Site icon ETHIO12.COM

አቶ የሱፍ ለቢሮ ኪራይ የሚወጣውን አንድ ቢሊዮን ብር ለማስቀረት እየተሠራ መሆኑን አስታወቁ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየዓመቱ በሥሩ ለሚገኙ ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ቢሮ ኪራይ የሚያወጣውን አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ ለማስቀረት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የሱፍ ኢብራሒም እንዳስታወቁት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየዓመቱ በሥሩ ለሚገኙ ተቋማት የሚያወጣውን ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ወጪ ለማስቀረት እየሠራ ነው።

ዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ቢሮ ኪራይ የሚወጣውን ከፍተኛ ብር ወጪ ለማስቀረት ተቋማቱ የየራሳቸው ቢሮ እንዲኖራቸው ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው።

በከተማ አስተዳደር ደረጃ ካሉት 46 ተቋማት መካከል የራሳቸው መገልገያ ቢሮ ያላቸው 14ቱ ብቻ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ የሱፍ 32ቱ የራሳቸው መገልገያ ቢሮ ስለሌላቸው የሚገለገሉት በኪራይ ቢሮ መሆኑንና ለ32ቱ ብቻ ከተማ አስተዳደሩ በየዓመቱ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ማውጣቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በአጠቃላይ ለ569 ተቋማት ቢሮ ኪራይ በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ብር ወጪ እያወጣ መሆኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ የሱፍ ገልፀዋል።በቀጣይ አራት ዓመታት 32ቱን የዘርፍ መስሪያ ቤት ጨምሮ 569ኙም በከተማ አስተዳደሩ ሥር የሚገኙ ተቋማት የራሳቸው መገልገያ ቢሮ እንዲኖራቸው ለማስቻል የአንድ ማዕከል አገልግሎት መገንባት የሚያስችል 6 ነጥብ2 ሄክታር ቦታ ከከተማ አስተዳደሩ ተረክቧል።

አስፈላጊ የሆኑ የአማካሪ ዲዛይኖችና ዝግጅቶችም ተጠናቅቀዋል። ግንባታ ሥራውን የሚያከናው ፕሮጀክት ተለይቷል። የዚህን ፕሮጀክት ጨረታ ለማውጣት የሚያስችልም ቅድመ ዝግጅት እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ካሉት 11 ክፍለ ከተሞች የራሳቸው መገልገያ ቢሮ ያላቸው ስምንቱ ክፍለ ከተሞች መሆናቸውን ገልፀዋል።የልደታ እና የነፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ቢሮ በግንባታ ላይ መሆኑን ጠቁመው፤የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በኪራይ ያለ መሆኑንና የራሱ ቢሮ እንዲኖረው ለማስቻል በቀጣይ ዓመት ወደ ግንባታ እንደሚገባም አመልክተዋል።

‹‹የሚገነቡት ሕንፃዎች የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመስጠት ለአገልጋዩም ለተገልጋዩም ምቹ እንዲሆኑ ይፈለጋል›› ያሉት ኀላፊው የሕፃናት ማቆያ፣ ካፌ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና መስጫ፣ የመኪና ማቆሚያና ሌሎች ከሕንጻው ጋር ተያያዢነት ያላቸው ግንባታዎች በአስገዳጅ አዋጅ ታግዞ የሚሰራበት መሆኑንም ተናግረዋል።

ባለፈው ስድስት ወራትም 38 የሕፃናት ማቆያዎች፣ የ72 ተቋማት የአሽከርካሪ ማቆሚያዎች፣የ19 የመጀመሪያ ሕክምና መስጫ፣የ189 ተቋማት የሠራተኛ ካፍቴሪያ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም

Exit mobile version