Site icon ETHIO12.COM

‹‹በብሔራዊ ምክክሩ በጥቃቅን ጉዳዮች ከመነታረክ ይልቅ በወሳኝ ጉዳዮች ተወያይቶ መታረቅ ያስፈልጋል›› በድሉ ዋቅጅራ – ዶ/ር

ህዝቡ በብሔራዊ ምክክሩ በጥቃቅን ጉዳዮች ከመነታረክ ይልቅ ያለመግባባት መነሻ በሆኑ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ለመታረቅ መዘጋጀት እንደሚገባው መምህር፣ ገጣሚና ደራሲ በድሉ ዋቅጅራ (ዶ/ር) አመለከቱ፡፡

ዶ/ር በድሉ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በብሔራዊ ምክክሩ በጥቃቅን ጉዳዮች ከመነታረክ ይልቅ በወሳኝ ጉዳዮች ተወያይቶ መታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ባለፉት 27 ዓመታት የጎሳ ፖለቲካ በአግባቡ ካለመያዙ የተነሳ የጋራ እሴቶች በእጅጉ ተሸርሽረዋል። በልዩነት ውስጥ የአንድነት መንፈስ ሊጠናከር ሲገባው ግለኝነት ጎልቶ በመውጣቱ ምክንያት የጋራ ጉዳዮች አደጋ ላይ ወድቀዋል ብለዋል፡፡

የጋራ ጉዳዮች በህዝቡ ዘንድ እኩል ተቀባይነትና የጋራ ግንዛቤ ባለመፈጠሩ እስከዛሬ የመነታረኪያ ምንጭ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡ 

ለአንድ አገር የመኖር ህልውና ወሳኝ የሆኑት እንደ ሰንደቅ ዓላማ፣ ህገመንግሥት፣ ታሪክና እሴቶች ባሉ የጋራ ጉዳዮች ላይ በህዝቡ ዘንድ የጋራ ስምምነት ባለመፈጠሩ በየጊዜው እየሰፋ የመጣው ልዩነትና አለመግባባት የግጭት መነሻ በመሆን ለመገፋፋትና ለመገዳደል ያበቃበት አጋጣሚ መከሰቱን ዶ/ር በድሉ አስታውሰዋል። 

የተለያየ ጥያቄ ያላቸው ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ያሉባት አገር ውስጥ በአንድ ጀምበር ሁሉንም ለምክክር ማቅረብ የማይቻልና የማይመከር ጉዳይ ቢሆንም፤ በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ግን ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡

ህዝቡ ብዙ የሚያነታርኩትና የሚያራርቁትን የጋራ ጉዳዮች በባለቤትነት ስሜት በውይይት እንዲያዳብር ያለምንም ገደብ መመካከሩ የግድ ይላል፣ ምክክሩ በመቻቻል፣ በቅንነትና በእውቀት መታጀብ እንደሚገባውም አሳስበዋል፡፡

ወደኋላ ያሉ ታሪኮችን በመቻቻል እንደየወቅቱ ሁኔታ ካልተስተናገዱና ውይይቱም በጥንቃቄ ካልተመራ ሌላ ገጽታ ስለሚይዝ ከሁሉም በላይ ለምክክሩ ስኬታማነት የምክክር ኮሚሽኑ ብስለትና ገለልተኝነት ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ 

ልዩነታቸውን በተገቢው ውይይት በማጥበብ የጋራ መግባባት ላይ የደረሱ እንደ ደቡብ አፍሪካና ሩዋንዳ ያሉ አገራት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እስከ ዛሬ የሚያነሱት ጥያቄ የለም፡፡ ውጤታማ ምክክር እንዴት እንደሚካሄድ ከአገራቱ ተሞክሮ ተወስዶ ከማንነት፣ ከህገመንግሥት፣ ከሰንደቅ ዓላማና ከታሪክ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችን በአግባቡ በመለየትና በማስተናገድ የኮሚሽኑ እንቅስቃሴ የአንበሳ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡

ባላቸው ተሞክሮ ብዙውን ጊዜ በአገራችን የሚቋቋሙ ኮሚሽኖች ስማቸውና ስራቸው ትልልቅ ሆነው ውጤታቸው ሲፈተሽ ሰዎቹ አዲስ ይምስሉ እንጂ በተጨባጭ የአንድ አካል ወገንተኛ በመሆናቸው ጥቁር ጠባሳ ጥለው አልፈዋል፡፡ ለሶስት ዓመታት ያህል ሊታሰብበት የተፈለገውና ኮሚሽን ማቋቋም ያስፈለገበት ምክንያት ለብሔራዊ ምክክሩ ተገቢ ትኩረት መሰጠቱን የሚያሳይ ጉዳይ በመሆኑ እንደ አቅዱ ውጤቱም አመርቂ መሆን አለበት ሲሉም ዶክተር በድሉ አሳስበዋል፡፡ 

እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ሰላማዊ፣ መተማመንና አንድነት የሰፈነባት የበለጸገች ኢትዮጵያ ለመገንባት የሁሉንም ሀሳብ የሚያስተናግድ ብሔራዊ ምክክር ብሎም እርቅ ማድረግ ይቅር የማይባል ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ዋቅሹም ፍቃዱ

አዲስ ዘመን ጥር 2/2014

Exit mobile version