Site icon ETHIO12.COM

ከ [አደባባዩ] ጀርባ

አደባባይ የሚለው ቃል የኦሮሚኛ ቃል መሆኑን ስንቶቻችሁ ታውቁ ይሆን? በአፋን ኦሮሞ:- አደ /Adda – ግንባር/ፊትለፊት ማለት ነው (ከተለያየ አቅጣጫ የሚወጡበት ሊገናኙበትና ሊታዩበት የሚተሙበት) ባባይ/በበይ/Babaayi – ደግሞ ከተለያየ አቅጣጫ የመጡ መንገዶች ለምሳሌ ከስቴድየም ከጊዮን ሆቴል ከ4 ኪሎ ከመገናኛ ከቦሌና ከመሿለኪያ.. አንድ ላይ ተገናኝተው የሚለያዩበት ቦታ እንደማለት ነው:: ይህ ለሁሉም አደባባዬች ይሰራል:: ልዩነትንም ያሳያል ማለት ነው::

ከዚህ የምንረዳው አደባባይ የሚለው ፅንሰ-ሃሳብ የወል የጋራ የመገናኛ የመተላለፊያና የብዝሃነትን እሳቤ በውስጡ የያዘ ሃሳብ መሆኑን ነው:: አደባባዩ በአንድነት ላይ የተመሠረተ ልዩነትንም ማሳያ ተምሳሌት ነው:: ልዩነት ደግሞ ጌጥና ውበት ነው እንጂ መለያየት ማለት አይደለም::

ያም ብቻ ሳይሆን አደባባይ ላይ ከየአቅጣጫው የመጣው ለረጅም ጊዜ በዘላቂነት ርስቴ ነው ብሎ ለዘለዓለም የሚቆምበትና የሚቆረብበት ቦታ ሳይሆን ሁሉም በየተራ ለተወሰነች ጊዜ ብቻ ተገናኝቶ ጉዳዩን ፈፅሞ የሚለያይበት/የሚተላለፍበት ጎዳና ነው:: ይህ ለደመራም ለኮንሰርትም ለአፍጥርም ለእሬቻም ለሩጫም ለልዩ ልዩ በዓላትም ለድጋፍና ለተቃውሞ ሰልፎችም ይሰራል::

ስለዚህ አደባባይ ስንል የህዝቦች ሁሉ የጋራ መጠቀሚያ ሃብት ነው እንጂ ለአዱ ተፈቅዶ ለሌላው የሚከለከል አይደለም ማለት ነው:: ምክንያቱ ደግሞ አደባባይ ስለሆነ:: አልያም አንዱ የሚቸረው ሌላው የሚነሳው ጉዳይ አይደለም::

ከአደባባዩ ጀርባ ያለው ጥያቄ ግን የልሙጣዊው አስተሳሰብን የእናታችን ተዋህዶ ሃይማኖት በማስመሰል የፓለቲካ ለምድና የ”ክህነት” ካባና አልብሶ በእጅ አዙር የጭፍለቃ እና የጠቅላይ አግላይ አስተሳሰብን የሚያራምድ ነው::

ይህ ሃይል ከዚህ በፊት ለረዥም ጊዜ በስመ ኢትዮጵያ እና አንድነት/አንዳይነትነት ስም በግልፅም ሆነ በስውር ብዙ መንገድ በመጓዝ በሌሎች ላይ የፈጠረው ጠንካራ የባህልና የቋንቋም ሆነ የሶሺዎ ፓለቲካል-ኢኮኖሚ የበላይነት (Hegemony) እንደነበረው ይታወቃል:: ይህን እውነታ ተቋማዊ ገፅታ ጭምር ይዞ ለዘመናት የቆየው የበላይነት አስተሳሰብና ተግባር ቅሪቱ አሁንም ቢኖርምና ለማንሰራራት ቢዳዳውም ላይመለስ ህልውናውን እንዳጣ ግን ጠንቅቆ ያውቃል::

ይሁንና ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ሁሉ የነበረውን የበላይነት ለማስቀጠል ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የአልሞት ባይ ተጋዳይነቱን ይፈራገጣል:: ይህ መፈራገጥ ደግሞ ከመላላጥ ውጪ ምንም አይጠቅምም:: ለሃገር ደግሞ ጠንቅ ነው:: አስተሳሰቡ ሃገራችንንም ጎድቷል ወደሃላም አስቀርቷል:: እየጎዳም ነው::

ይህ ሃይል “የሰው ውሃ-ልክ” እኔ ብቻነኝ: ጠቅላይ እኔ ብቻነኝ ሃገር እኔ ብቻነኝ ሃይማኖት እኔ ብቻ ነኝ… ወዘተ እያለ ይቃዣል:: በዚህም ለራሱ የሰጠው ግምትና ምስል መሬት ካለው እውነታ ጋር ግን የማይሄድ ያረጀና ያፈጀ ይልቁንም የሚጋጭና የሚጣረስ አጀንዳ ነው::

አሁን አሁን ደግሞ መሬቱም ፀሎቱም … ሁሉም የኛ እያለ ይጮሃል:: በአደባባዩ ሲዘፈንበትና አሸሸ-ገዳሜ ሲባልበት ትንፍሽ ሳይል ቆይቶ ለፀሎትና ለሰብአዊ እርዳታ ሲሆን ለምን ነሰረው? መልሱ አስተሳሰቡም ተግባሩም ፅንፈኛ ስለሆነ ነው::

የመሬቷን ነገር ግን አቤቤ ቱፋዎች እንዳይሰሙህ ዝም ብትል ሳይሻል አይቀርም:: አለበለዚያ ኦዲት ከተደረገ ያለአግባብ የያዝከው ወረራህ ይጋለጥና ቱሪስት ትሆናለህ ባሻዬ: ይህ ሃይል እኩልነት አይመቸውም:: እኩል ሁን ስትለው ያመዋል:: ዘራፍ ያዙኝ ልቀቁኝ ክብሬ የበላይነት ነው እያለ በድሮ በሬ ለማረስ ይፈልጋል:: ልብ አርጉ የተጠየቀው እኮ እኩልነት ብቻ ነው:: ከሌሎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ደግሞ እኩልነት ውዴታ ብቻ ሳይሆን መሠረታዊ ግዴታ ጭምር ነው:: ይህ አንዱ የሃገራችን ስሪት ስብራትና ብልሽት መሆኑ ልብ ይለዋል::

ይህ ሃይል ስታፈጥሩ ስታመልኩ ገቢ ስታሰባስቡ (ያውም በጦርነቱ ለተጎዱት) ለድጋፍ ወይም ለተቃውሞ ሰልፎች ስትወጡ ለግል ለመንግስትና መንግስታዊ ላልሆኑ ተቋማት የአደባባይ ላይ ዝግጅቶች… ወዘተ እኔን አስፈቅዱ ነው እያለ ያለው::

የኔ ቡራኬ ከሌለበት የተቀደሰ ሃሳብም ቢሆን ቦታ የለውም እኔ ከባረኩት ግን “የረከሰም” ዝግጅት ቢሆን አደባባዩን እፈቅዳለሁ እያለ ነው:: ይህ ደግሞ ያለፈበት አተያይ ነው:: የሞራል የእምነት የህግ የባህልና የሰብአዊነት ይዘትም ይጎድለዋል::

ይህ ሃይል በቀረርቶው በሙዚቃው በስነቃሉ በትውፊቱ በፊልሙ (ባይ ዘ ዌይ ፊልመኛም ነው) በስብከቱ በሃይማኖቱ… ወዘተ ስለእኩልነት ስለነፃነት ስለሰላም ሰለፍቅር ስለአብሮ መኖርና መቻቻል ስለቸርነት ስለቅንነት ባልንጀራን እንደራስ ስለመውደድ ብሎም ስለምድራዊው ሳይሆን ስለሰማያዊ ርስት ወዘተ… በቲዎሪ ያወራል እንጂ ተግባሩን አይኖረውም:: አያውቀውምም:: በሰፈሩም አልደረሰም::

ከመስቀሉ ጀርባ ቁማርተኞች እንዳሉ ሁሉ ከአደባባዩም ጀርባ ቁማርተኞች እንዳሉ መረዳት ተገቢ ነው:: ስለምህረትና ይቅርታ በንድፈ-ሃሳብ ብቻ ቢያስተምርም በተግባር ግን የሰሞኑ የእስረኞች መፈታት ለዚህ ሃይል አልተመቸውም:: በተለይ የ… መፈታት:: ለምን ይመስልሃል? እሱ የሚያስበው ልሙጥ ሃሳብ ስላልተሳካ ብቻ ነው:: በሌላ መንገድ ደግሞ ስለ ሃገራዊ ምክክርና መግባባት አስፈላጊነትን ጮክ ብሎ ይናገራል እንጂ ተግባሩን መስማት አይፈልግም:: ያመዋል:: ሞኖፓሊ አመሉ ስለነበር ነው::

ሲጠቃለል ህዝቡ ከአደባባዩ ጀርባ ያለው አስተሳሰብ ጨው የሌለው ልሙጥ ሽሮ መሆኑን በመረዳት በተለይ ደግሞ ወጣቱ በደፈናው ግግግግግርርርርር ከማለት ይልቅ በተረገጋጋና በሰከነ መንገድ ለልዩነት (diversity) ለእኩልነት (equality) እና ለአሳታፊ (inclusive) ዘመናዊ አስተሳሰቦች ራሱን ማዘጋጀትና ማነፅ ይገባዋል::

ባሻዬ በፊለፊትም ሆነ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ለግል ጥቅማቸው ብለው የሚነግዱ የረከሰ መንፈስ ያለባቸውን “መንፈሳዊም” ሆኑ ስጋዊ ርካሽ የውሸት ነጋዴዎችን ማክሰር ይቻላል::

የብዝሃ ባህል ቋንቋ ሃይማኖት እምነት ርዕዮት አስተሳሰብ … ወዘተ እናት ሃገር ኢትዮጵያንም መጠበቅ በእኩልነት የሚያምንና የሚኖር ዜጋ ግዴታም ጭምር ነው::

ያንጊዜ የጠቅላይ አግላይና ዘውደኛውና ዘውገኛው ልሙጣዊ ዋልታ ረገጡ-አስተሳሰብም ቦታ አጥቶ እስከወዲያኛው ይመክናል:: እኩልነትና ወዳጅነት ያብባል!

አደባባይ ለሁሉም!

በላይ ባይሳ

ጥር 5/ 2014 ዓ.ም

Exit mobile version