Site icon ETHIO12.COM

“በማያባራ ስቃይና ሰቆቃ ውስጥ ላሉ ዜጎቻችን ፈጣን ምላሽ መንግስት እንዲሰጥ በጥብቅ እንጠይቃለን” ኢዜማ

በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ወረዳ 168 ንፁሀን ዜጎች በኦነግ ሸኔ ግድያ እንደተፈጸመባቸው መንግሥት አስታውቋል። ከእነዚህ ውስጥም 87 ሰዎች በጅምላ ተገድለው አስክሬናቸው መገኘቱ ታውቋል። 81 ሰዎችም በተለያዩ የወረዳው አካባቢዎች ተገድለው ተገኝተዋል። በኦሮሚያ ክልል እንዲህ ያሉ የጅምላ ግድያዎች የዕለት ተዕለት ተግባራት ከሆኑ ሰነባብተዋል። ዜጎች በገዛ ሀገራቸው በማንነታቸው ምክንያት በህይወት የመኖር እድል እየተነፈጋቸው ይገኛሉ፡፡ በማያባራ ስቃይ እና ሰቆቃ ውስጥ ላሉ ዜጎቻችን ፈጣን ምላሽ መንግስት እንዲሰጥ በጥብቅ እንጠይቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ) የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባሩ ሊሆን የሚገባው የዜጎችን ደኅንነትና ሰላም ማስጠበቅ ነው ብሎ በፅኑ የሚያምን ሲሆን፤ በተደጋጋሚ እንደሚታየው ግን ይህን ሃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ሳይችል ቀርቶ ንፁሃን ዜጎች ከቀያቸው እንዲፈናቃሉ ብሎም እንዲገደሉ ሆኗል፣ እየሆነም ነው፡፡ መሰል ድርጊቶች በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ መግለጫ ከመስጠት እና መፅናናትን ከመመኘት የዘለለ ተጨባጭ ስራ መስራት ያልቻለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስትም በክልሉ እየተፈፀሙ ላሉት አሰቃቂ ግድያዎች ተጠያቂነት አለበት፡፡ ሃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት እና የሚታየው ከፍተኛ ቸልተኝነት በመንግስት መዋቅር ውስጥ ተባባሪነትና ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ፍላጎት ያለመኖሩ ማሳያ ነው፡፡

የመንግስት የአስተዳደርና የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ግልፅነት ለህዝብ የሚሰጥ ችሮታ አይደለም፡፡ ህዝብ በገዛ ሀገሩ ላይ ምን እየተካሄደ መሆኑን የማወቅ መብት አለው፡፡ ይልቁንም ከህዝብ የተደበቀ መንግስት ብቻ የሚያውቀው «የተለየ ጉድ» በአገራችን ላይ አለ ብለን አናምንም፡፡ የኢትዮጵያ ዕድሎችና ፈተናዎች ሩቅና ስውር አይደሉም፡፡ በእዚህ ነባራዊ እውነታ ውስጥ ብንሆንም በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ ቦታዎች የፌደራል መንግስት እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሕግና ስርዓትን ለማስከበር የተቸገሩበትን ምክንያት በግልፅ ለህዝብ ሊያሳውቁ የሚገባ ሲሆን የተፈፀመውን እጅግ አሰቃቂ ጥቃት በተመለከተ የፈፃሚዎቹን እና የተጎጂዎችን ማንነት ለመለየት በገለልተኛ አካል አንዲጣራ እንጠይቃለን፡፡

ዜጎች መንግሥት ደህንነቴን አያስጠብቅልኝም ብለው ከደመደሙ ወደማያባራ ቀውስ እንደምናመራ ልብ ልንለው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም ዜጎቹንም ከመሰል ግድያ የመታደግና ደህንነታቸውንና ሰላማቸውን አስቀድሞ የማስጠበቅ ሥራ የራሱ የመንግሥት ድርሻ መሆኑን ተረድቶ አስፈላጊ የሚባለውን የቅድመ መከላከል ሥራ መሥራት ይገባዋል። ይህንን መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላትም ለፍርድ ሊቀርቡ ይገባል። የሟች ቤተሰቦችና ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎችም ተገቢ ካሳ እንዲያገኙ ጥሪ እናቀርባለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) መተኪያ የሌለው ውድ ህይወታቸውን ባጡት ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን ይገልፃል። ለሟች ቤተሰቦችና ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ)
የካቲት 1 ቀን፣2014

Exit mobile version