ETHIO12.COM

አሸባሪው ትሕነግ በአፆኪያ ገመዛ የጅምላ ግድያ መፈፀሙ ተገለፀ

አሸባሪው ትሕነግ በሰሜን ሸዋ ዞን አፆኪያ ገመዛ ወረዳ አንቦ ውሀ ቀበሌ ላይ የጅምላ ግድያ መፈፀሙን የሚያረጋግጥ መረጃና ማስረጃ ይፋ ሆነ። በጭፍጨፋው የአምስት ዓመት ሕጻንና የአዕምሮ በሽተኞች እንደሚገኙበት ተመልክቷል።

እስካሁን ባለው መረጃ 70 የሚደርሱ ንፁሀን (ከአምስት ዓመት ህፃን ጀምሮ አዛውንቶችና የአዕምሮ ታማሚ ሳይቀር) የጅምላ ግድያው ሰለባ እንደሆኑ ጭፍጨፋው ሲፈጸም ያዩ እማኞች አስታውቀዋል። የጅምላ ግድያው የተፈፀመው ኅዳር 24 ሲሆን ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችና ተጎጅዎች ዛሬም ድረስ እየሞቱ መሆኑን፣ እንዲሁም ወደ ቀብር ሲሄዱ የስፍራው የዋልታ ዘጋቢ በቦታው ሆኖ መመልከቱን በፊልም አስደግፎ ገልጿል።

በአንድ መቃብር ላይ ብቻ እስከ 51 የሚደርሱ የጅምላ ግድያ ሰለባዎች እንደተቀበሩ የቀበሌዋ ነዋሪ የአይን እማኞች ገልጸዋል። አካባቢው በወራሪው የሽብር ሃይል ስር በመሆኑ የተነሳ መትረፍ የሚችሉ እንኳን ቢኖሩ ወደ ህክምና ለመውሰድ አስቸጋሪ እንደነበርም አመልክተዋል። የሟቾች ቁጥር እስከ መቶና ከዚያ በላይ ሊደርስ እንደሚችል የጉዳቱ ሰለባ ቤተሰቦች ለዋልታ ተናግረዋል።

የጅምላ ግድያውን የፈፀመው የሽብር ቡድኑ ትራፊ በማህል ሜዳና ማጀቴ አካባቢ ድባቅ ሲመታ የፈረጠጠው ወራሪ እየተግተለተለ በሰሜን ሽዋ አፆኪያ ገመዛ ወረዳ አንቦ ውሀ ባለ ጫካ ለማለፍ ሞክሮ ነበር። የአካባቢው ሚሊሻ አላሳልፍ ብሎ እግር ለእግር እየተከተለ ሙትና ቁስለኛ ስላደረገው፣ከመደምሰስ የተረፈው የሽብር ቡድኑ ቅሬት በአንቦ ውሃ ቀበሌ ንፁሃን ላይ የበቀል ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ነዋሪዎቹ ለዋልታ ዘጋቢ ተናግረዋል።

አሸባሪው የትሕነግ ወራሪ ኃይል በማይካድራ፣ በጭና ተክለ ሀይማኖት፣ በአጋምሳ፣ በጋሊኮማና ሌሎችም የፈፀመውን የጅምላ ግድያ በአፆኪያ ገመዛ ወረዳ የአንቦ ውሀ ቀበሌ ላይ በመፈፀም ለሰው ልጀ ሁሉ ጠላትነቱን እንዳስመሰከረ ማሳየቱን ተመልክቷል። ዶክተር ዳንኤል የሚባሉት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር በዚህ ሁሉ ስፍራ የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ለምን ” የዘር ማጥፋት ወንጀል ነው” እንደማይለውና ይህን ላለማለት ምን መስፈርት እንደጎደለ አለማስታወቁ ጥያቄ ያስነሳ ነው።

Exit mobile version