Site icon ETHIO12.COM

“ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት ሃገራዊ ዉይይት”አቶ ሌንጮ ለታ

” ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት የምንችለዉ በትጥቅ ትግል ሳይሆን በበሰለና በሰለጠነ ዉይይት ብቻ ነዉ። “- አቶ ሌንጮ ለታ

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት የሚዘጋጀዉ 18ኛዉ ዙር የጉሚ በለል የዉይይት መድረክ ” የብሔራዊ ዉይይቱ አንኳር ጉዳዮችና ሃገራዊ ፋይዳዉ” በሚል ርዕስ ተካሄዷል።

ለዉይይት መድረኩ የተዘጋጀዉን የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት በኦሮሞ ፖለቲካ ዉስጥ ትልቅ ከበሬታ የሚሰጣቸዉ አንጋፋዉ ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ ሲሆኑ በሃገራዊ ወይይቱ አስፈላጊነትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዙሪያ አንኳር ነጥቦችን አንስተዋል።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መገንባት የሚቻለዉ በትጥቅ ትግል ሳይሆን በበሰለና በሰለጠነ ወይይት ብቻ ነዉ ያሉት አወያዩ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት ከጦርነት ይልቅ ሰላማዊ ወይይት ተመራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ሃገራዊ ዉይይቱ ለኦሮሞ ህዝብ በጣም አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት አወያዩ ሃገራዊ ዉይይቱ በርካታ ድምጾችና ፍላጎቶች የሚንጸባረቁበትና የሚሰሙበት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

እኩልነት በሌለበት አንድነትን መፍጠር አይችልም ያሉት አወያዩ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመፍጠር ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ራሳቸዉን የሚመለከቱባትን ኢትዮጵያን መገንባት ይገባል ብለዋል።

ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን በሂደት እንጂ በአንድ ጊዜ መገንባት አይቻልም ያሉት አቶ ሌንጮ ለታ እንከን የሌለበት ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን መፈለግ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነዉ ብለዋል።

አንዳንድ የዉይይቱ ተሳታፊዎችም ያለፉት ስርዓቶች ሲከተሉት የነበረዉ ፖለቲካዊ አስተሳሰብና ትርክት በሕዝቦች መካከል ልዩነት እንዲሰፋና አለመግባባት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

ያለፉት ስርዓቶች በህዝቡ መካከል ጥለዉ ያለፉትን የተዛቡና ተቀባይነት የሌላቸዉ ትርክቶችንና አስተሳሰቦችን በማረም ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት ሃገራዊ ዉይይቱ ትልቅ ድርሻ አለዉ ብለዋል።

ፖለቲከኞች: ጋዜጠኞች: አርቲስቶችና ምሁራን ለሃገራዊ ዉይይቱ ስኬት የድርሻቸዉን ሊወጡ እንደሚገባም ገልጸዋል።

ተሳታፊዎቹን ያወያዩት የኦሮሚያ ዳያስፖራ ዳይሬክተር አቶ አሚን ጁንዲ ሲሆኑ በዉይይት መድረኩ ላይ ታዋቂ የኦሮሞ ፖለቲከኞች: የሚዲያ አመራሮችና ጋዜጠኞች: አትሌቶች: አርቲስቶችና ሌሎች ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። via OBN

ወንድማገኝ አሰፋ

Exit mobile version