ETHIO12.COM

በክልል አገር ስብከቶችና በኦርቶዶክስ እምነት አመራሮች ውስጥ ልዩነት እንዳይፈጠር ስጋት አለ

ሁለት ክልሎች ምን እየተደረገ እንደሆነ ሊገባቸው እንዳልቻለ ጠቅሰው ማብራሪያ መጠይቃቸውን አገረ ስብከቶቹ ለሚገኙበት አስተዳደር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተባባሪያችን ከአዲስ አበባ ዘግቧል። በሌላም በኩል የመስቀል አደባባይን ተንተርሶ እየተኬደበት ያለው አካሄድ ልዩነት እንዳይፈጥር የሰጉ አብቶችም አሉ።

መጠቀሚያ መሆንን የሚቃወሙ፣ ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያኒቱ ህልውና ላይ የተፈጸውን ድርጊት የማይረሱ፣ ዳግም ለበግ ለምድ ለባሽ ቀበሮዎች ሃሳብ ማሳኪያ ዕቃ መሆንን የማይመኙ፣ የቤተክርስቲያን ጥያቄ ታላቅነቷን ዝቅ በማያደርግ መልኩ ደርዝ ይዞ ከመጯጯህ ተላቆ እንዲከናውን የሚመኙ መኖራቸውን መዘንጋት አይገባም። በዚህ ደረጃ የሚመላለሱ ምዕመናን እንደሚበዙ ማወቅ ተገቢ ነው …

የሁለት ክልል አገረ ስብከት አመራሮች ለሚገኙበት ክልል የጠየቁት ዝርዝር ጉዳይ ባይገልጸም፣ ያራሳቸውን አቋም ለመያዝ ያመቻቸው ዘንዳ እየሆነ ስለለው ጉዳይ ጥርት ያለ ማብራሪያ እንዲሰጣቸው መነጋገራቸው ታውቋል። የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በታሪኳ ጸባና ሁከትን የምትዳኝ እንጂ ለሁከትና ለጸብ መነሻ እንዳልሆነች የሚያምኑት እነዚሁ ክፍሎች፣ በየጊዜው በቤተክርስቲያኗ ዙሪያ የሚሰማው ንትርክ አደጋው የከፋ እንዳይሆን ስጋት እንዳላቸው አመልክተዋል።

ስህተትን በመነጋገር ማረም፣ በተግሳጽ ምሳለፍ ሲገባ የሚዲያ ሲሳይ ሆኖ የሚያገባውም የማያገባውም ከመንፈሳዊ ባህሪያት ባፈነገጠ መልኩ የሚያካሄዱት ፍልሚያ ማንንም ተጠቃሚ እንደማያደርግ መመሪያ የጠየቁት አብቶች ማንገራቸውን ተባባሪያችን አስታውቋል። ይህ በዓለም ካሉ እንኳን ባምይጠበቅ ደረጃ መስቀል እያነሱ ምዕመን ከምዕመን እንዲጋጭ የሚያነሳሱ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ ቤተክርስቲያን በራስዋ አስተዳደር ማናቸውንም ጉዳይ እንድትይዝ በገሃድ የመጠየቅ አሳብ እንዳላቸውም አመልክቷል። የሚጠብቁት ለቀረቡት ማብራሪያ ምላሽ እስኪሰጣቸው ነው። ማብራሪያ እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸውን ክልሎች ማረጋገጫ እንዲሰጡ ጥያቄ ቢቀርብም ጥያቄ መቀረቡን ሳያስተባብሉ ዝርዝር መግለጫ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ጥልቀት ያለው ሪፖርት ማቅረብ አልተቻለም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ አማራና አፋር ክልል በዚህ ደረጃ ንጹሃን ሲገደሉ፣ መነኩሴ ቆባቸው ወልቆ ሲደፈሩና ንጹሃን በጅማላ ሲጨፈጨፉ ምንም ድምጽ አላሰሙም። በትግራይ ለደረሰው ቀውስ ግን በገሃድ የዓለም መንግስታትን ጣልቃ ገብነት መጠየቃቸው አይዘነጋም።

አገልግሎታቸው በአዲስ አበባ የሆነ አባት ” ምኑም አላማረኝም” ሲሉ ይህ አካሄድ መንፈሳዊነትን በሚያስቀድሙት የቤተክርስቲያኒቷ አባላት ዘንዳ ቅሬታ እንደፈጠረ ለተባባሪያችን አስረድተዋል። ከሌላኛው ወገንም መታበይና አጉል መባለግ እንዳለ ያመለከቱት አባት ” ይህ የልዩነት ምንጭ ሆኖ በዚህ ደረጃ መካሰስና መዘላለፍ ውስጥ መገባቱ ያሳዝናል” ብለዋል።



በመስቀል አደባባይ ጉዳይ ህጋዊ ጥያቄ ቀርቦ በንግግር፣ አለያም የህግ ሰዎች ጉዳዩን እንዲይዙት አድርጎ መከናወን ሲቻል አንዱ በሌላው ላይ እንዲነሳ የሚደረገው ቅስቀሳ ዋጋ የሚያስከፍልበት ደረጃ እንዳይደርስ ስጋት እንዳላቸው፣ ይህንኑ አንስተው ከአንዳንድ ባልደረቦቻቸው ጋር በጎንዮሽ መወያየታቸውን አስረድተዋል። ጉዳዩን በሽምግላና ለመያዝና ለመቋጨት፣ ያልተገባ ንግግር አድርገው ለጸብ ምክንያት የሆኑትም ሰዎችና ተቋማት በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው ቢኖሩም ብዙም እንደማይበረታቱ አመልክተዋል።

“መስቀል አደባባይ ንብረትነቱ የቤተክርስቲያኒቱ መሆኑ ሃቅ ነው። ግን አታጥረው፣ አትገነባበት ወይም ለሌላ ልማት ልታውለው አይችላትም” ያሉት አባት ህዝብ ተከባብሮ እንዲጠቀምበት ለማድረግ መንግስት ሳይኖር የሃይማኖት ተቋማት ቁጭ ብለው ቢነጋገሩ የሚቋጩት ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል። አያይዘውም መንግስት መንግስት ነው፤ የሚገባውን ክብር መስጠትም ሃዋሪያዊ ግዴታ ነው እንደሆነ አመልክተው በዚህ ደረጃ ቀውስ ሊፈጠር የቻለበት ምክንያት እንዳልገባቸው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ታሪክ ጳጳስ በህይወት እያሉ በላያቸው ላይ አዲስ መሪ በመሾም የቤተክርስቲያን አናቷ ለሁለት ተከፍሎ መሳቂያ ሆና ዕድሜ ስትገፋ ከቆየች በሁዋላ ይህን ሃፍረት የለውጡ አመራሮች በመቅረፍ ተከፍሎ የነበረውን ሲኖዶስ አንድ ማድረጋቸው ይታወሳል። ይህን ያደረገ መንግስት፣ ተውስዶ የነበረ ንብረት በቅጽበት የመለሰ መንግስት “እንዴት ጠላት ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል?” በሚል ተደጋጋሚ ከሚቃወሙት በላይ ብዛት ያላቸው ጥያቄ አቅራቢ ወገኖች እንዳሉ ይታወሳሎ።

ዝገጅት ክፍላችን በቀጣይ የክልል አገረ ስብከት አመራሮችን በማነጋገር እናቀርባለን። የመስቀል አደባባይ ጥያቄ ቁልጭ ብሎ ምን እንደሆነ ቃለ በቃል የሚናገር የለም። የባለቤትነትም ይሁን ሌላ ጥያቄ በስማ በለው በፈስ ሚዲያና የሴራ ፖለቲካ በሚፈልቅባቸው ሚዲያዎች ሳይሆን ሲኖዶስ በየወቅቱ ጥርት ያለ፣ የቤተክርስቲያኒቱን ደረጃና ክብር በተበቀ፣ ቅድስናዋን በሚመጥን ጨዋ አግባብ ለህዝብ መግለጫ ሊሰጥ እንደሚገባ የሚመክሩ አሉ። ከዚህ ውጭ የጨረባ ሰርግ ይመስል ደብዳቤ እየረጩ በየሚዳው መጯጯህ የቤተክርስቲያኒቱን ክብር የሚያጎድል እንጂ የሚያጎላ እንዳልሆነም አመልክተዋል። ቤተክርስቲያን እንደ ወንጌል መምህርነቷ እርጋታን፣ ማስተዋልን፣ መስከንን፣ ፍቅርን፣ ክብርን፣ መቻቻልን፣ ርህራሄን ባገኘችው አጋጣሚ ሁሉ ማስተማር ስለሚጠበቅባት ከዚህ ሃዋሪያዊ ተልዕኮዋ የሚያስታትን መንገድ ሁሉ ልጠየፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በመጨረሻ ዛሬ ይፋ በሆነ ዜና ጉዳዩን በሰላም ለማጠናቀቅ ቀጠሮ ተያዟል። ያንብቡ

የካቲት 4ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ለዛሬ ቋሚ ሲኖዶስ ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር ለመወያየት ቀጠሮ ተይዞበት በነበረው አጀንዳ ዙሪያ የከተማ አስተደዳደሩ ተወካዮቹ ከቋሚ ሲኖዶስ አባላት ጋር ከተወያዮ በኋላ ከንቲባዋ ቀድሞ በተያዘው የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ስብሰባ ምክንያት ዛሬ መገኘት ስላልቻሉ ቀጣዩ ውይይት በመጪው ማክሰኞ የካቲት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4:00 ሰዓት ከንቲባዋ በተገኙበት በመንበረ ፓትርያርኩ የቋሚ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይቱን ለማድረግ እና ችግሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቀጠሮ መያዙን ቅዱስ ፓትርያርኩና የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ በሰጡት የጋራ መግለጫ አረጋግጠዋል።

Exit mobile version