀል ምርመራ እና ክስ የስራ ክፍል በማቋቋም ስራ እንዲያስጀምር አቅጣጫ አስቀምጧል።

በተጨማሪም ግብረ-ሀይሉ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች ስራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ተጎጂን ማዕከል ያደረገ የአሰራር ስርዓትን እንዲከተሉ እና ትኩረታቸውም ተጎጂዎች እውነትን የማወቅ እና ፍትህ የማግኘት መብቶቻቸው አንዲከበሩ እንዲሁም አቅም በፈቀደ መጠን የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ እና ካሳ የሚያገኙበትን ስርዓት ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንዲያተኩሩ አቅጣጫ ተቀምጧል።

ግብረ-ሀይሉ ከዚህ በተጨማሪ የፍትህ ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግብረ-ሀይሉ የተጣለበትን ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይችል ዘንድ አግባብነት ካላቸው ሀገራዊ እና አለምአቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከአቅም ግንባታ ጋር የተያያዙ የቴክኒክ እርዳታ እና ድጋፍ እንዲገኝ ተገቢውን እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የስራ መመሪያ ሰጥቷል።

ግበረ-ሀይሉ የተጣለበትን ኃላፊነት አፈጻጸም አስመልከቶ ለህዝቡ ተከታታይነት ያላቸው ወቅታዊ መረጃዎችን የሚያቀርብ መሆኑንም አስታውቋል።

(ኢ ፕ ድ)

Exit mobile version