Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ህዝብ በአሸባሪው ሕወሓት የታሪክ ባለዕዳ እንጂ አትራፊ አይሆንም!

ሁሉም ነገር ፍጥረታዊ ጅማሬና ፍጻሜ አለው። ለዚህ የማይገዛ ምንም ዓይነት ህልውና የለም። ይህንን መገንዘብም ሆነ መገንዘብ አለመቻል እውነታውን ሊገዳደረውም ሆነ ሊለውጠው አይችልም። ከዚህ ይልቅ ላልተገባ ዋጋ መክፈልና ለተበላሸ ፍጻሜ ራስን የማዘጋጀት ያህል ሆኖ የሚታሰብ ነው።

በተለይም ያልተገቡ ጅማሬዎች የቱንም ያህል ውልደታቸውና ዕድገታቸው ፈጣንና ስኬታማ ሆነው ቢታዩም፤ የዘላለማዊነት መንፈስ የተጋሩ እስኪመስሉ አደባባዮችን ሞልተው ከፍ ያሉ ገዥ ድምፆች ቢመስሉም ፤ ፍጻሜያቸው ግን የክፉ ትውልድ ማስተማሪያ የህይወት ተሞክሮዎች ከመሆን አያልፍም።

ያልተገቡ ጅማሬዎች የቱንም ያህል የብዙዎችን ቀልብ ስበው፤ በብዙዎች ህይወት ውስጥ የህልውና መሰረት እስከ መሆን የደረሰ አቅም መግዛት ቢችሉም እንኳን፤ የተበላሸ ፍጥረታቸውን በብዙ መስዋዕትነት በመዋጀት ፍጻሜያቸውን ማስተካከልም ሆነ ማሳመር አይቻልም።

የአሸባሪው ሕወሓት እውነታም ከዚህ የተለየ አይደለም። የቡድኑ ፍጥረታዊ ጅማሬው የተበላሸ በመሆኑ በብዙ መስዋእትነት ስኬታማ እስኪመስል አራት ኪሎ ቤተመንግሥት ቢደርስም ፤ መንግሥት ሆኖ በተሟላ ቁመና ሀገርና ህዝብን ማገልገል የሚያስችል ስብእና መፍጠር አቅቶት ፍጻሚውን አፋጥኖታል።

ፍጥረታዊ ብልሹነቱ በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ሳይቀር እያንዳንዷን ቀን በስጋት እንዲያሳልፍ አድርጎታል፤ እያንዳንዷን ቀን ለማለፍ ሴራዎች ላይ መደገፍን ዋነኛ ምርጫው እንዲያደርግም አስገድዶታል። በዚህም ነገዎቹን ከሴራዎች በሚወለድ አቅም ላይ ተስፋ አድርጎ እንዲንቀሳቀስ ሆኗል።

ይህ መቼም ቢሆን እፎይታ ሊፈጥር የማይችል ፍጥረታዊ ብልሹነት ፤ አሸባሪው ሕወሓትን “ከስመ ነፃ አውጪነት “ ፍጹም ወደ ሆነ አሸባሪነት ለውጦታል። የቡድኑ የአሸባሪነት ደረጃም ከዚህ ቀደም ባልታየና ባልተሰማ መልኩ ሲኦል እስከ መግባት የሚያደርስ ድፍረትና መታወር እንዲላበስ አድርጎታል።

ከዚህ መታወሩ በመነሳትም በእውር ድንግዝግዝ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ግልጽ ጦርነት በማወጅ የሀገሪቱን ህልውና ስጋት ውስጥ የሚከት ተግባር ፈጽሟል። በዚህም የትግራን ህዝብ እንደ ህዝብ አደጋ ውስጥ ከትቶታል። በአገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ከፍ ያለ ታሪክ ያለውን ይህንን ህዝብ ባልተገቡ ትርክቶች የማንነቱ መሰረት ከሆነው የገዛ ታሪኩ ጋር እንዲጣላ አድርጎታል።

ይህ የቡድኑ ፍጥረታዊ ብልሹነት እወክለዋለሁ ለሚለው ለትግራይ ህዝብ ቀርቶ ለራሱ ህልውና አደጋ ሆኖ ፍጥረታዊ ሞቱን አፋጥኖታል። ይህን ለመረዳት ከሁሉም በላይ ያለፉትን ሦስት ዓመታት የቡድኑን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ በአግባቡ መመልከቱ በራሱ በቂና ከበቂ በላይ ነው።

ያለፉት ሦስት ዓመታት ለቡድኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ ራሱን በአግባቡ ተመልክቶ ፍጥረታዊ ብልሽቱን እንዲያስተካክል የተሻለ ዕድል የሰጡት ነበሩ ፤ ይሁንና ቡድኑ ዕድሉን እንደ መልካም አጋጣሚ ከመጠቀም ይልቅ ብልሹ ፍጥረቱ በፈጠረበት ያልተገባ እብሪት ሳይጠቀምባቸው ቀርቷል።

በአንድ በኩል ብልሹ ጅማሬው የፈጠረበትን ስጋት አሸንፎ ለመውጣት የሄደባቸው የሴራ መንገዶች ባስገኙለት ጊዜያዊ ድሎች ፍፁም መታመኑና መንገዱንም አልፋና ኦሜጋ አድርጎ መውሰዱ፤ እራሱን እንዲያርም የተሰጠውን ዕድል እንዳይጠቀምበት ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖበታል።

በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያን ህዝቦችንም ሆነ የትግራይን ህዝብ ከሴራው በታች አድርጎ ማየቱና ሴራውን አሸንፈው መውጣት የሚያስችል ያደገ ንቃተ ህሊና ባለቤት አይደሉም ብሎ መታመኑ፤ ለዚህም በዘመኑ በፈጠራቸው የህዝቦችን አንድነት የሚፈታተኑ ትርክቶች መታመኑ ያለ አዋቂ ሳሚ አድርጎ ሞቱን አፋጥኖታል።

በርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃተ ህሊና ቡድኑ እንደሚያስበው እንዳልሆነ ያለ አንድ የጥይት ድምፅ ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት መቀሌ እንዲከት በማድረግ በተጨባጭ አሳይቷል። ላለፉት 50 ዓመታት የዘራቸውን የጥፋት ትርክቶች ትርጉመ ቢስ በማድረግ ከፍ ባለ አንድነትና ወንድማማችነት እጅ ለእጅ ተያይዞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጅማሬ ውስጥ ገብቷል።
የትግራይ ህዝብም ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ የተለየ ዕጣ ፈንታ ስለሌለው፤ ከቡድኑ ፍጥረታዊ ብልሹነት ሊያተርፈው የሚችል አንዳችም በጎ ነገር እንደማይኖር ለመረዳት ጊዜው አልረፈደም። የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ሕወሓት የትናንት ያልተገቡ ጅማሬዎችም ሆነ፤ ዛሬ አደባባይ ከሞሉ የሽብር ተግባራቶች የታሪክ ባለ ዕዳ እንጂ አትራፊ አይሆንም!

ይህ ርዕሰ አንቀጽ የአዲስ ዘመን ህዳር 26 ቀን 2014 ዓ.ም ዕትም ነው

Exit mobile version