Site icon ETHIO12.COM

ትህነግ ሲያልቅ “መጋረብ” ጀምሯል

የትግራይ ህዝብ ያለቁበትን ልጆቹን እንዳይጠይቅ ሁልጊዜም በጦርነት ጠምዶ ለማቆየት በሚል ሴጣናዊ ተልዕኮ ነው አፋር ላይ ካራ የመዘዘው። ብዙ ርቀት አይወስደውም። መንግስት ይፋዊ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ የሚወስድ ከሆነ በቀናት ውስጥ ኮተቱን ሰብስቦ እንደልማዱ ወደመቀሌ መፈርጠጡ የማይቀር ነው። ለጊዜው ያስጨንቅ ይሆናል። የመንግስትም ዝምታ ሊያሳስብ ይችላል። ግን ጭንቀቱም ሀሳቡም በቅርቡ ምላሽ የሚያገኙ ይመስለኛል። ህወሀት ብዙ እድሎችን ያመከነ ቡድን ነው። ሌላ እድል የሚኖረው አይሆንም። የትግራይ ህዝብ የ300ሺህ ልጆቹን መጨረሻ እየጠየቀ ነው።

በመሳይ መኮንን
ህወሀት ያኮረፉ ቡድናችን መሰብሰብ ጀምሯል። በደህና ጊዜ ያጠራቀማቸውንና ያሰለጠናቸውን ፈረሶቹን አሁን ላይ ከያሉበት ጠርቶአቸዋል። ሰሞኑን አፋር ሲገባ ብቻውን አልነበረም። በፈረሶቹ ታጅቦ መሆኑ ተሰምቷል። የቀድሞ የአፋር ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩትን ሰው መቀሌ አስቀምጦ ሲቀልባቸው ከረመና ለሰሞኑ ወረራ አንድ የአፋር ስም የያዘ ቡድንና ጥቂት ታጣቂዎችን ሰጥቶአቸው አፋርን ነጻ እናወጣለን የሚል መፈክር አስጨብጦ አስገብቶአቸዋል። በሶማሌ ክልል ያኮረፉ ግለሰቦችንም እንዲሁ አሰባስቦና የዳቦ ስም አውጥቶላቸው ብጥብጥና ቀውስ እንዴት መፍጠር ይቻላል የምትል የአጭር ጊዜ ኮርስ ሊሰጣቸው ተዘጋጅቷል። ታማኝ ፈረሱ ሸኔ ቃሉን ሳያጥፍ፣ የህወሀትን ውለታ ለመክፈል ካራ ስሎ ንጹሃን ላይ ዘመቷል። ተመሳሳይ ላባ ያላቸው ወፎች ለጥፋት በረራ ሰማዩ ላይ ተፈናጠዋል። ኢትዮጵያን ቀውስ ውስጥ የመዝፈቅ ተልዕኮ አንግበው ተነስተዋል።

ከንቱ ልፋት ነው። የከሰረ ነጋዴ የዱቤ ደብተሩን ቢያገላብጥ ትርፍ አያገኝበት። ህወሀት ታንኩንና ባንኩን በመዳፉ በጨበጠበት ዘመን ያላሳካውን የኢትዮጵያ መፍረስ አሁን አከርካሪው ተሰብሮ፣ የሞት ጉንፋን እያሳለ ሊያደርገው ቢሞክር ውጤትም ትርጉምም የለውም። አፋር ዳግም የገባበት ምክንያት ፈጽሞ ልረዳው አልቻልኩም። በህወሀቶች ጭንቅላት ውስጥ ሆኜም ላስበውና ልመራመረው ሞክሬ አንጎሌን ከማስጨነቅና ከማዛል ያለፈ አንዳች ስሜት የሚሰጥ ነገር ላገኝ አልቻልኩም። በእርግጥ ሰዎች እየተገደሉ መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። የሰላማዊ ዜጎች መፈናቀልን አሁንም መስማት ልብን ይሰብራል። መንግስት እርምጃ እንደወሰደና በቀጣይም የተጠናከረ ምላሽ እንደሚሰጥ ፍንጭ ያገኘሁ ቢሆንም የእስከአሁኑ መዘግየት ያስከፈለውን ዋጋ በቀላሉ የማየው አይደለም። አሁንም የመንግስት የተጠናከረ እርምጃ ይጠበቃል። አፋሮች ኢትዮጵያን ባሉ ለምንስ እንዲህ ይሰቃያሉ?

የህወሀት ፈረሶች ከህወሀት ጋር የጀመሩት ጥምረት እስከየት እንደሚወስዳቸው እርግጠኞች ናቸው ብዬ አላምንም። አፋር ላይ ዳግም ሰይፍ ከመዘዘው ህወሓት ጋር የተሰለፉት አኩራፊዎቹ የቀድሞ የአፋር አመራሮችና ተከታዮቻቸው ወራጅ ወንዝ ላይ ተንሳፈው ከጥልቁ ጨፌ ውስጥ ተቀብረው የመቅረታቸውን ጉዳይ ለመግለጽ ነቢይ መሆን አይጠይቅም። ለራሱም መቆም አቅቶት ላለመውደቅ ከሚወዛወዘው ህወሀት ጋር መሰለፍ፣ ያውም የአፋር ህዝብ ላይ ትልቁን እልቂት የፈጸመውን ቡድን አጅቦ ለጥፋት መሰማራት ለጊዜው አደጋው በግልጽ ላይታያቸው ይችላል። መጨረሻቸው ግን ህወሓት ሳያስጥላቸው አውላላ ሜዳ ላይ እንደሚተወዋቸው ካልተረዱት ድንቁርና አንጎላቸው ውስጥ ቤቱን ሰርቶ ተደላድሏል ማለት ይቻላል። በክራንች ሆኖ እያነከሰ ደም እንዳሰከረው ጅብ ከሚንጠራወዘው ህወሀት ጋር መሰለፍ በገዛ እጅ የራስንም ሞት መጋበዝ እንጂ ሌላ ምንም ትርጉም የለውም።

ሶማሌ ክልልን ለማወክ የተነሱት አኩራፊዎች የሚገጥማቸው እጣ ፈንታም ተመሳሳይ ነው። ክልሉ የሰላም አየር እየማገ፣ ህዝቡም ከማያባራ ግጭት ተላቆ የተረጋጋ ህይወት እየመራ ባለበት በዚህን ወቅት ወደቀደመው የጨለማ ዘመን ሊመልሱት የተነሱት የኦብነግ ሀይሎችና መሰል አኩራፊ ፖለቲከኞች ሁለት ጊዜ ማሰብ ካልቻሉ መጨረሻቸው አጉል እንደሚሆን አልጠራጠርም። ሙስጠፌ ፍጹም ነው የሚል ድምዳሜ መስጠት ባይቻልም በአንጻራዊ መለኪያ የሶማሌን ህዝብ ወደ አዲስ ምዕራፍ ለመውሰድ የጀመራቸው ስራዎች መሬት እየረገጡ፣ ለውጥም እያመጡ መሆናቸውን መመስከር ይቻላል። ይህ አዲስ ምዕራፍ በፈተናዎች ሳይንበረከክ፣ ለቀውስ ጠማቂዎች እንዳይመች ሆኖ በማያወላውል መሰረት ላይ መቆሙን ያልተረዱት ጥቂት አኩራፊዎች የጥፋት አባታቸው ህወሀት ዘንድ መሄዳቸው በራስ አንገት ላይ ገመድ የማጥለቅ ያህል የሚታይ መጥፎ ውሳኔ ነው።

ህወሀት ክንፉ ተሰብሯል። እግሩ ተቆርጧል። ረጃጅም እጆቹ አጥረው ከትግራይ አልፈው እንዳይረዝሙ ተደርገዋል። ጀብደኝነትንና ባዶ ጉራን ታቅፎ የቀረው የህወሀት ቡድን ሰሜን ሸዋ ደብረሲና ድረስ ዘልቆ ያላሳካውን ቅዥቱን ዳግም የሚሞክርበት አቅምም፣ ሞራልም የለውም። አፋር ላይ የሚቧጨረው ያለ ጦርነት አንድ ሌሊት ማደር የማይችል ቡድን በመሆኑ ብቻ ነው። የትግራይ ህዝብ ያለቁበትን ልጆቹን እንዳይጠይቅ ሁልጊዜም በጦርነት ጠምዶ ለማቆየት በሚል ሴጣናዊ ተልዕኮ ነው አፋር ላይ ካራ የመዘዘው። ብዙ ርቀት አይወስደውም። መንግስት ይፋዊ የመልሶ ማጥቃት እርምጃ የሚወስድ ከሆነ በቀናት ውስጥ ኮተቱን ሰብስቦ እንደልማዱ ወደመቀሌ መፈርጠጡ የማይቀር ነው። ለጊዜው ያስጨንቅ ይሆናል። የመንግስትም ዝምታ ሊያሳስብ ይችላል። ግን ጭንቀቱም ሀሳቡም በቅርቡ ምላሽ የሚያገኙ ይመስለኛል። ህወሀት ብዙ እድሎችን ያመከነ ቡድን ነው። ሌላ እድል የሚኖረው አይሆንም። የትግራይ ህዝብ የ300ሺህ ልጆቹን መጨረሻ እየጠየቀ ነው። ነገ ድቅድቅ ሆኖ ጨልሞበታል። ዛሬን ከህወሀት መገላገል ይፈልጋል። ቢያንስ ከትግራይ ምድር የሚነሳ የህዝብ ብሶት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ህወሀትን ያሰናብታል። ካልሆነም ተደጋጋሚ እድል በሰጠው የኢትዮጵያ ህዝብ ግብዓት መሬቱ ይፈጸማል። በቅርብ የምናየው እውነት ነው። –

ነጻ አስተያየት – ርዕስ የተቀየረ

Exit mobile version