ETHIO12.COM

ጤና ሚኒስትር “ደግፉኝ” ሲል ለወገን ጥሪ አቀረበ

በሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ለማቋቋምና መልሶ ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ጤና ሚኒስቴር የድጋፍ ጥሪ አቀረበ፡፡
ታኅሣሥ 06/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ጤና ሚኒስቴር በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ለማቋቋምና መልሶ ሥራ ለማስጀመር እንዲቻል ሁሉንአቀፍ የድጋፍ ጥሪ አቅርቧል፡፡
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ካደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት በተጨማሪ ሕዝብ የሚገለገልባቸውን የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የሕክምና ግብዓት ማከማቻ ተቋማትን እና ሌሎች ማኅበራዊ ተቋማት አውድሟል፡፡ የሕክምና መሳሪያዎችን እና ሌሎች ግብዓቶችንም ዘርፏል፡፡
በጤና ተቋማት ላይ የደረሰው ወድመት በተለይ ድጋፍ ለሚሹ ዜጎች የመሰረታዊ እና ድንገተኛ ሕክምና አግልግሎት አሰጣጥ በእጅጉ አስተጓጉሏል። እስካሁን ባለው መረጃ ከ2 ሺህ 700 በላይ የሚሆኑ የጤና ተቋማት አገልግሎት የማይሰጡ ሲሆን በአሁን ወቅት በመንግሥት ተደራሽ ያልሆኑ አከባቢዎች ሲካተቱ ዉድመት የደረሰባቸዉ ቁጥር ከዚህ እንደሚያሻቅብ ይጠበቃል ብሏል ጤና ሚኒስቴር።
አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድን በከፈተው ጦርነት በከፈተባቸው አካባቢዎች አቅራቢያ አገልግሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች እንዲጨናነቁ እና መደበኛ ከኾነዉ አቅማቸዉ በላይ አገልግሎት እንዲሰጡ አስገድዷል ነው ያለው ሚኒስቴሩ።
 
 
ለኅብረተሰቡ ቀጣይነት ያለዉ አገልግሎት ለመስጠት እንዲያስችል እና አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ኹሉንም ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ያሳተፈ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ጥሪ ማድረግና የመልሶ ማቋቋሚያ ሀብት ማሰባሰብ እጅጉን አስፈላጊ ኾኖ ተገኝቷል ብሏል፡፡
ጤና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት እና አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዚህ አደጋ ምላሽ ለመስጠት እንዲያግዝ ሁሉአቀፍ ድንገተኛ አደጋ የጤና ምላሽ ሥርዓት አቋቁሞ ዘርፈ ብዙ ርብርብ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጿል። በአሁኑ ወቅትም ይህን ፈታኝ የሆነ ተግዳሮት ለመግታት ዝርዝር ተግባር ያለው ስትራቴጂ በመንድፍ ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቀሰው ሚኒስቴሩ ከእነዚህም የመጀመሪያዉ እና በአሁኑ ወቅት እየተሠራበት ያለዉ የተዘረፉ እና ዉድመት የደረሰባቸዉን ጤና ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የመንግሥት ተቋማት ጋር በማጣመር ተቋማቱን መልሶ ማቋቋም እና ሥራ ማስጀመር መሆኑን አመላክቷል፡፡
አሁን ላይ ከውድመቱ ከፍተኛነትና የጤና ጉዳይ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑና ለማኅበረሰቡ የሚሰጠውን ጤና አገልግሎት በፍጥነት ለማስጀመር የተደራጀ ድጋፍ ከሁሉም አቅጣጫ ማሰባሰብ ከመቼዉም ጊዜ በላይ እና ከሁሉም በፊት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን አስታውቋል፡፡
አሁን ላይ የወደሙ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እና ሥራ ለማስጀመር እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚስፈልግ እንደሆነ ጤና ሚኒስቴር ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ግኝት ማረጋገጡ ተመላክቷል፡፡ ይህንን የሃብት ማሰባብሰብ እና ድጋፍ ሥራን ለማስተባበር ጤና ሚኒስቴር የባለሙያ ቡድን አቋቁሟል፤ በግለሰብም ኾነ በቡድን ድጋፍ ማድረግ ለሚፈልጉ ኹሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊ መረጃ እና ትብብር ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።
በሀገር ውስጥም ኾነ በዉጭ ሀገር ያሉ መላዉ ኢትዮጵያዊያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ የግሉ ዘርፍ፤ ለጋሽ ድርጅቶች፤ አጋር ድርጅቶች፤ ሲቪክ ማኅበራት፤ የሙያ ማኅበራት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት የወደሙ የጤና ተቋማት ማቋቋምና ሥራ ማስጀመር ጥሪ በመቀበል በሁሉም አይነት መስክ ድጋፍ እንዲያርጉ ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ድጋፍ ለማድረግ በኦንላይን ድረ ገጽ https://www.moh.gov.et/site/donations መጠቀም የሚቻል ሲሆን አስፈላጊውን ተጨማሪ መረጃም በኢሜይል አድራሻ moh@moh.gov.et , abnet.zeleke@moh.gov.et ማግኘት የሚቻል መሆኑን ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
Exit mobile version