Site icon ETHIO12.COM

«ማደንዘዣ እወጋለሁ ብሎ የሬሳ ማድረቂያ መርፌ የሚወጋና ታካሚን በጥፊ የሚማታ የጤና ባለሙያን የሚያፈራ ትምህርት በቃ»

ከህክምናና ጤና ባለሙያዎች የሙያ ብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ በታካሚዎችና በህክምና አገልግሎት አሰጣጡ ላይ የሚታዩ ተግዳሮቶችን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሕክምናና የትምህርት ጥራት አግባብነት ምዘናና ማረጋገጫ ሥርዓት መዘርጋቱን የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን አስታወቀ። «ማደንዘዣ እወጋለሁ ብሎ የሬሳ ማድረቂያ መርፌ የሚወጋና ታካሚን በጥፊ የሚማታ የጤና ባለሙያን የምናፈራበት የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ከዚህ በኃላ ሊቆም ይገባል» ተባለ።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን በዘርፉ የሚታዩ ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ከጤና ሙያ ማህበራት ጋር በመሆን ሰባት የሙያ ስታንዳርዶችን ማዘጋጀቱን አስታዉቋል።

ከትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ያገኘነዉ መረጃ እንደሚያሳየዉ ከ55 የሚበልጡ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በተለያዩ የሙያ አይነቶች የህክምናና የጤና ትምህርት ይሰጣሉ።

ከ324 ከሚበልጡ የግል ትምህርት ተቋማት መካከል ደግሞ ከ100 የሚበልጡት በተመሳሳይ መልኩ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ይህንኑ የህክምናና የጤና ትምህርት ይሰጣሉ።

እነዚህ የመንግስትና የግል የትምህርት ተቋማት በየ አመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ባለሙያዎችን ቢያስመርቁም በየጤና ተቋማቱ የሚታየዉን የሕክምና አገልግሎት ችግር በዘላቂነት መቅረፍ አልቻሉም።

ከነዚህ የትምህርት ተቋማት የሚመረቁ ተማሪዎችም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የጤና ባለሙያ መሆን አለመቻላቸዉ የህክምናና ጤና ትምህርት አሰጣጥ ስርዓቱ ከፍተኛ ዕጥረት ያለበት መሆኑን በይፋ አረጋግጧል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር አንዷለም አድማሴ ማደንዘዣ እወጋለሁ ብሎ የሬሳ ማድረቂያ መርፌ የሚወጋና ታካሚን በጥፊ የሚማታ የጤና ባለሙያን የምናፈራበት የትምህርት አሰጣጥ ሂደት ከዚህ በኃላ ሊቆም ይገባል ይላሉ።

በህክምናና በጤና የሙያ ዘርፍ ተመርቀዉ ወደ ተለያዩ የአለም ሃገራት የሚሄዱ ተማሪዎችም ከሌሎች ሃገሮች አንጻር ተወዳዳሪና ብቁ የህክምና ባለሙያ መሆን አቅቷቸዉ ሌላ ስራ የሚሰሩበትና ሙያቸዉን የሚቀይሩበት አካሄድም ሊያከትም ይገባል ብለዋል።

ለዚህም ከኢትዮጵያ የህክምና ሙያ ማህበራትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ሰባት የህክምናና ጤና ሙያ ብቃት መለኪያ ወይም ስታንዳርድ አዘጋጅተናል ብለዋል።

የሙያ ብቃት መለኪያ የተዘጋጀላቸዉ የትምህርት ፕሮግራሞችም የሜዲካል ዶክተር: የአንስቴዢያ: የጤና መኮንን: የሜዲካል ላቦራቶሪ: የሚድ ዋይፍ: የነርሲንግና የፋርማሲ ፕሮግራሞች መሆናቸዉን ለOBN ተናግረዋል።

ከአሁን በፊት የነበሩ ችግሮችን እናስተካክል ብንል ፍርድ ቤቱም ማረሚያ ቤቱም አይበቃንም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የመንግስት: የግል ትምህርት ተቋማትና የህክምና ማህበራት ለትምህርት ጥራት ተገቢዉን ትኩረት ሰጥተዉ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

ብቁና ተወዳዳሪ የህክምና ባለሙያዎችን የሚያፈሩ ተቋማትን ደግሞ ዕዉቅና በመስጠት ልናበረታታቸዉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተግባር ይግዛዉ በበኩላቸዉ የህክምናና የጤና ትምህርት ተቋማትን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን ቁርጠኝነት ይጠይቃል ብለዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ከህክምና ማህበራት ጋር በመተባበር ያዘጋጀዉ የሙያ ብቃት ምዘናና የዕዉቅና አሰጣጥ ስርአትምጨከአሁን ቀደም የነበሩ ችግሮችን ከመቅረፍ ረገድ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

በጤና ሚኒስቴር የሰዉ ሃብት ልማት ዳይሬክተሩ አቶ አሰግድ ሳሙኤል ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የጤና ዘርፉ የሚፈልገዉን የተማረ የሰዉ ሃይል በብዛት ለማፍራት በአስር ቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ቢመድብም ዘርፉ የሚፈልገዉን የሙያ ብቃትና ጥራት ማረጋገጥ ግን አልተቻለም ብለዋል።

በባለስልጣኑ የተዘጋጀዉ የሙያ ብቃት መመዘኛና ማረጋገጫ ሥርዓት ግን በጤና ተቋማት ዉስጥ የሚታየዉን የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ችግር ከመቅረፍ አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል: ኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎችም በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል ብለዋል።

የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን ባዘጋጀዉ የህክምናና የጤና ሳይንስ ፕሮግራሞችና መመሪያዎች የብቃት ማረጋገጫ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙ ዩኒቨርስቲዎችም የመንግስትና የግል ትምህርት ተቋማት ለፕሮግራሞቹ ተፈጻሚነት የድርሻቸዉን ሊወጡ ይገባል ሲሉ ለOBN ተናግረዋል።

በትምህርት ጥራት ችግር የህክምናና የጤና ሙያ መነቀፍ የለበትም ያሉት ተሳታፊዎቹ የተለያዩ የህክምና ማህበራት ለጤናና ህክምና አገልግሎት መሻሻል የድርሻቸዉን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

ወንድማገኝ አሰፋ OMN

Exit mobile version