ኢዜማ አፈና፣ መፈናቀልና እገታ ባለስልጣናትን በህሊና፣ በሕግ፣ በሕዝብ እና በታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል አለ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በኦሮሚያ ክልል ውስጥ እለት ከእለት እየጨመረ የመጣው የንጹሐን ዜጎች መፈናቀል፣ እገታ፣ አፈና እና ግድያ በከፍተኛ ሁኔታ ያስጨንቀዋል፡፡ በተለይ እራሱን “የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት” እያለ የሚጠራው ኦነግ ሸኔ የተባለው የሽብር ቡድን በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ውድመት እና እንግልት ቀን በቀን እየተባባሰ መጥቷል፡፡

የተለያዩ ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን በሰላም በድርድር እና በውይይት ለመፍታት መሞከር ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ ላይ ግርታ ባይኖርም ለሰላም ነው እየተባለ ንጹሐን ዜጎች ላይ በጠራራ ጸሐይ እየደረሰ ያለው ቅጥ ያጣ አፈና፣ ግድያ፣ ግፍና ሰቆቃ ሊታገሱት ይገባል ማለት ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡

በጥቅምት ወር 2015 ዓ.ም. የተፈረመውን የፕሪቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ባወጣነው መግለጫ በተለያዩ አካባቢዎች ላይም ለሰላም ውይይትና ድርድር በር አንዲከፈት አሳስበን የነበረ ሲሆን ይህን ተከትሎም በጋምቤላ እና በቤኒሻንጉል ክልል የነበሩ ታጣቂዎች በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ እንደፈቱ ተዘግቧል፡፡

መንግሥትም የሰላም በሩን ከፍቶ በኦሮሚያ ክልል እየተንቀሳቀሰ ከሚገኘው ኦነግ ሸኔ ከሚለው አሸባሪ ቡድን ጋር ታንዛኒያ ላይ ሰላማዊ ውይይት እንደጀመረ ሲያሳወቅ ተስፋ አድረገን የነበረ ቢሆንም ከድርድሩ በኃላ የሽብር ቡድኑ ጥፋት እየባሰበት ሲመጣ እንጂ ሲቀንስ ወይም ጨርሶ ሲጠፋ አላስተዋልንም፡፡ ይህም ንጹሐን ዜጎች በገዛ ሀገራቸው ለአፈና እና ግድያ እየዳረጋቸው መደበኛ እለታዊ ሕይወታቸውን ተረጋግተው እንዳያከናውኑ እያደረጋቸው ነው፡፡

በመንግሥት በኩል የተለያዩ ምክንያቶችን በማቅረብ ቡድኑን ጨርሶ ለማጥፋት እንዳልተቻለ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለጉዳዩ ሲጠየቁ፤ የሸኔ የሽብር ቡድንን አስቸጋሪ አወቃቀር በመጥቀስ እርምጃ ለመውሰድም ኾነ ለመደራደር የሚመሩት መንግሥት መቸገሩን ሲገልፁ ሰንብተዋል፡፡

በዚህ ወቅት የሽብር ቡድኑ አባል ነን የሚሉ ታጣቂዎች በወለጋ ሁለት ዞኖች፣ በምዕራብ፣ ምስራቅ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ በሱሉልታ ወረዳ ቦቁ ጎልባ፤ ኤካ ጋጆና፤ ቦቁ ሁሩታ እና ሞዬ ጋጆ በሚባሉ ቀበሌዎች፤ በዝዋይ፣ መቂ፣ ሰዴን ሶዶ ወረዳ፣ የአዳ ባርጋ ወረዳ፣ ኩዩ ወረዳ፣ ገርበ ጉራቻ፣ ዋጫሌ ወረዳ፣ በአዳማ፣ በመተሀራ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በአርሲ ዞን፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ በሚገኙ ቦታዎች ላይ ንጿሃን ዜጎችን እያገተ እና እየገደለ ፣ የትራንስፖርት እና እቃ ማጓጓዣ መኪና ሹፌሮችን እያፈነ እና በርካታ የጸጥታ ስጋት የሆኑ ተግባራት እየፈጸመ እንዳሻው እየተንቀሳቀሰ የዜጎችን ህልውና እየተፈታተነ፣ ሀገራችንንም የምድር ሲኦል እያደረገ ነው፡፡ በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ጭምር የሚንቀሳቀሰው ኦነግ ሸኔ፤ ኢሞራላዊ በኾነ መንገድ የሃይማኖት ሥፍራዎችን ሳይቀር እያዋረደ ነው።

See also  አል-ሲሲ በቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያን በልማት ማገዝ እንደሚፈልጉ አስታወቁ፣ ለ"ትብብር" ጥሪ አቀረቡ

ይህንን የሚያክል የሀገር ህልውና ችግር በየእለቱ እንደተራ ዜና እየሰሙ ማለፍ የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን የሚመለከታችሁ የመንግሥት የጸጥታ መዋቅሮች ልብ ልትሉት ይገባል፡፡ በምንም መልኩ የዜጎች በሕይወት የመኖር ዋስትና በመንደር ሽፍቶች ሲገፈፍ በቸልታ ሊታለፍ አይችልም፡፡

መንግሥት የሚጠየቀውን መስዋዕትነት ኹሉ ከፍሎ የዜጎችን ደኅንነት ካላስጠበቀ፤ አስፈላጊነቱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በሁሉም ሥፍራ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ተንቀሳቅሶ መሥራት፣ ያለሰቀቀን መኖር እና የደኅንነቱ መጠበቅ እንደ ዳገት ሊከብደው አይገባም፡፡

በተደጋጋሚ እንደገለጽነው የመንግሥት በጣም ትንሽ የሚባለው ኃላፊነት የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ይህንን መሠረታዊ መንግሥታዊ ግዴታ አለመወጣት የአቅም ማጣት ወይም የግዴለሽነት ችግር ነው፡፡ መንግሥት ያለበትን ሁኔታ በግልጽ አሳውቆ፤ ሕዝብን በማስተባበር ዘመቻ በማካሄድ የሽብር ቡድኑን አደብ ማስገዛት ይጠበቅበታል፡፡

ይህንን አለማድረግ ግን የቸልተኝነት ወይም የግድያው ተባባሪነትን ማሳያ ከመኾን ያለፈ ትርጉም የለውም፡፡ እዚህ ጋር መረሳት የሌለበት ዋና ጉዳይ ግን መሰል አይነት በደሎች የሚፈጥሩት ብሶት ዜጎች በራሳቸው ተደራጅተው ሰላምና እና ደህንነታቸውን ወደ ማስጠበቅ ይገቡና ወደ አላስፈላጊ ትርምስ ውስጥ ሊያስገባን እንደሚችል ነው፡፡ ይህን ከግንዛቤ በማስገባት ነገ ዛሬ ሳይሉ አፋጣኝና የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚኖርበት መንግስትን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

ምንም እኳን ላለፉት ጥቂት ዓመታት መንግሥት በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሽብር ድርጅቶች እንዲሁም በታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሴራ ተጨባጭ የሰላም እና ደኅንነት ቀውስ ውስጥ መግባቱን ብንገነዘብም፤ ባለንበት ወቅት በራሱ አንደበትና በመገናኛ ብዙኀን እንደምንመለከተው መንግስት ጠንካራ የፀጥታ መዋቅር ማደራጀቱን እና የማያዳግም የሰላም ማስከበር ሥራ እያከናወነ መኾኑን እየገለጸ ስለኾነ፤ የሸኔ የሽብር ቡድን እስካሁኗ ሰዓት ድረስ እንዳሻው መፈንጨት ምንም አይነት ምክንያት ሊቀርብበት የማይችል ሙሉ በሙሉ የመንግሥት የራሱ ድክመት መሆኑን ሊያምን ይገባል፡፡

በሕዝብ ይሁንታ የመንግስት መንበር ይዣለሁ ብሎ የሚያምን ኃይል ከመንግሥት ኃላፊነት ቀዳሚ የሆነውን መተላለፊያ ኮሪደሮች ማስከበር አለመቻል ሰበብ እንጂ ምክንያት ሊገኝለት አይችልም። እንዲህ አይነት አንገብጋቢ እና ቅድሚያ ሊሠጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ቢኖሩም አስቸኳይ እና አንገብጋቢ ባልሆኑ ችግሮች ላይ ትኩረት መሥጠቱ ዜጎችን ለከፍተኛ ጥርጣሬ ዳርጓል። በመኾኑም፤ ይህንን ሀገራዊ የኅልውና አደጋ በመገንዘብ የሚከተሉትን አስቸኳይ እና ዘላቂ እርምጃዎች እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡

See also  አሸባሪው ሕወሓት መሰረተ ልማትና ድልድይ የሚያፈርሰው ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማወናበድ ትርፍ ለማግኘት ነው – ትዴፓ

1ኛ/ የፌደራል መንግሥት በየጊዜው የጥፋት ተልዕኮውን እያሰፋና የራሱን ኃይል ለማግዘፍ የሚፍጨረጨረውን ኦነግ ሸኔን አደብ ለማስያዝና ዜጎችን ከሰቆቃ ለመታደግ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች ለህዝብ በይፋ እንዲያሳውቅ!

2ኛ/ ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ እንደገለጽነው በራሱ ብልጽግና መንግሥት ውስጥ ተሰግስገው ለአሸባሪው ቡድን ሚስጥራዊ ድጋፍ በማድረግ የህዝብን ሰቆቃ የሚያባብሱና የቡድኑን እኩይ ተግባር በቸልታ የሚመለከቱ በተዋረድ ያሉ አካላትን ቁርጠኛ ሆኖ በመታገል ምንጩን እንዲያደርቅ!

3ኛ/ አሸባሪው ቡድን በዚህ ወቅት አፋፍሞ በየአቅጣጫው እየፈጸመ ያለውን መርህ አልባ እንቅስቃሴ ከወዲሁ እንዲሽመደመድ ካላደረገና ትጥቅ በፍጥነት ማስፈታት ካልቻለ የተጀመረውን ድርድር ማስቀጠል አዳጋች እንደሚሆንበት አጥብቀን መግለጽ እንሻለን።

በመጨረሻም እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩ አስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃዎች ካልተወሰዱ በአሸባሪው ሸኔ ከዚህ ቀደም ለተፈጸሙትም ኾነ ከዚህ በኋላ ለሚፈጸም ግድያ፣ መፈናቀል፣ እገታ፣ ውድመት እና ሰቆቃ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የፌደራል እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በህሊና፣ በሕግ፣ በሕዝብ እና በታሪክ ተጠያቂ እንደሚኾኑ ሊያውቁት ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)

ሰኔ 17/2015 ዓ.ም.

Leave a Reply