Site icon ETHIO12.COM

አማራ ክልል በድፍረት መነጋገር አለበት- “የአማራ ፖለቲካ ዛሬም እንደታመመ ነው!”

” የህግ የበላይነት መረጋገጥ የአማራን ህዝብ ሊጠቅመው ካልሆነ በስተቀር አንዳች ጉዳት አያስከትልበትም፡፡ በህግ የበላይነት እምነት እስካሳደርን ድረስ ሁሉም ነገር በአግባቡ ይስተናገዳል፡፡ መንግስትም የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ፤የህግ የበላይነትን በማስከበር ስም ያልተገባ ተግባር እንደማይፈጽም ማረጋጥ ይኖርበታል፡፡ እንደዚህ ከሆነ የአማራ ፖለቲካ በቶሎ ከህመሙ ሊፈወስ ይችላል፤ያለበለዝያ ፖለቲካዊ ህመሙ ተባብሶ የአማራን ህዝብ ከባድ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል፡፡ ፖለቲካዊ ህመሙ ከባድ ነው”

ፎቶ – በአማራ ክልል ምስኪኖች ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከተዘጋጀ ሪፖርት የተወሰደ። ዛሬም ህጋዊነትን በመቃወም በፋኖ ስም የሚሸቅጡ ይህን ዳግም ውርደት እየጋበዙ ነው። ከጽሁፉ ጋር ይዛመዳል በሚል ተጠቅመንበታል። አማራ ክልል በተወሰኑት ክፍሎች ላይ እርምጃ ወስዶ ህግ ካላስከበረ አደጋው የከፋ መሆኑንን የቹቹ አለባቸው ጽሁፍ ያሳያል

በቹቹ አለባቸው – ከማህበራዊ ገጹ የተቀዳ

2011 የፀደይ ወራት ላይ ‹የአማራ ፖለቲካ ታሟል› በሚል ርዕስ፣ አንድ መጣጥፍ ፅፌ ነበር፡፡ የህመሙ ቅርጽ ካልተለወጠ በስተቀር በይዘት ደረጃ እንዳለ ነው፡፡ በተለወጠ አካባቢ፣ የኃይል አሰላለፉ ተለዋዋጭ በሆነበት ሁኔታ ፖለቲካችን ባለበት መርገጡ አልፎም ህመሙ እየበረታበት መሄዱ ያሳስበኛል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ፤ ከመቸውም ጊዜ በላይ እጅግ አሳሳቢ ነው። ባልተቋጨ የህልውና ጦርነት ውስጥ ሆነን በአደጋው ልክ አብረን ለመቆም ተስኖናል፡፡ በየቀኑ አጀንዳ እየተፈበረከ ከስትራቴጂያዊ ጉዳዮቻችን ውጭ በጥቃቅን እንዴውም በግለሰባዊ ጉዳዮች እንጠመዳለን፤ የሕዝብ ህልውና አደጋ ውስጥ ገብቶ የግል ዝናና ክብር ያሳስበናል፡፡ ልብ የሚያደማው ነገር ደግሞ አካባቢን መሰረት ያደረገ ወደ እርስ በርስ መፋተግ ተመልሰን እየገባን መሆኑ ነው፡፡ ይህን መጠራጠር አይገባም።

ለዚህ ችግር እንደአንድ መንስዔ ሊወሰድ የሚችለው መዋቅራዊ ድክመት ነው። በተለይም ይህ ችግር ብልጽግና እንደገዥ ፓርቲ ሁለንተናዊ አመራርን ከማረጋገጥ ጋር የተያያዘ ችግር ስለመሆኑ የታመነ ነው፡፡ በዚህ በኩል ፖለቲካዊና ፀጥታዊ አመራርን ከማረጋገጥ ባሻገር የሕዝብን አቅም ለህልውና ጦርነቱ አሟጦ በመጠቀም ረገድ ወጥነት ያለው አመራር እየተመለከትን ነው ለማለት ይቸግራል፡፡ ከዞን ዞን የአደረጃጀት ክፍተቶች አልታዩም ማለት አይቻልም፡፡ በፀጥታ ተቋማት ግንባታ ላይ ራስ-በቅ ለመሆን የተሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ሆኖ በሁሉም ዘርፍ የሕዝብን አቅም ለፀረ-ወረራ የመጠቀም፣ ከአደረጃጀት የሚነሳ የማያቋርጥ ክትትልና ድጋፍ ላይ የሚቀረን ስራ ብዙ ነው፡፡

የዚህ ክፍተት ከተለያየ ዓላማና ፍላጎት በመነሳት (በሌሎች) በየዕለቱ በሚፈበረኩ አጀንዳዎች ሕዝብ፣ መዋቅሩ፣ አመራሩና የፖለቲካ ተዋንያን በተቃርኖ ተጠምደው ውለው ያድራሉ፡፡ የሀሳብም ሆነ የተግባር አንድነት እየተመናመነ በአንጻሩ የተቃርኖ አጀንዳዎች እዚህም እዚያም እየተበራከቱ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያው ደግሞ ሰሞኑን የምናስተውለው ውዥንብር አንዱ ማሳያ ነው። ትግሉ ከጥንተ-ጠላት የትግሬ ወራሪ ኃይል ጋር መሆኑ ቀርቶ፣ የጎንዮሽ ፍትጊያ ሆኖ፣ ዳግም ክፍፍል ውስጥ እየገባን ነው፡፡ የህልውና አደጋ ውስጥ የወደቀውን ሕዝባችንን እናንቃ፤ እናደራጅ እያልን፣ አንዳንዱ የህልውና ትግልና የሰፈር ብሽሽቅን በቅጡ መለየት አልችል ብሎ የአማራን ጉዳይ ‹እንዘጭ እንቦጭ› በሚያሰኝ ሁኔታ መጫዎቻ ሊያደርገው ይሞክራል፡፡ የህግ የበላይነት መከበር የአማራ ህዝብ መዳኛ መሆኑ ታምኖ የታደረ ሀቅ ሁኖ እያለ በዚህ ዙሪያ እንኳን መግባበት ተስኖን ሰንፈርስና ስንሰራ የምንውል ጉዶች ሁነናል፡፡

አንዳዱ ጉደኛ ደግሞ የግል ቂምና ቁርሾን የህልውና አደጋ በተደቀነበት ሕዝብ ትግል ስም አምጥቶ ሒሳብ ሊያወራርድ ይሞክራል፡፡ አንዳንዱም ትግሉን የግል ዝናና የኪሱ ማድለቢያ የማድረግ ዓላማ ይዞ፣ ‹ሞላ ጎደለ› በሚል የባንክ አካውንቱን አንጋጦ ሲመለከት ይውላል፡፡

በጥቅሉ የአማራ ፖለቲካ የሀሳብና የትግል መስመር ጥራት መጓደል ዳግም ገጥሞታል፡፡ የህልውና አደጋ የገጠመን አልመስል ብለናል፡፡ የትግሉ መስመር ፈሩን እየሳተ ወንድም በወንድሙ ላይ የሚያደባበት የጥፋት አዙሪት ይዞናል፡፡ ለድጋፍና ተቃውሞ የሀሳብ ጥራት መሆኑ ቀርቶ ወንዜነት መገለጫው ሆኗል፡፡ አካባቢን መሰረት አድርጎ የሚሰጥ ድጋፍና ተቃውሞ፣ ከወዲሁ ካልታረመ መዘዙ ዳግም የከፋ እንደሚሆን ልንጠራጠር አይገባም።

በድፍረት መነጋገር መጀመር አለብን። ዛሬ በውስጣችን የሚታዩ የነገር-ውጣሬ አጀንዳዎችን በግልጽ ተነጋግረን ማስተካከል ካልቻልን፣ አንድም በዚህ የህልውና ጦርነት ውስጥ አሸናፊ ሆነን መውጣት አንችልም፤ አንድም ደግሞ ነገ ወደማንወጣው መከራ ልንገባ እንችላለን። በዚህ ረገድ በአማራና በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችና ምሁራን ‹የት ላይ ነን?› የሚለውን የፖለቲካ ተጠየቅ መነሻ አድርገው በድፍረት መነጋገር ቢጀምሩ፣ ሁኔታዎችን ወደመስመር ለማስገባት ያስችላል። ፖለቲከኞችና ምሁራን በጥልቀት ራሳቸውን፣ ሕዝባቸውንና አገራቸውን መፈተሸ ከቻሉ፣ አክቲቪስቱ የነሱን መንገድ ለመከተል ሊደፋፈር ይችላል። በርግጥ አክቲቪስቱ የልሂቃኑ ፍላጎት ነጸብራቅ ነውና የአማራ ፖለቲከኞችና የዘርፍ ልሂቃኑ አውቆ ለመታረም ዕድል ካገኙ አክቲቪዝሙ ከተራ ብሽሽቅ ወጥቶ ወደስትራቴጂያዊ የአማራ ጉዳዮች ማማተሩ አይቀርም፡፡

ፖለቲካችንን የማርጋት አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይገባም! ኃይላችን የማሰባሰብ ጉዳይ ለነገ የማንለው የቤት ስራችን ነው፡፡

የአማራ ህዝብ ከረዥም መራራ ትግልና ከባድ መስዋትነት በኋላ እዚህ ደርሷል፡፡ ከፊት ለፊቱም መራር ተጋድሎ ይጠብቀዋል፡፡ አሁን ለደረሰበት የትግል ምዕራፍ ለመድረስ የተለያዩ የትግል ስልቶችን ተግባራዊ አድርጓል። በተለይም ስሜትና ቁጣ አዘል እንቅስቃሴና የትጥቅ ትግል ጭምር ዋነኞቹ የትግል ስልት ተደርገው ተተግብረዋል። እነዚህ የትግል ስልቶች ትህነግን ከማዕከል ፖለቲካ ለማስወገድ ሲባል መተግበርም ነበረባቸው። ከዚያ ተጋድሎ በኋላ ከሌሎች ወንድም ሕዝቦች ጋር በመተባበር ባመጣው የፖለቲካ ለውጥ የራሱን፣ የኢትዮጵያንና የቀጠናውን ፖለቲካዊ አሰላለፍ መቀየር ችሏል፡፡ ጥንተ-ጠላቱ በእብሪት የከፈተውን የጦር ወረራ በመመከት የበዛ ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ራሱንና ሀገርን ማዳን ችሏል፡፡ አሁንም ግን ዳገቱ ላይ ነው፡፡ አማራ እንደሕዝብ የተፈተነበት ዘመን ቢኖር ይህ ዘመን ነው፡፡ ከከረመብን የፖለቲካ ህመም በፍጥነት ማገገም ካልቻልን መጭው ጊዜ ካለፍንበት የከበደ ይሆናል፡፡ መውጫ በሩ ጽኑ ወንድማማችነት ነው፡፡ ከግለኝነት ይልቅ ሕዝባዊነት መዳኛችን ሊሆን ይገባል፡፡

ሰሞኑን የተከፈተው የ“ኢ-መደበኛ አደረጃት“ አጀንዳ አውዱን ስቶ ወዳልተፈለገ ጎዳና እዳይከተን እፈራለሁ፡፡ በርከት ያሉ ሰዎች አጀንዳውን በሜሪቱ ከማየት ይልቅ ለራሳቸው ዓላማ ማሳኪያ አድረገው ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ታዝቢያለሁ፡፡ እስከማውቀው ድረስ የክልሉ መንግስት በህልውና ዘመቻው ዋጋ ለከፈሉት ፋኖዎች እውቅና ሰጥቷል፤ ቀሪ ነገር ካለም በሂደት የሚስተካከል ነገረ ይኖራል ብየ አስባለሁ፤ለምሳሌ ሽልማት፡፡ ከዚህ ውጭ ፋኖን ውለታ ቢስ አድርጎ የማስቀረት ፍላጎት አለ ብየ አላምንም፤ ይህ ፍላጎት ካለ ሁላችን የምንታገለው አመለካከትና ተግባር ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ በአንድ ወሳኝ ነገር እንተማመን፡፡ ይሄውም የህግ የበላይነት መረጋገጥ የአማራን ህዝብ ሊጠቅመው ካልሆነ በስተቀር አንዳች ጉዳት አያስከትልበትም፡፡ በህግ የበላይነት እምነት እስካሳደርን ድረስ ሁሉም ነገር በአግባቡ ይስተናገዳል፡፡ መንግስትም የህግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት ሁሉ፤የህግ የበላይነትን በማስከበር ስም ያልተገባ ተግባር እንደማይፈጽም ማረጋጥ ይኖርበታል፡፡ እንደዚህ ከሆነ የአማራ ፖለቲካ በቶሎ ከህመሙ ሊፈወስ ይችላል፤ያለበለዝያ ፖለቲካዊ ህመሙ ተባብሶ የአማራን ህዝብ ከባድ ዋጋ ሊያስከፍለው ይችላል፡፡ ፖለቲካዊ ህመሙ ከባድ ነው!!!

በመጨረሻም የዐማራም ሆነ የኢትዮጵያ መዳኛው ተቋማዊነት ያለው የማያቋርጥ የፀጥታ ኃይል ግንባታ ነውና የ11ኛ ዙር ልዩ ሀይል ፖሊስ ምዝገባ በመጀመሩ ወጣቶች የአማራ ልዩ ኃይልን እንድትቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላችኋል፡፡

Exit mobile version