Site icon ETHIO12.COM

ዘመቻ ለህብረ ብሔራዊ አንድነት አሸባሪው ሕወሓት ሙሉ ለሙሉ እስከሚደመሰስ ተጋግሎ ሊቀጥል ይገባል!

አገራችን በአገር ውስጥ እና በውጭ ኃይሎች የተሰነዘረባትን የተቀናጀ ጦርነት በድል እየተወጣች ትገኛለች፡፡ ይህን ተከትሎም አጥልቶባት የቆየው የስጋት ደመና ተገፍፏል፤ ከአስፈሪውና መስቀለኛው መንገድ ወጥታ በድል ጎዳና እየተጓዘች ነው፡፡ 

ከሀዲው ሕወሓት እሱ ካልገዛት በቀር ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የማይፈነቅለው ድንጋይ እንደሌለ ሲገልጽ በነበረው ልክ ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦል መውረድ ካለበት እንደሚወርድ በተደጋጋሚ ሲያረጋግጥ በነበረው ልክ ኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ ጦርነት ከፍቷል፡፡ ጦርነቱንም ከአማራ ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ብሎ የአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖችን እንዲሁም የአፋር ክልልን በመውረር ነው ያቀጣጠለው፡፡ በእዚህም በአማራና የአፋር ህዝብ ላይ ታሪክ ይቅር የማይለው ተዘርዝሮ የማያልቅ ግፍ ፈጽሟል፡፡

ይህ በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመ ግፍ ያስቆጣቸው የኢትዮጵያ መንግሥትና መላ ኢትዮጵያውያን በወሰዱት የተቀናጀ እርምጃ አከርካሪው ተመትቷል፡፡ ዘሎ በገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች ዘሎ መውጣት በማይችልበት መልኩ ከክልሎቹ እንዳይወጣ እየተደረገ ተቀጥቅጧል፡፡ በዚህም ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶበት ክልሎቹ ከቡድኑ ነጻ ወጥተዋል፡፡ ለወራት በስቃይ ውስጥ የቆዩት ህዝቦችም የነጻነት አየር ማግኘት እየቻሉ ነው፡፡ የቡድኑ የአራት ኪሎ ህልምም ቅዠት ሆኖበት ቀርቷል፡፡

የትህነግ ቅዠት እነዚህን ክልሎች ማጎሳቆል ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፤ ዋናው ተልዕኮው የጅቡቲን መስመር በመቁረጥ የመደራደር አቅሙን ማሳደግ ፣ አዲስ አበባን በመቆጣጠር አራት ኪሎ ቤተመንግሥት መግባት የነበረ እንደመሆኑ በቡድኑ ላይ ጀግኖች የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎችና መላ ኢትዮጵያውያን የተጎናጸፉት ድል ደማቅና ትርጉሙም በእጅጉ ብዙ ነው፡፡ 

የቡድኑ አቅም ምን ድረስ እንደሆነ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ በተካሄደ የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በሚገባ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት እና የኢትዮጵያውያንን ኃያልነት በዚያ ወሳኝ ዘመቻ ወቅት ቀምሶታል፡፡

ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንደሚባለው ከዚህ ምት ያልተማረው ትህነግ መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ አሻፈረኝ ብሎ ነው ሌላ ታሪክ ይቅር የማይለው ግፍ የፈጸመው፡፡ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ የትግራይና አፋር ክልሎች የተወሰኑ ዞኖችን በመውረር እጁ በግፍ ተጨመላለቀ፡፡ በተለይ የአማራ ክልል ህዝብን እንደ ህዝብ ለማጥፋትና ለማዋረድ ፣ ወደ ድህነት አረንቋ እንዲመለስ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት አድርጎ ነው ወረራውን የፈጸመው፡፡ 

በስልጣን ዘመኑ የቀበራቸውን አሉኝ የሚላቸውን የጦር መሳሪያዎች፣ የአጋሮቹን ምዕራባውያን ድጋፎች በተለይም ለሰብአዊ አገልግሎት መዋል ያለባቸውን ከባድ ተሽከርካሪዎችን ፣ የእርዳታ ምግብንና የሳተላይት መገናኛን ጨምሮ ለጦርነቱ በማዋል ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማውን ቀጣይ ዘመቻ ዋና ተግባር የጀመረው በእነዚሁ ክልሎች ነው፡፡ 

የክልሎቹን የተለያዩ ዞኖችንና ወረዳዎችን ወርሮ ንጹሃን ዜጎችን በአሰቃቂ ሁኔታ እየጨፈጨፈ በመግደል በጅምላ ቀብሯል፤ ታጣቂዎቹ ሴት ህጻናትና መነኮሳትን ጭምር በጦር መሳሪያ አስገድደው በቡድን ደፍረዋል፡፡ ጌጣ ጌጣቸውንና ጥሪታቸውን ቀምተዋል። ሊጥና ሽሮ በርበሬም ዘርፏል ፣ ቡድኑ ብዙ ሚሊዮኖችን አፈናቅሏል፤ ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ የመንግሥትና የግል የመሠረተ ልማት ተቋማትን ብሎም ኢንዱስትሪዎችን ዘርፏል፤ የተቀረውን ጥቅም እንዳይሰጥ አድርጎ ክፉ ጠላትነቱን በሚያስመሰክር ደረጃ አውድሟል፡፡ ከህጻናት ፣ ከአቅመ ደካሞች አፍ ነጥቆና የአርሶ አደሩን የኑሮ መሠረት የሆኑትን በሬዎች አርዶ በልቷል፤ ሞፈር ቀንበራቸውን ፈልጦ አንድዷል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችን፣ ትምህርት ቤቶችን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን የጅምላ መቃብር ስፍራ አድርጓል፡፡ ቡድኑ የፈጸመው ግፍ ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡

ከተባባሪዎቹ ምዕራባውያን ጋር በመሆን ሀሰተኛ መረጃዎችን በመፈብረክና በማሰራጨት የዓለም ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር አድርጓል፤ የኢትዮጵያ እውነት ትቢያ እንዲለብስ፣ የእሱና ተባባሪዎቹ አለም አቀፍ ተቋማትና ምእራባውያን ሀሰተኛ መረጃ በመላ ዓለም እንዲናኝ በማድረግ ኢትዮጵያን በፕሮፓጋንዳውና በዲፕሎማሲው መስክ ክፉኛ ወግቷል፡፡ 

ቡድኑ ይህን ሁሉ ሲያደርግ ዓላማው ኢትዮጵያን ማፍረስና በተለይ የአማራ ህዝብን ማዋረድና ወደ ድህነት አረንቋ መመለስ ነበር፡፡ በእርግጥም ብዙ ጥቃት ፈጽሟል፡፡ የፈጸማቸው ጥቃቶችና የሸረባቸው ሴራዎች ግን ሞቱን አጣድፈውለት፤ በመላ ኢትዮጵያውያን የተባበረ ክንድና በተቀናጀ ዘመቻ በአጭር ጊዜ እንደ እባብ ተቀጥቅጦ ህልሙ እንዲመከን ተደርጓል፡፡ 

በዚህ ድል ውስጥ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን በየተሰለፉበት ግንባር ሙሉ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ድሉ የእነሱ ሁለንተናዊ አንድነት እና የተናበበ ሥራ ውጤት ነው፡፡ በቡድኑ ግፍና ሴራ የተቆጡ ኢትዮጵያውያን የመንግሥታቸውን ጥሪ ተቀብለው በጦር ሜዳ ውሎ፣ በፕሮፓጋንዳና ዲፕሎማሲ ዘመቻ ፣ በደጀንነት በሀብት ማቅረብና በስንቅ ዝግጅት ያደረጉት ርብርብ ቡድኑ ወራት የፈጀበትን የወረራ ዘመቻ በ15 ቀናት የመከላከልና መልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመደምሰስ አስችሏል፡፡ ቡድኑ ከገባባቸው የአማራና አፋር ክልሎች እንዳይወጣ ተደርጎ እንደ አባብ ተቀጥቅጧል፡፡ ይህም ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ አድርሶበታል፡፡

ተቆርጠው የቀሩ የቡድኑ ታጣቂዎች በየደረሱበት በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይሎችና በማህበረሰቡ እርምጃ እየተወሰደባቸው ነው፤ እግሬ አውጪኝ ብሎ ወደ ትግራይ እየገባ ያለው ኃይልና መሪዎቹም ቢሆኑ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በቀር ከዚህ ፍትሃዊ ጦርነት በምንም መልኩ አያመልጡም፡፡ በቆፈሩት ጉድጓድ ይቀበራሉ፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ይህን ከሀዲና አሸባሪ ቡድን ከመደምሰስ የሚያቆማቸው ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር በዚህ ዘመቻም በድጋሚ ማየት ተችሏል፡፡ 

መላ ኢትዮጵያውያን አሸባሪው ሕወሓት የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ክፉ ጠላት መሆኑን አስቀድመው ቢያውቁም፣ በቅርቡ በተለይ በአማራና በአፋር ከልል የፈጸማቸው ግፎች፣ ሲታይ ደግሞ ይህን ቡድን ጨርሶ የመደምሰሱ ሥራ አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚኖርበት በሚገባ አመላክቷል፡፡

በእርግጥም ድላችን የሁለንተናዊ አንድነታችንና መናበባችን ውጤት ነው፡፡ ይህን ሁለንተናዊ አንድነትና መናበብ አሁንም አጠናክሮ በመቀጠል ቡድኑ ጠረኑም እንዳይቀር አድርጎ ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ የተያዘውን ዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት ዘመቻ ቡድኑ ሙሉ ለሙሉ እስከሚደመሰስ ድረስ ከነግለቱ ሊቀጥል ይገባል!

አዲስ ዘመን ታህሳስ 14 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version