Site icon ETHIO12.COM

የባህል፣ የግብረገብና የማሕበራዊ ሚዲያው ቱማታ

መደላድል፤ 

“ቱማታ” የሚለው ነባር ቃል ለብዙዎቻችን ቤትኛ መሆኑ ባይዘነጋም ከሦስት ያህል የመዛግብተ ቃላት ፍቺዎቹ መካከል ለዚህ ጽሑፍ ዐውድ የተመረጠው አንዱ ድንጋጌ እንዲህ የሚል ነው፡- “ቱማታ፡- ፍጅት፣ መደበላለቅ፣ እርስ በእርሱ መደባደብ፣ ወይንም በጦር ጨበጣ መዋጋት።” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል። 

ለተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ብያኔው ጥሩ መደላድል ስለሆነ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ከባህል፣ ከግብረገብ እሴቶችና ከቴክኖሎጂው መሠረታዊ ጽንሰ ሃሳብ፤ በተለይም ከማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ጋር እያዛነቅን ደጋግመን እንጠቅሰዋለን።

 ወደ ጉዳያችን እንዝለቅ፤

በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖር ማንኛውም ዜጋ ስለ ባህሉ እሴቶችና ትሩፋቶች ተናገር ቢባል በኩራት፣ በድምቀትና በደስታ ተሞልቶ የሚገልጻቸው በርካታ ዝርዝሮች ሊኖሩት እንደሚችሉ መገመት አይከብድም። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው። ባህል ወሰን የለሽ፣ ዘርፈ ብዙ፣ ውስብስብ፣ የትም የሚገኝ፣ በሰብዓዊ ፍጡራን የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ዘር፣ ቀለም፣ ፆታ፣ ዕድሜ፣ የትምህርት ደረጃ ወዘተ. ሳይገድበው በማሕበረሰብ እሴትነቱ ከፍ ብሎ የሰው ልጆች ሁሉ የሚጋሩት የጋራ ጉዳይ ስለሆነ ነው። 

ባህል እውቀታችን፣ ልምዳችን፣ እምነታችን፣ አመለካከታችን፣ እሴታችን፣ ንፅረተ ዓለማችን (worldview)፣ በሕይወት ያሉና የሌሉ ታዋቂና የመልካም ሥነ ምግባር አርአያ ሰብ ተምሳሌቶች በንብርብርነት የሚፈጥሩት የሰብዓዊ ፍጡራን ሁሉ የጋራ ትሩፋትም ነው። ማንም ሰው ከፖለቲካ ገለልተኛ ነኝ ሊል ይችል ይሆናል፣ ከማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች፣ ከእምነትና ከአምልኮ ሥርዓቶችም ማፈንገጥና አሻፈረኝ ማለት ይቻል ይሆናል። አላርስም፣ አልነግድም፣ አልማርም ብሎ ለጊዜውም ቢሆን ከራስ ጋር ኩርፊያ መግጠምም ይቻላል።

ባህል አልባ ሆኜ መኖር እችላለሁ ብሎ መወሰን ግን በፍፁም የሚቻልም የሚሞከርም አይደለም። ባህል “ከነርቭ ሥርዓታችን ንዝረት” ጋር መመሳሰሉም ስለዚሁ ነው። ያለፈው ዘመን በዛሬ ውስጥ ህልው ሆኖ የሚኖረው በጽሑፍ ከቆዩልን የታሪክ ገጾችና ከሚዳሰሱ ቅርሶች በተሻለ ሁኔታ በባህል ውስጥ ነው።

የታሪክ ገጾች የሚመሰሉት በሙዚዬም ውስጥ እንደተቀመጡ ቅሪተ አካላት ነው፤ ባህል ግን እንደ እድሜ ባለጸጋው የቅዱስ መጽሐፉ ማቱሳላ “ሽበቱን አንዠርግጎና አስከብሮ” በመቶዎች ዓመታት ውስጥ “አንቱ እየተባለ” ሳይደበዝዝ ተከብሮ የመኖር ብቃት ያለው፤ ማሕበረሰቡም መልሶ የጋራ ያደረገው የራሱ ውርስ ውጤት ነው። 

ግብረገብም እንዲሁ አንድ ማሕበረሰብ በአሜንታና በይሁንታ የተቀበለው ለጋራ ሕይወት አኗኗር የሚጠቅም የውስጣዊ ሕግ መርህ ነው። መደበኛውና ውጫዊው ሕግ “አድርግ ወይንም አታድርግ” በሚሉ ሁለት አሳሪና አስገዳጅ ትዕዛዞች የሚመራ ሥርዓት ነው። ውጫዊውን ሕግ ያለማክበር ደረጃው ይለያይ እንጂ “ተገቢ” የሚሰኝ ቅጣት ያስከትላል። 

የግብረገብ ሕግጋት ግን ከባህልና ከማሕበረሰብ የጋራ ጥልቅ እሴቶች የሚመነጩ ስለሆነ የቅጣቱ ድንጋጌ የሚወሰነው በራስ ህሊናና በማሕበረሰብ ትዝብት፣ አክብሮት ወይንም ግሳጼ ፈራጅነት ነው። ማሕበረሰብ በግብረገብ የታነጸን ግለሰብ ያከብራል፣ በአንቱታም

ነዎሩ እየተባለለት ይመሰገናል። በአንጻሩም በማሕበረሰቡ ግብረገባዊ እሴቶች ያመጸ ዜጋ ከማሕበሩ ቁርኝት እንዲነጠል ይደረጋል። ግብረገብ፡- የሁለት ጥምር “ንጥረ ነገሮች ውጤት” ነው። አንድም ከሃይማኖት፤ ሁለትም ከማሕበረሰቡ “መልካም” እሴቶች። ይህ ማለት ግን ግብረገብና ሃይማኖት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ማለት አይደለም፤ በጭራሽ። በሚከተሉት የሃይማኖት ቀኖና የታነጹ መልካም ግብረገብ ያላቸው ግለሰቦች የመኖራቸውን ያህል በአንጻሩም ለሃይማኖት ቁብ ሳይሰጡ በሥነምግባራቸው ግን ከፍ ብለው የሚስተዋሉ ግለሰቦችም ቁጥር ቀላል የሚሰኝ አይደለም። 

ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ስለ ባህልና ስለ ግብረገብ ለመነጋገርና ለመወያየት የምንገደድባቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም ከብዙዎቹ መካከል በምሳሌነት ሊጠቀስ የሚገባው ቴክኖሎጂው ያጎናጸፈን የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን “በረከተ መርገምነት” ግን በዋነኛነት መታየት ያለበት አንገብጋቢ ጉዳይ ነው። ግዙፏ ዓለማችን ከዳር ዳር ተኮማትራ በመዳፋችን መጠን ያህል ጠባለች። 

ቀደም ባሉት ዓመታት “ዓለማችን እንደ አንድ መንደር ጠባለች” እየተባለ የሚገለጸው ዛሬ ዛሬ እውነታው መሽቶበት በተንቀሳቃሽ ስልኮቻችን መስፋፋት ምክንያት “ዓለም ከመዳፋችንም ጠባ ወደ ጣቶቻችን ተቃርባለች” ወደሚል እምነት ሽግግሩ ከፍ ብሏል። በዋነኛነት “ጣቶቻችንን ያሰለጠንንበት”፣ ሙሉ ስሜታችንን ያስገበርንበትና የዕለት አኗኗራችንን ዘይቤ ደርበን በመከናነብ የተሟሟቅንበት ዘመነ ግሎባላይዜሽን የወለዳቸው ሳይንሳዊ ሥልጣኔዎችና ቴክኖሎጂዎች በባህልና በግብረገብ ህልውናና ቀጣይነት ላይ እየፈጠሩ ያለው ተጽእኖ ዝም ተብሎ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን ቆም ብለን በአትኩሮት ልናጤነው እንደሚገባ ማስገንዘቡ አግባብም ተገቢም ነው። 

የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ እንቅስቃሴ ጥንትም የነበረ ዛሬም ሆነ ወደፊት የሚገታው የሌለ ክስተት ነው። በሰዎች እንቅስቃሴ ውስጥ መልካምም ይሁን ያልተገባ ተጽእኖ ከየባህሎቹ መኮረጅ ወይንም መዋስ ተፈጥሯዊ አካሄድ ነው። የራስን ባህልና የግብረገብ መርህ ከሌላው ባለ ባህል የተሻለ አድርጎ መከራከርና መሟገትም እንዲሁ አይቀሬ እውነታ ነው። 

የእንቅስቃሴዎቹ ዓይነቶች የተለያዩ ናቸው። ሰዎች በሀገራቸው ውስጥና ከሀገራቸው ውጭ በንግድ፣ በሃይማኖታዊ ጉዞ፣ በትምህርት፣ በጉብኝት፣ በማኅበራዊ ጉዳዮች፣ በስደት፣ ወዘተ መንስዔነት ከባህል ባህል መንቀሳቀሳቸው የነበረና ዛሬም ድረስ የሚተገበር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችልም ሊዘነጋ አይገባም።

በቴክኖሎጂው ፈጣን እንቅስቃሴ እየተደገፈ ያለውን ይህንን መሰሉን ተፈጥሯዊ የሰዎች ፈጣን እንቅስቃሴ ይበልጥ ጤናማና ውጤታማ ለማድረግና የአንዱን ባህል አንዱ አውቆ እንዲያከብር፣ በዚያ ማሕበረሰብ ውስጥ ሲገኝም ባዕድነት፣ መገለልና የባህል ግጭት (Culture shock) እንዳይገጥመው ዘመኑ በሚገባ አግዞታል፤ በዚህ አኳያ ቴክኖሎጂውን “ነዎሩ” ብሎ ማክበር ተገቢ ነው። በአንጻሩም “የእነ እከሌ ባህል ባህሌ ሆኗል፣ ግብረገባቸውም ማራኮኛል” እየተባለ የእፉኝት እንቁላል ማሕበረሰቡ ባጸደቀውና ለዘመናት ጠብቆ ባኖረው “ቅርጫት ውስጥ እንዲፈለፈል ማድረግ” አደጋውን ሊያከፋው ይችላል።

ይህ ማለት ግን ቀዳሚው ትውልድ ያቆየው ባህልና የግብረገብ ትሩፋቶች በሙሉ በዛሬው የእኛነት አኗኗር ሲመዘኑ ምናልባትም መቶ በመቶ ሚዛን የሚደፉ ናቸው ማለት እንዳይደለ ግን መረዳቱ መልካም ነው። 

ግብረገብንም በተመለከተ “ዘመኑ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ስለሆነ ባፈጀና ባረጀ ማሕበረሰባዊ እሴቶችና መርሆዎች መገዛት ተገቢ ሊሆን አይገባም” የሚሉ መሟገቻዎች መቅረባቸው ብቻም ሳይሆን “በስመ ግብረገብ በግለሰቦች መብትና ነፃ ፈቃድ ላይ እንደ ቋጥኝ የከበደ ሸክም ማሸከም አግባብ አይደለም” የሚሉ መከራከሪያዎችም በየቦታው ሲደመጡና በግራና በቀኝ ሲወነጨፉ በማድመጥ ቱማታው እያነወጠን መሆኑ የሚካድ አይደለም።

እንዲያም ቢሆን ግን በዘመን ወለዱ የማሕበራዊ ሚዲያ እየተኩራራን እኛ ባልተፈጠርንበት ዘመን የኋሊት እየተንደረደርንና “በቴክኖሎጂው የዕውቀት ዐይን ርግብ ተጀቡነን” ትውልዱ የተሸመነበትን ባህሎችና የግብረገብ መርሆዎች በጅምላ ማንኳሰሱና ማቃለሉ አግባብ ይሆናል ተብሎ አይታመንም።

ይህን መሰሉ አሉታዊ ምልከታ አለመተማመንን ስለሚፈጥር በአንድ ሀገር ሁለንተናዊ አቋም ላይ የሚያስከትለው ውጤት ዘንቦ የሚያባራ ብቻ ላይሆን ይችላል። ስለ ዘመን ወለዱ የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ብዙ ማለት ቢቻልም በዋነኛነት ግን በነባር አገራዊ ባህሎቻችንና በቅቡል ግብረገባዊ እሴቶቻችን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ በተመለከተ ኮስትር ብሎ መወያየቱ ጊዜው የሚጠይቀው መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ማመኑ አግባብነት ይኖረዋል።

ለዚህ እውነታ ማስረጃው ኃላፊነት በጎደላቸው የማሕበራዊ ሚዲያ ሜዳዎች ላይ እየተስተዋሉ ያሉትን ከጦርነት ያልተናነሱ የሽምቅ ቱማታዎችን ማስተዋሉ ብቻ በቂ ይሆናል። 

በበርካታ የአገራችን ባህሎች ውስጥ አንድን ግለሰብ ከግብረገብ ባፈነገጠ መልኩ በግላጭ መሳደብ ነውር ብቻ ሳይሆን ማሕበራዊ መገለልን የሚያስከትል ኢሥነምግባራዊ ድርጊት ጭምር ነው። በተለይም የዕድሜ አንጋፎችን፣ አዛውንቶችን፣ የሃይማኖት መምህራንን፣ ከፍ ያለ ሥልጣነ ክህነት ያላቸውንና በከፍተኛ የመንግሥት ስራዎች ላይ የተሰማሩ አንቱዎችን ቢሳሳቱ እንኳን ጨዋነት በተላበሰ ቋንቋ ከማረም ይልቅ ማዋረድ፣ ማንቋሸሽና ስማቸውን በሃሜት ለውሶ በአደባባይ ላይ እያሰጡ ማጥፋት ማሕበራዊ ቅጣት ብቻ ሳይሆን የፈጣሪንም ቁጣ እንደሚያስከትል ባህሎቻችንም ሆኑ እምነቶቻችን ሲያስተምሩን የኖሩት ዋና ርዕሰ ጉዳይ ነው። 

ይህ ሲባል ግን ስህተት በይሉኝታ ይሸሸግ፣ ጥፋትም ሳይኮነን ይታለፍ ማለት አይደለም። የዚህ ወቅት የአገራችን የማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም፤ የጠቃሚነቱ ጎኖች እንደተጠበቁ ሆነው፤ በአሉታዊ መልኩ ፈር መሳት ብቻ ሳይሆን የአገርን አንድነትና የሕዝቦችን አብሮነት ጭምር እየናደ እንደሆነ የምናስተውለው ነው።

በማሕበራዊ ሚዲያዎች ተጀቡኖና በሀሰት ስምና መታወቂያ ራስን ሸሽጎ የሚነዙት አሉባልታዎችና ክፋቶች እያስከፈሉን ያለው ዋጋ በቀላሉ የሚገመቱ አይደለም። ነባር የባህል ትሩፋቶቻችን በጥቂት “እሳት ጫሪ አሉባልተኞች” እንዳልነበረ ሆኖ ሲናድ፣ ቅቡልነት ያላቸው ማሕበራዊ የግብረገብ እሴቶች ሲሸረሸሩና የግለሰቦችና የተቋማት ስሞች በአሉባልታ ሲጎድፉና በውሸት ቅንብር እየተዘሩ ሕዝቡን ሲበክሉ ሃይ ባይ ጠፍቶ ቱማታው መካረሩ የት ወስዶ የት እንደሚያደርሰን ለመገመት አዳጋች ሆኖብናል። 

የቱማታው ዘመቻ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነም የነገይቱ አገራችንና ሕዝባችን ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰላሰሉ አይከፋም። በዚህ ጽሑፍ መንደርደሪያ ላይ “ቱማታ” የሚለውን ቃል ስንበይን ከዘረዘርናቸው መሠረታዊ እሳቤዎች መካካል “ፍጅት፣ መደበላለቅ፣ እርስ በእርሱ መደባደብ፣ ወይንም በጦር ጨበጣ መዋጋት” የሚሉትን ብያኔዎች በትክክል የምናስተውለው በባህል፣ በግብረገብና በማሕበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን መካከል በሚደረግ የአጥፍቶ መጥፋት ግብግብ ውስጥ ነው።

በሶሻል ሚዲያ የጨዋታ ሜዳ ውስጥ “ሰይጣናዊ መለያ” በለበሰ ድብቅ አጀንዳ “ቅዱስ የሚሰኝ” መልካም ተግባርን አንበርክኮ መርታት የተለመደ ተግባር ሆኗል። ምክንያታዊ ይሁንም አይሁን ፖለቲካው ሲፈጭ፣ ሲቦካና ሲጋገር መዋልና ማደር ዋነኛ የዘመኑ ፋሽን ሆኗል። “ምን ይሉኝ” ባይነት ጊዜው እንዳለፈበት እየተቆጠረ የ“ነበር” ክብሩ ሳይቀር አሻራው እስከ መደብዘዝ ደርሷል።

ትንሹን አተልቆ፣ የገዘፈውን አኮስሶ ፍርድ እየሰጡ መዋል የብዙዎች የዕለት ቀለብ ሆኗል። የብዙዎች ውሎ አምሽቶ ማን ምን አለ? ማንስ ስለምን ጻፈ ወይንም “ፖሰተ”? መባባል ከማለዳ ሰላምታ አስቀድሞ በእሽቅድምድም ሲተገበር ማስተዋል እንግዳ አይደለም።

“ባህሌ፣ ግብረገቤ፣ ሥነምግባሬ ወዘተ.” እያሉ በኩራት መናገር ሥሩ እየደረቀ በመሄድ ላይ ያለ ይመስላል። ችግሩ ዓለም አቀፍ ወረራ ይሁን እንጂ የእኛው ደዌ ግን ትንሽ ጠንከር ሳይል የቀረ አይመስልም። መንግሥት ራሱ ለሚያወጣቸው ሕጎች ፈጣን እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ዐይን አፋር ሲሆን እያየን ምላሻችን ትዝብት ብቻ ሆኗል። የሕግ አተገባበር ልምሻውም ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው። 

በዚሁ ጉዳይ የሃይማኖት አባቶች የ“ሥልጣነ ክህነታቸው” ምርኩዝ ከእጃቸው ላይ ወድቆ መቆዘምን የመረጡ ይመስላል። አንዳንዴ እነርሱ ራሳቸው የነገር ፍም በገል እያቀበሉ ምዕመኑ እንዲያጋግለው ሲያራግቡ መመልከት እንግዳችን አይደለም። 

የባህልና የግብረገብ ዐይኖች እምባ አቆርዝዘው ሲተክዙ፤ አዲሱ መጤ የማሕበራዊ ሚዲያ ፊት ግን በሀሰትና በይሉኝታ ቢስነት ቅባት ወዝቶ መመልከት የዘመናችን ወግ ሆኗል። ኢትዮጵያ ሆይ አንድ በይን ! ሰላም ይሁን።

(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)

 gechoseni@gmail.com

አዲስ ዘመን ጥር 21/2014

Exit mobile version