Site icon ETHIO12.COM

የትዳር አጋሩን በዘነዘና መትቶ የገደለው ግለሰብ በጽኑ እስራት ተቀጣ

የዐቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያሥረዳው ተከሳሽ ታምራት ቦጋለ ሸጎ ጥር 17 ቀን 2013 ዓ.ም በግምት ከሌሊቱ 4፡30 እስከ 6፡00 ባሉት ሰዓታት ውስጥ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ጉርድ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ “ለምን ለእራት ብር አልሰጠህኝም በሚል የትዳር አጋሩ ከሆነችው ሟች አመነች አብርሃም ጋር በተነሳ ጭቅጭቅ ሟች አመነች አብርሃምን የ4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው መንታ ልጆቻቸው ፊት በቡና መውቀጫ ብረት ዘነዘና ጭንቅላትዋንና አንገትዋን ደጋግሞ በመምታት ከገደላት በኋላ ወደ ወላይታ ሰዶ በመሄድ እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል፡፡

ዐቃቤ ሕግም ከፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ተገቢውን ማስረጃ የማሰባሰብ ስራ ካከናወነ በኋላ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ጉዳይ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 539/1/ሀ ስር በተደነገገው መሰረት በተከሳሽ ላይ የሰው ግድያ ወንጀል ክስ መስርቶ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ ችሎት አቅርቧል፡፡

በመቀጠልም ተከሳሹ ዐቃቤ ህግ ባቀረበበት ክስ ላይ የእምነት ክህደት ቃሉን እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ ጠይቆት ሙሉ በሙሉ ያላመነ በመሆኑ እንደካደ ተቆጥሮ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች እንዲሰሙ፤ የሰነድ ማስረጃዎቹም እንታዩ ተደርጓል፡፡ በዚሁም መሰረት ተከሳሽ እንዲከላከል ብይን የተሰጠ ቢሆንም ተከሳሽ መከላከያ ማስረጃ እንደሌለው ለፍ/ቤቱ በመግለፁ ፍ/ቤቱ በቀረበው የዐቃቤ ሕግ ማስረጃ መሰረት ተከሳሽ በወንጀል ህግ አንቀጽ 539/1/ሀ ስር ጥፋተኛ ሲል ፍርድ በመስጠት ታህሳስ 26 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

ከዚህ የክስ መዝገብ ላይ መማር ያለብን ጉዳይ በቀላሉ ተነጋግረን ልናልፋቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ስሜታችንን መቆጣጠር ሳንችል ስንቀር እራሳችንን ለእስር ሌሎችንም ለጉዳት መዳረጋችን ሊታፈስ እንደማይችል ውሃ ጸጸቱ ከባድ ነውና ከድርጊት በፊት ማሰቡ ይጠቅማል፡፡

Exit mobile version